>
5:18 pm - Saturday June 15, 5163

ኢኤን ኤን የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በግለሰብ ስም የተከፈተ የመከላከያ አዛዦች ንብረት መሆኑን ምንጮች ገለጹ (ኢሳት)

(ኢሳት ዜና ጥር 25 ቀን 2010 ዓም)

የህወሃት የፌስ ቡክ ሰራዊት አባላት ከመንግስት ካዝና ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያገኙ ምንጮች አጋልጠዋል
ኢን ኤን ኤን የተባለው እና በግለሰብ ስም የሚንቀሳቀሰው የቴሌቪዥን ጣቢያ የመከላከያ ንብረት መሆኑን ታማኝ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ቢኒያም ከበደ በሚባል ግለሰብ ስም የተከፈተ ቢሆንም፣ ንብረትነቱ የመከላከያ ሰራዊት ኣዛዦች ነው።

በጄ/ል ሳሞራ የኑስ ዋና አዛዥነት፣ ከ95 በመቶ በላይ በአንድ ብሄር አባላት የሚመራው መከላከያ ሰራዊት፣ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ሙሉ ባጀት መድቦ እያንቀሳቀሰው ይገኛል። ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከወራት በፊት በአማራና ኦሮሞ ብሄሮች መካከል ግጭት የሚፈጥር ቀስቃሽ ዘገባ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ በቅርቡ የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ኢኤን ኤን ሁለቱን ብሄሮች ለማጋጨት ሆን ብሎ የሰራው ዘገባ ነው በማለት በድፍረት እስከመናገር ደርሰው ነበር። ለኢኤን ኤን ድጋፍና ከለላ የሚሰጠው በዘራይ አስጎደም የሚመራው ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ አመራሮች ስልጣን መልቀቅ ነበረባቸው በማለት አቶ ንጉሱ መናገራቸውን ተከትሎ፣ የኢኤን ኤን ጋዜጠኞች የብአዴን አመራሮችን የሚተቹ ጽሁፎችን በፌስ ቡክ ላይ ለቀዋል።

አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ ኢ ኤን ኤን ከጀርባው ጠንካራ ድጋፍ የሚሰጠው አካል እንዳለ በንግግራቸው የጠቆሙ ቢሆንም፣ በግልጽ ያንን አካል ለመጥቀስ አልደፈሩም። የኢሳት ታማኝ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ ኢ ኤን ኤን የህወሃት ጄኔራሎች በነጻ ሚዲያ ስም ያቋቋሙትና ሙሉ በሙሉ በጄኔራሎች የሚመራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ሚሚ ስብሃቱ በምትባል ጋዜጠኛ ስም የተቋቋመው ዛሚ እየተባለ የሚጠራው የሬዲዮ ጣቢያ ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከደህንነት መስሪያ ቤቱና ኢፈርት ከሚባለው የህወሃት ኩባንያ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል። በጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ የዛሚን አመታዊ በጀት የሚሸፍን ሲሆን፣ ጋዜጠኞችም በደህንነት መስሪያ ቤቱ እየታዘዙ በፈለጉት ባለስልጣን ላይ አስተያየትና ትችት ሲያወርዱ የሚጠይቃቸው ግለሰብ የለም።

ጌታቸው አሰፋና ሳሞራ የኑስ ህወሃትን በበላይነት ለመያዝ ትግል ማድረግ ከጀመሩ መቆየታቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ በቅርቡ ህወሃት ባደረገው ጉባኤ ችግሩ እንደተፈታ የተገለጸ ቢሆንም፣ ሽኩቻው ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው። የሁለቱ ሚዲያዎች እጣ ፋንታም በእነዚህ ሁለት የህወሃት ባለስልጣናት እጣ ፋንታ እንደሚወሰን ምንጮች ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ሚልኪያስ የሚባል እና ተፈራ የሚል የሃሰት የአባት ስም የሚጠቀም “ጎግል” መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰራ ግለሰብ የአብዛኞቹን ባለስልጣናት ዌብሳይት በመክፈት እየተቆጣጠረው እንደሚገኝ ምንጮች ገልጸዋል። ካናዳ ውስጥ የሚኖረው ግለሰብ Ethiopia prosperous, Konjo Ethiopia የተባሉ ዌብሳይቶችን ያስተዳድራል። ሚሊኪያስ ቡና ያለቀረጥ ወደ ካናዳ በማስገባት ከፍተና ትርፍ እያጋበሰ ከመገኘቱም በላይ፣ ለባለስልጣኖች በሚሰጠው የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሁም ዌብሳይቶቹን ለሚያስተዳድርበት ካናዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፈለው ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ግለሰቡ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ለአምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን፣ ለአስቴር ማሞና ለሌሎችም ባለስልጣናት የዌብሳይት እና የኢንተርኔት ስራዎችን እንደሚሰራላቸው በዚህም ከኢትዮጵያ ኢምባሲ ደጎስ ያለ ክፍያ እንደሚከፈለው ታውቋል። “ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ለ”ጎግል” ካመለከቱብኝ ስራየን ሊያሳጡኝ ይችላል” በሚል ፍርሃት፣ ሚሊኪያስ የአባቱን ስም መቀየሩን የሚገልጹት ምንጮች፣ አጠቃላይ የአገዛዙን ባለስልጣናት የኢንተርኔት እንቅስቃሴ በበላይነት በመምራት መረጃዎችንም እንደልብ እንደሚያገኝ በዚህም የተነሳ የጠየቀው ክፍያ እንደሚፈጸምለት አክለው አስረድተዋል።

ህወሃት በበላይነት ከሚያንቀሳቅሳቸው ፋና፣ ዋልታ ፣ ኢ ኤን ኤን፣ ዛሚ ከመሳሰሉት ሚዲያዎች በተጨማሪ፣ መረጃዎችን አውራምባ ታይምስ ዌብሳይት ያሰራጫል። አውራምባ ታይምስ ቀድሞ በተቃዋሚነት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ታስሮ ከተፈታና ውጭ አገር ተሰዶ የተወሰኑ አመታትን ቆይቶ ፣ ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ድርድር ወደ አገር ቤት በተመለሰ ዳዊት ከበደ በተባለ ግለሰብ የሚመራ ሲሆን፣ የመንግስት መስሪያ ቤት የሆነው የፖስታ ድርጅት ለዳዊት ከበደ 100 ሺ ብር በአመት እየከፈለው የሚገኝ ሲሆን፣ በህወሃት ትዕዛዝ ክልሎች ተገደው የልማት ቪዲዮ እንዲያሰሩና ስራውን ደግሞ ዳዊት የተባለው ግለሰብ እንዲሰራው እንደሚደረግ፣ ለዚህም ስራው ለ30 ደቂቃ የቪዲዮ ስራ፣ 80 ሺ ብር እንደሚከፈለው ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት ምንጮች ገልጸዋል። ዳዊት ከበደ በሌሎች የህወሃት አባላት ዘንድ በጥርጣሬ እንደሚታይ እና ሌሎች የህወሃት አባላት “ማንም የተቃዋሚ ትራፊ መሃላችን አስገብታችሁ ማጅራታችንን እንዳታስመቱን” እያሉ እንደሚያሸማቅቁት ምንጮች ገልጸው፣ በተለይም እስጢፋኖስ ፊት ለፊት በተሰጠው አፓርትማ መኖሪያ ቤት ዙሪያ ጥያቄዎችን እያነሱበት ነው። “ እኛም አፓርትማ እንዲሰጠን ትንሽ ወደ ተቃዋሚው ገባ ብለን እንውጣ” በማለት አንዳንድ የህወሃት አባላት የሰላ ትችቶችን እንደሚሰነዝሩበት ምንጮች ገልጸዋል።

በውጭ አገር የሚገኙ የህወሃት አባላት ገንዘብ እያሰባሰቡ በአቶ ስብሃት ነጋ በኩል ከሚልኩት ገንዘብ፣ ዳዊት ከበደና ሌላው የህወሃት አባል የፌስቡክ ሰራተኛ የሆነው ዳንኤል ብርሃኔ ተከፋይ መሆናቸው ታውቋል። ዳንኤል ብርሃኔ የተባለው ግለሰብ ከኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መስሪያቤት 17 ሺ ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈለው ሲሆን፣ ላፕቶፕ እና ሲዲኤም ኤ ተሰጥቶት የተለያዩ ጽሁፎችን በፌስ ቡክ ላይ በመልቀቅ የድርጅቱን ስራዎች ይሰራል። የኢንተርኔት ወጪውም ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤቱ ነው። ግለሰቡ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ አንዳንድ ኢምባሲዎች “ራሱን ገለልተኛ አስምስሎ” በማቅረብ፣ መረጃዎችን እየጻፈ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኢምባሲዎችም እንደ ገለልተኛ ግለሰብ ቆጥረውት ክፍያ ይፈጽሙለታል። ከዚህ በተጨማሪ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና ለሌሎችም መስሪያ ቤቶች ጽሁፎችን ከኢንተርኔት ገልብጦ በመጻፍ ክፍያ የሚፈጸምለት ሲሆን፣ በአንድ ወቅት ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከኢንተርኔት ወስዶ የጻፈው ጽሁፍ በመጋለጡ፣ በክፍያ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር።

የዳንኤል ብርሃነ ወንድም የሆነው ፍጹም ብርሃነ የተባለው ግለሰብ ደግሞ፣ ቀድሞ የኮሚኒኬሽን ተጠሪ ሆኖ ሲሰራ በነበረው ጌታቸው ረዳ ቀጥተኛ ትዕዛዝ፣ ከመመሪያ ውጭ የሚኒስትሩ ልዩ ረዳት አማካሪ ሆኖ ተቀጥሮ ያለምንም ስራ ወርሃዊ ደሞዝ ሲከፈለው ቆይቷል። ጌታቸው ረዳ ከሃላፊነቱ ሲነሳ ክፍያውም መቋረጡን ምንጮች ገልጸዋል። የፍጹም ቅጥር ጉዳይ በመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ውስጥ ትልቅ ውዝግብ ፈጥሮ ቆይቷል።

ዋሲሁን ተስፋዬ የተባለው የፌስቡክ ጸሃፊ ደግሞ ከኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር 17 ሺ፣ ከፖሊሲና ጥናት ምርምር 10 ሺ እንዲሁም ከብአዴን ጽ/ቤት አዲስ አበባ ቅርንጫፍ 6 ሺ ብር በድምሩ በወር 33 ሺ ብር እንደሚከፈለው ምንጮች አጋልጠዋል።
እነዚህ ዋና ዋና የሚባሉት የህወሃት የኮሚኬሽን ሰራተኞች ከመንግስትና ከድርጅቶቻቸው ከሚያገኙት ክፍያ በተጨማሪ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ስም እንዲሁም የተለያዩ በአላት ሲዘጋጁ በአማካሪነትና በጸሃፊነት እየተሳተፉ ከፍተኛ ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ይከፈላቸዋል።

ህወሃት በማህበራዊ ሚዲያ ለሚሳተፉ የፌስ ቡክ ሰራዊት አባላት እንደተጽኖ ፈጣሪነታቸው እየታዬ በ” ሼር፣ ላይክና ኮሜንት” ወይም በስርጭት፣ ተወዳጅነትና አስተያየት ብዛት እየቆጠረ ከመንግስት ካዝና ገንዘብ እንዲከፈላቸው ያስደርጋል። ዝቅተኛ ተከታይ ያላቸው የፌስ ቡክ ካድሬዎች እስከ 2 ሺ ብር ወርሃዊ ክፍያ ሲያገኙ፣ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው ደግሞ እስከ 5 ሺ ብር በቋሚነት ይከፈላቸዋል። ተከታዮቻቸው ባደጉላቸው ቁጥርም ክፍያቸው በዚያው ልክ እንደሚያድግ፣ አጠቃላይ የኢንተርኔት ወጪያቸው የሚሸፈነው በኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤቱ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የማህበራዊ ሚዲያው የሳይበር ሰራዊት በሚል በህቡዕ የተደራጀ ሲሆን፣ እንቅስቃሴውን ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል፣ በረከት ስምዖንና ጌታቸው ረዳ እንደመሰረቱት ታውቋል። በእነዚህ 3 ሰዎች ስር ደግሞ 5 በፌስቡክ፣ 2 በዌብሳይቶች ላይ የሚሰሩ እንዲሁም ጠላት ብለው የፈረጁዋቸውን ዌብሳይቶች የሚከታተሉ እና ግብረመልስ የሚሰጡ ሰዎች ተመድበዋል። 2 ግለሰቦች ደግሞ በፌስቡክ ላይ የሚወጡ ጽሁፎችን እየተከታተሉ ለባለስልጣናት የሚያሳውቁ ሲሆኑ፣ ከኢህአዴግ ጽ/ቤት የተላከና ለሚሰጡ አስተያየቶችና ጽሁፎች ፖለቲካዊ ትርጉም እየሰጠ መልስ እንዲጻፍ የሚያደርግ አንድ ግለሰብ መኖሩን ምንጮች ጠቁመዋል። ለህወሃት የፌስ ቡክ ሰራዊት ድጋፍ የሚሰጡ ከኢንፎርሜሽን ደህንነት ኤጀንሲ የኑስ ፣ ከመከላከያ ሰራዊት ኮ/ል ህሉፍ ፣ ከፌደራል ፖሊስ ገብረ እግዚአብሄር፣ እንዲሁም ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት መስሪያ ቤት ደግሞ አባይ የሚባሉ ግለሰቦች አሉ። እነዚህ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉትን መረጃዎች በመያዝ ግብረመልስ እንዲሰጥ ከማድረግ ጀምሮ ማንኛውንም የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣሉ።
በሳይበር ሰራዊቱ አማካኝነት የተከፈቱ በርካታ የፌስ ቡክ አካውንቶች ያሉ ሲሆን፣ አካውንቶችም በተቃዋሚ፣ በሴት ፣ በወንድ፣ በተሳዳቢ፣ በተረጋጋ ሰው እና በመሳሰሉት ሰዎች ባህሪ የተከፈቱ ናቸው።

ከእነዚህ በተጨማሪ በፌደራልና በክልል ኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤቶች የተደራጁ የፌስ ቡክ ሰራዊት የሚባሉ መኖራቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ ዮናስ በሚባል ግለሰብ የሚመራ እና ከቻይና በተወሰደ ልምድ የተቋቋመ የማህበራዊ ሚዲያ ዳይሬክቶሬት መኖሩን አክለው ገልጸዋል።

Filed in: Amharic