>

ነጩ…ፈረስ ማነው? …(ጥላሁን ጽጌ)

ከአድዋ ጦር ማግስት በቆሰለ አርበኛ የተማረከ ሰው
እልፍኝ ውስጥ ሆኖ እንደዚህ ጠየቀ…
“ሲወጋ፣ሲያዋጋ፣ሲያጠቃን የነበር
ነጩ ፈረስ የታል?”
ይሄ …ነጭ ወራሪ ይቀልዳል ልበል?

ነጩ ፈረስማ?!
ጦርነት ስትለፍፍ ፣ ድንበር ስትገፋ
መሬት ስትቆፍር ፣ ዱካ ስታሰፋ
ይቅርብህ እያለ ምክር ያቀረበው
አላወክም እንጂ ነጩ ፈረስ? ያ ነው!

ነጩ ፈረስማ!?
አይገባውም ብለህ ፣ አልተማረም ብለህ እንደ ስፔን ፣
ፖርቹጋል እንግሊዝ ተመኝተህ
አፍሪቃ ምድር ላይ ግዛት ልያዝ ብለህ
ሰውነቱን ንቀህ
በጥቁረቱ ስቀህ
በብረት ካቴና አስረህ ያደማኸው
አላወክም እንጂ ነጩ ፈረስ ያ! ነው!

ነጩ ፈረስማ!?
ከኤርትራ ምድር መቀሌ አምባላጌ፣
ማን አለብኝ ብለህ ስትገፋ ስትወርረው አይገባውም ብለህ
ውጫሌ ምድር ላይ
በቃላት ውስጥ መርዝ ለውሰህ ሰጥተኸው እውነቱን
ተርጉሞ “እምምቢ” ያለህ ሰው ነው!!

ነጩ ፈረስ የታልል?
ነጩ ፈረስ የታልል??
ይሄ ነጭ ወራሪ ይቀልዳል ልበል??

ነጩ ፈረስማ!
ያንተን ስልጡን ሀገር ፣ የሰለጠነን ሰው የዘመነውን ጦር ፣
የታጠቀን አረር መትረየስ ሳይፈራ ፣ መድፉን ቁብሳይሰጠው
እምቢ ላገር ብሎ የተዋጋህ ሰው ነው!!

ነጩ ፈረስማ?!
ነጩ ፈረስማ!?
ተደፈርኩኝ ብሎ ከሰሜን፣ደቡብ ጫፍ
ምዕራብ ምስራቅ ነቅሎ
የከፋ ዘመኑን ፣ የሆድ ስሞታውን
ተመደፈር በታች አቅልሎ አሳንሶ
ግማሹ በፀሎት ጨፌውን ነስንሶ
ግማሹ በወኔ ጎፈሬውን ነቅሶ
እንደ አንበሳ አግስቶ ፣
እንደነብር ዝቶ
በምታ ነጋሪት ሁሉም በአንድ ከቶ
አድዋ ምድር ላይ በጦር በጎራዴ የተጋፈጠህ ሰው
አላወክም እንጂ ነጩ ፈረስ ያ ነው!!

ነጩ ፈረስ የታል??!
ነጩ ፈረስ የታል!??
ይኼ… ነጭ ወራሪ ይቀልዳል ልበል?!

ነጩ ፈረስማ?!
የጣይቱን ምክር ያባ መላን መላ
እሺሺ ብሎ ሰምቶ በልቡ እያብላላ የእቴጌዋን ምድር
ትዕዛዝ አክብሮ የምትጠ~ጣውን ምንጭ ከብቦተቆጣጥሮ
ውሃ ውሃ ያሰኘህ ደንቆሮ ነው ያልከው አላወክም እንጂ
ነጩ ፈረስ ያ! ነው!!

ነጩ ፈረስማ…
ነ~ጩ ፈረስስማ!!?
እምነት በልቡ አስሮ አንድነት አክብሮ ፈጣሪውን ሰምቶ
ከራሱ ጋር ታርቆ
ጦርና ጎራዴ ባጭር ባጭር ታጥቆ
ሆ…ብሎ ሲመጣ ሆ…ብለህ ተኩሰህ
አገር ትኑር ባለ … አገር ትኑር ባለ
አገሩ ላይ ገድለህ
እሳት የሚተፋ ባሩዱ ሲያልቅብህ
በቀደመው ጥይት ቆስሎ የማረከህ
ደሙ እየፈሰሰ ውሃ ጠጣ ያለህ
አይገባውም ብለህ ንቀህ የደፈርከው
ንቀቱን ዋጥጥ አርጎ አንተን የማረከው

ነጩ ፈረስማ
መቀሌ አምባላጌ ዶግ አመድ አድርጎህ በአድዋ ተራሮች
እፍረት አከናንቦህ ባቆሰልከዉ ጀግና እፍረት እጅ ሰጥተህ
ማተብ ባታከብርም ማተብ እያሳህ
እልፍኝ አስገብቶ አብልቶ ያጠጣህ
ሮምን የጣለ አለም ያከበረዉ…
ሮሮ…ምን የጣለ አለም ያከበረው
የጥቁር ህዝብ ኩራት መመኪያ የሆነው ለማረከው ግብር
ጥሎ ያጠገበው
የአድዋው ጀግና የቴዎድሮስ ልጁ
የ ዩሃንስ ወንድም የ ጣይቱ ባሏ
አላወክም እንጂ ነጩ ፈረስ ያልከው
የጥቁር ህዝብ ኩራት ንጉስ ምኒሊክ ነው!!
ነጩ ፈረስ
ማነው?

Filed in: Amharic