>

”የህወሓት የበላይነትን ለማስቀጠል የአማራን ሕዝብ ማስተማር ይገባል!” (ስዩም ተሾመ)

ጥር 12/2010 ዓ.ም “በወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታ የብሮድካስት ሚዲያ አዝማሚያ” በሚል ሃገራዊ የሚዲያ ኮንፍረንስ መካሄዱ ይታወሳል። በዚህ ኮንፍረንስ ላይ የኢትዮጲያ ብሮድካስት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ዘርዓይ አሰግዶም አረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩ ባንዲራ ምስል ያለበት የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ማስታወቂያ “እንዴት በአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ የፌስቡክ ገፅ ላይ ይወጣል?” በማለት አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ተችተዋል። እንደ አቶ ዘርዓይ አገላለፅ፣ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ቀለማት ያለበትን ነገር በማህበራዊ ሚዲያዎች መልቀቅ ሆነ ማስተዋወቅ ሕገ-መንግስቱን አለመቀበል እንደሆነ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ባለ ኮከቡ ባንዲራ ሲቃጠል “ሕገ-መንግስቱ እንደተቃጠለ ወስዶ ሕዝቡን ማስተማር እንደሚገባ” ሲገልፁ ተስተውሏል።

ከላይ በተጠቀሰው ዕለት እኔ በአዲስ አበባ በኩል ወደ አሰላ እየሄድኩ ነበር። ዕለቱ የጥምቀት ማግስት እንደመሆኑ ከዓለምገና-ሰበታ እስከ አቃቂ-ቃሊቲ ድረስ መንገዶቹ ሁሉ በባንዲራ አሸብርቀዋል። በየቦታው የተዘረጋው ባንዲራ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ሆኖ መሃሉ ላይ የኮኮብ ምልክት የለውም። በእርግጥ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ በአረንጓዴ-ቢጫ-ቀዩ ባንዲራ መሃል ባለ ኮከቡ ባንዲራ “በመርፌ-ቁልፍ” ተያይዞ ተመልክቼያለሁ።

ከዚህ በተጨማሪ፣ አብዛኞቻችን በዘንድሮ ታላቁ ሩጫ ላይ የፌደራል ፖሊሶች አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ያለበትን ነገር በሙሉ ከተሳታፊዎች ሲቀሙ እንደነበር ይታወሳል። በአጠቃላይ የቀድሞ ባንዲራ የሚውለበለብበት ቦታ ከግዜ-ወደ-ግዜ እየሰፋና እየጨመረ መምጣቱን መገንዘብ ይቻላል። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ጨምሮ የማህብረሰቡ አቋምና አመለካከት ከተቀየረ ሰነባብቷል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ባንዲራን ጨምሮ በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ባለበት ቆሞ የቀረው ህወሓትና ህወሓት ብቻ ነው።

ከዚህ አንፃር ለምሳሌ አቶ ዘርዓይ አሰግዶም ባንዲራ እና ሕገ-መንግስቱን በማያያዝ ያቀረቡትን የመከራከሪያ ሃሳብ እንመልከት። የብሮድካስት ባለስልጣኑ ኃላፊ እንደገለፁት ባለ ኮከቡ ባንዲራ ሲቃጠል ሕገ-መንግስቱ እንደተቃጠለ ወስዶ ሕዝቡን ማስተማር ይገባል። ነገር ግን፣ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የተመሰረተው በባንዲራ መቃጠልና አለመቃጠል ላይ ሳይሆን ከአንቀፅ 8-12 በተዘረዘሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ ነው። የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረታዊ መርሆች፤ አንቀፅ (8)፡- የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ አንቀፅ (9)፡- የሕግ-መንግስት የበላይነት፣ አንቀፅ (10)፡- ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ አንቀፅ (11)፡- የመንግስትና ሃይማኖት መለያየት፣ እና አንቀፅ (12)፡- የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ መርሆች መንግስታዊ ስርዓቱ የተመሰረተባቸው ምሶሶዎች (pillars) ናቸው። በስልጣን ላይ ያለ መንግስት፤ የሕዝብ ሉዓላዊነትና የሕግ-መንግስቱን የበላይነት ማረጋገጥ፣ እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር ከተሳነው፣ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ-የሚገባ ከሆነ፣ እንዲሁም ሥራና አሰራሩ ግልፅነትና ተጠያቂነት ከሌለው የተመሰረተበትን መሰረታዊ ዓላማ ስቷል።

በዚህ መሰረት፣ ከተጠቀሱት መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አንዱን ወይም ሁለቱን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የተሳነው መንግስት ከተወሰነ ግዜ በኋላ ይወድቃል። ምክንያቱም ሕልውናው የተመሰረተበትን መርህ ተግባራዊ ማድረግ የተሳነው መንግስት ፋይዳ-ቢስ ነው። በመሆኑም በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ያጣል። በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነቱን ያጣ መንግስት ከተወሰነ ግዜ በኋላ ወይ በምርጫ አሊያም በአመፅ ከስልጣን ይወገዳል።

ነገር ግን፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ መርሆች ተግባራዊ ማድረግ ተስኖታል። በቀላሉ የፀረ-ሽብር ሕጉ ብቻውን ከአምስቱ መርሆች ውስጥ አራቱን በቀጥታ ይጥሳል። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- የፀረ-ሽብር ሕጉ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይጥሳል። ሁለተኛ፡- አንደኛ ላይ በተጠቀሰው መሰረት የፀረ-ሽብር አዋጁ የሕገ-መንግስቱን የበላይነት ይጥሳል። ሦስተኛ፡- የፀረ-ሽብር ሕጉ በገዳም የሚኖሩ መለኩሴዎች እና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችን ለመክሰስ፣ በዚህም በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ያገለግላል።

አራተኛ፡- በመንግስት ሥራና አሰራር ላይ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ሃሳብና አስተያየት የሰጡ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያንና የመብት ተሟጋቾችን በሽብርተኝነት ወንጀል ለመክሰስ ያገለግላል። በዚህ መሰረት፣ ከላይ ከተጠቀሱት አምስት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አራቱ (4) በፀረ-ሽብር ሕጉና በአተገባበር ሂደቱ ተጥሰዋል።  እስካሁን ድረስ በኢህአዴግ መንግስት ያልተጣሰው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ ብቻ ነው።

በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ (8) መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” በማለት ይደነግጋል። የሉዓላዊ መብትና ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ባለቤትነትና የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆኑት ብሔሮች ደግሞ እንደ ዜጎች መብታቸውን በራሳቸው መጠየቅ ሆነ መጠቀም አይችሉም።

ከዚያ ይልቅ፣ በብሔሮች ስም የዜጎችን ሉዓላዊ መብትና ስልጣን በመግፈፍ የራሱን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ እየተጠቀመበት ያለው ህወሓት ነው። ስለዚህ አንቀፅ 8 እስካሁን ያልተጣሰበት መሰረታዊ ምክንያት የህወሓት የበላይነት በዚህ መርህ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተው የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት ከፅንሰ-ሃሳብ ጀምሮ የህወሓትን የበላይነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል ተደርጎ የረቀቀ ነው።

በአጠቃላይ ሕገ-መንግስቱ የፈረሰው በ2001 ዓ.ም የፀረ-ሽብር ሕጉ ተግባራዊ ሲደረግ ነው። አሁን በላው ነባራዊ ሁኔታ “ሕገ-መንግስቱን ማስከበር” ማለት የህወሓት የበላይነት ማስቀጠል ነው። ከዚህ አንፃር “ባለ ኮከቡ ባንዲራ ሲቃጠል ሕገ-መንግስቱ እንደተቃጠለ ወስዶ ሕዝቡን ማስተማር ይገባል” የሚለው የአቶ ዘርዓይ አሰግዶም አገላለፅ “የህወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል የአማራን ሕዝብ ማስተማር ይገባል” የሚል እንድምታ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል።

Filed in: Amharic