>

አቤቱታ... እነሆ አዲስ አበባ እንዲህ ስትል ሰማኋት (እንዳለጌታ ከበደ)

‹…አዲስነቴን፣ አበባነቴን ልጠራጠረው ምንም አልቀረኝ፡፡ ውስጤም መልኬም ተዥጎርጉሯል፡፡ አኗኗሬ ሁሉ ‹ፀጉራም በግ አለ ሲሉት ይሞታል› የተባለው አይነት የሆነብኝ መሰለኝ፡፡ ሰልፉ ረዝሟል፡፡ ታክሲ ለመሳፈርም፣ ዳቦ ለመግዛትም ሰልፍና ግፊያው ጠንከር ብሏል፡፡ ህንጻዎችም ረዝመዋል፡፡ ግና መንገድና ህንጻ ብቻውን ቢዋብ፣ እንቁጣጣሽ መስሎ ቢንቆጠቆጥ፣ በከበረ ድንጋይ ቢሽሞነሞን በህንጻው የሚኖረው፣ በመንገዱ የሚመላለሰው ህዝብ ጭንቅላት ካልለማ፣ ለአዕምሮ ልማቱ ካልታሰበበት ህንጻ ብቻውን ምን ያደርጋል?
መሸት ሲል እናቶች ጨለማ ለብሰው ሲለምኑ አያለሁ፤ አባቶች ቡና የሚጋብዛቸው መንገደኛ ሲቀላውጡ አያለሁ፤ ታዳጊ ልጆች ትምህርት ቤት ሳሉ በተገኙበት በምግብ እጦት ምክንያት ህሊናቸውን ስተው እንደሚወድቁም አንብቤያለሁ፡፡

በደሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው ልዩነት አለቅጥ ሰፍቷል፡፡ ደሃው በገዛ ሀገሩ እንደባይተዋር ተቆጥሮ፣ እንደተሰደደ ሰው ቁዘማ እያበዛ ነው፡፡ ሳቁ በጥርሶቹም በልቡም መሀል የለም፡፡ ረግፏል፡፡ ተገፍቷል፡፡ ተገፏል፡፡ እንባው፣ ላቡና ደሙ እንደተነጠቀ ሰው ሆኗል፡፡ በየዕለቱ፣ በቲቪ ብቅ ብለው የሚያውቃቸው አንዳንድ ጉምቱ ባለስልጣናት በዘመድ አዝማዶቻቸው ስም ያስተከሏቸውን ህንጻዎች፣ ሆቴሎች መቁጠርና ማስቆጠር ሆኗል ስራው፡፡ እና ይሄን እያሰበ፣ አዲስ አበባ አሁን ነው አዲስ የሆነችው ሲባል አይዋጥለትም፤ ‹በእኔ በደሃው እንባ፣ በደሃው ላብ፣ በደሃው ደም የተሰራ ነው› ብሎ ሲያጉተመትም እየሰማሁ እንዴት እንቅልፍ ሊወስደኝ ይችላል? ይህ ጉምጉምታ ይህ ሹክሹክታ እየሰማሁ፣ ስለዥንጉርጉርነቴ የተጋነነ ነገር ሲነገር እያዳመጥኩ እንዴት ዝም ልል እችላለሁ?

… እናት ነኝ፤ የድሆቹ ቤተሰቦቼ ልብ ጠፍ መሬት እንዲሆን አልፈልግም፤ የቅናት እሾህና የበቀል ኩርንችት እንዲበቅልባቸው አልመኝም፤ ግን ወደ ሰገባቸው እስኪመለሱ፣ ጊዜ የሚወስዱ ሰይፎች በልጆቼ እጆች እንዲታዩ አልፈቅድም፤ ልጆቼ እርስበርስ በዘር ተከፋፍለውና በወንዝ ተካለው እንዳይዋዋጡብኝና እንዳይበላሉብኝ ጸሎቴ የፀና ነው፡፡ የማይፈሩ፣ የማይተፋፈሩ፣ በድፍረት የሚነጋገሩ፣ በላ ልበልሃ ገጥመው ለመዋቀስና ለመካሰስ የማይሰንፉ ዜጎች እንዲኖሩኝ ነው ህልሜ፡፡
በፊት እኮ እንዲህ የበዛ አልነበረም፡፡ ሙስና ገነትን ወደ ምድር ለማውረድ የሚታገል ብሔራዊ ሃይማኖት አልነበረም፡፡ ሌብነት ህጋዊ ፍቃድ የተሰጠው ሙያ አልነበረም፡፡ ከወንድም ነጥቆ መጉረስ የፊተኞች መንግስት ባለስልጣናት መገለጫ አልነበረም፡፡ ምነው የኢሳያስ ትንቢት ተዘነጋ? ምነው፣ ‹ጉቦን ለመቀበል በደለኛን ንጹህ ለሚያደርጉ፣ ለበደል አልባ ሰው ፍትህን ለሚነፍጉ ወዮላቸው!› ብሎ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ችላ ተባለ? ምነው ነብዩ ‹የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣ የእነሱም ስር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደትቢያ ይሆናል፡፡› ብሎ ስለ ጉቦ ተቀባዮችና ፍትህ አጉዳዮች የተናገረው ቃል ተናቀ? ምነው የእውነት ብርሃን ጨለመ?
በእውነቱ አሞኛል፤ መንፈሴ ታውኳል፤ ልቤ እንደመንገዴ ተቆፍሮ በአዲስ መልክ ተቀይሷል፡፡ ደሃው አንገቱን ደፍቶ ያዘነበው እንባ ቢጠራቀም የበቀሉብኝን፣ በሙስና ታንፀዋል የተባሉትን ፎቆች ከእግር ጥፍራቸው እስከራስ ጸጉራቸው የሚያጥብ ይመስለኛል፡፡
ልቤ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ እየሄድኩ ይሁን እየመጣሁ፣ እየነቃሁ ይሁን እየተኛሁ፣ እየታደስኩ ይሁን እየፈረስኩ ግራ ገብቶኛል፡፡ መንግስት ‹እያሽሞነሞንኩሽ ነው፤ አለምሽን እያሳየሁሽ ነው፤ ከመሰሎችሽ እንዳታንሽ እያደረግኩሽ ነው› ይለኛል፡፡ ነዋሪው ደግሞ ‹እያስገፈተርሽን፣ እያስደፈርሽን፣ ጉርሻችንን እያስነጠቅሽን፣ ከእርስታችን እያስፈነቀልሽን ነው› ይሉኛል፡፡ ምን እየሆንኩ ነው?
አሁን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተሰምቶኛል፡፡ ሰሞኑን በእኔ ክልል ስር ያሉ ህንጻዎችን አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት አለብኝ፡፡ ከየት መጣችሁ? ማነው የተከላችሁ? ስር መሰረታችሁ ምንድነው? ከመቼው በቀላችሁ? ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ምነው የተቀመጣችሁበት የሹም ወንበር፣ የምትተነፍሱት አየር፣ የምትናገሩበት ቋንቋ፣ የምትቀዱበት ምንጭ ተመሳሳይ ሆነ ብዬ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ ምን ብሎ እንደሚተቻቸው፣ ምን ብሎ እንደሚጠቋቆምባቸው ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ የተሰራችሁበት ንጥረ ነገር ሀቅ የወለደውና በኪራይ ሰብሳቢነት ያልተሰበሰበ ከሆነ ይባርክላችሁ ብዬ ልመርቅላችሁ፤ በህዝቡ ላብ፣ እንባና ደም የተሰራ ከሆነም ሰርቃችሁ የወሰዳችሁትን ገንዘብ መልሱ፤ የበደላችሁትን ህዝብ እንባ አብሱ ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ካልሆነ፣ የነጠቅነውን አንመልስም ይሉ እንደሆነ የወሰዳችሁት ገንዘብ ይነቃችሁ፤ ከፈን መግዣም ይሁናችሁ ብዬ ልረግማቸው እፈልጋለሁ፡፡

Filed in: Amharic