>

ሁላችንም ፌሚኒስት መሆን አለብን! (ክፍል አንድ) [በፈቃዱ ዘ ሃይሉ]

(ቺማማንዳ ኒጎዚ አዲቼ እንደጻፈችው)

ኦኮሎማ ከልጅነት ጓደኞቼ አንዱ ነበር። የሰፈሬ ነዋሪ የነበረ ሲሆን ለኔ የታላቅ ወንድሜ ያህል ነበር፤ አንድ ወንድ ልጅ ከወደድኩ የኦኮሎማን አስተያየት እጠይቅ ነበር። ኦኮሎማ ቀልደኛ እና ጎበዝ ሲሆን ጫፉ ሹል የሆነ የእረኛ ቦቲ ጫማ ያደርግ ነበር። ዲሴምበር 2005፣ ደቡብ ናይጄሪያ ውስጥ አውሮፕላን ሲከሰከስ ኦኮሎማ ተቀጠፈ። እስካሁንም ድረስ የሚሰማኝን ስሜት በቃላት ለመግለጽ እቸገራለሁ። ኦኮሎማ አብሬው ልከራከር፣ ልስቅ ልጫወት የምችለው ሰው ነበር። ለመጀመሪያ ግዜ ፌሚኒስት ብሎ የጠራኝ ሰው ነበር።

ያኔ የዐሥራ አራት ዓመት ልጅ ነበርኩ። አንዴ እነሱ ቤት ውስጥ ካነበብናቸው እና በግማሽ ያጣጣምነው ዕውቀት ላይ ተመሥርተን እየተከራከርን ነበር። ክርክሩ ስለምን እንደነበር አሁን አላስታውስም። የማስታውሰው እየተከራከርኩት በገፋሁ ጊዜ ኦኮሎማ አየት አደረገኝና ‘ታውቂያለሽ? ፌሚኒስት ነሽ’ አለኝ።

እያደነቀኝ አልነበረም። ከድምፁ ያስታውቃል። አባባሉ ልክ አንድ ሰው ‘ታወቂያለሽ? የሽብርተኞች ደጋፊ ነሽ’ ሲል ዓይነት ነው።

ፌሚኒስት የሚለው ቃል ምን እንደሆነ ግን አላውቅም ነበር። እንደማላውቅ ደግሞ ኦኮሎማ እንዲያውቅብኝ አልፈለግኩም ነበር። ስለዚህ እንዳልሰማ አለፍኩት። ቤቴ ስገባ መጀመሪያ ያደረግኩት ነገር ቃሉን መዝገበ ቃላት ላይ መፈለግ ነበር።

~~~

ወደፊት የሆነ ዓመታትን እንሻገር።

በ2003 አንድ ከብዙ ነገሮች መካከል ሚስቱን የሚደበድብ እና መጨረሻው የማያምር ወንድ ገጸ ባሕርይ ያለበት ፐርፕል ሂቢስከስ የተሰኘ ልቦለድ አሳተምኩ። ይህንን ልቦለድ ናይጄሪያ ውስጥ እያስተዋወቅኩ እያለሁ፣ አንድ መልካም፣ ጋዜጠኛ ምክር ሊሰጠኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። (እንደምታውቁት ናይጄሪያውያን የተከበረ ምክር ለመስጠት ይፈጥናሉ።)

ሰዎች ልቦለዴን ፌሚኒስት ነው እያሉ እንደሆነ ነገረኝ። ጭንቅላቱን በሐዘን እየወዘወዘ ሲመክረኝ ፌሚኒስቶች ባል በማጣታቸው ምክንያት ደስተኛ ያልሆኑ ሴቶች ስለሆኑ ራሴን ፌሚኒስት ብዬ እንዳልጠራ ነገረኝ።

ወዲያው ራሴን ደስተኛዋ ፌሚኒስት እያልኩ ልጠራ ወሰንኩ።

ከዚያ በኋላ አንዲት ናይጄሪያዊት ምሁር ፌሚኒዝም ባሕላችን እንዳልሆነ ነገረችኝ፣ ፌሚኒዝም አፍሪካዊ እንዳልሆነ እና እኔ ራሴን ፌሚኒስት ያልኩት በምዕራባውያን መጽሐፎች ተፅዕኖ እንደሆነ አስረዳችኝ። (በጣም ነበር የገረመኝ። ምክንያቱም በልጅነቴ ያነበብኳቸው መጽሐፎች ፀረ ፌሚኒስት ነበሩ። ሚልስ ኤንድ ቡን ያሳተማቸውን የፍቅር ታሪክ መጽሐፍት ሁሉ ከ16 ዓመቴ በፊት ሳላነብ አልቀረሁም። እናም ‘ለፌሚኒስትነት የሚመጥኑ’ የሚባሉትን መጽሐፍቶች ባነበብኩ ቁጥር መጨረስ አቅቶኝ እሰላች ነበር።)

ለማንኛውም፣ ፌሚኒዝም አፍሪካዊ አይደለም ስለተባልኩ አሁን ደግሞ ራሴን ደስተኛ አፍሪካዊ ፌሚኒስት ብዬ ለመጥራት ወሰንኩ። ከዚያ አንድ የተከበረ ጓደኛዬ ራሴን ፌሚኒስት ብዬ መጥራቴ ወንዶችን እጠላለሁ ማለቴ እንደሆነ ነገረኝ። ስለዚህ፣ ራሴን ወንዶች የማትጠላ ደስተኛ አፍሪካዊ ፌሚኒስት ብዬ ለመጥራት ወሰንኩ። በዚህ ሒደት አንዴ ወንዶች የማትጠላ፣ ለወንዶች ሳይሆን ለራሷ ሊፕስቲክ እና ባለተረከዝ ጫማ የምትመኝ ደስተኛ አፍሪካዊ ፌሚኒስት ሆኜ ነበር።

እርግጥ ነው ይሄ ሁሉ ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው። ጉዳዩ የሚያሳየው ፌሚኒዝም የሚለው ቃል የተጫነበት ዕዳ ብዛቱን ነው። አሉታዊ ጭነት፦ ወንድ ትጠላላችሁ፣ የጡት ማስያዣ ትጠላላችሁ፣ አፍሪካዊ ባሕል ትጠላላችሁ፣ ሴቶች ሁሌም ኃላፊነት እንዲወስዱ ትፈልጋላችሁ፣ ሜካአፕ አትጠቀሙም፣ የቆዳ ፀጉራችሁን አታነሱም፣ ሁሌም ትቆጣላችሁ፣ ቀልድ አይገባችሁም፣ ዲዮዶራንት አትጠቀሙም።

~~~

አሁን ደግሞ ወደልጅነት ትዝታዬ ይኸውላችሁ።

በደበቡ ምሥራቅ ናይጄሪያ የዩንቨርስቲ ከተማ የሆነችው ንሱካ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለሁ፣ አስተማሪያችን የሴሚስተሩ መጀመሪያ ላይ አንድ ፈተና ፈትናን ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻልነውን የክፍል አለቃ እንደምታደርገን ነገረችን። የክፍል አለቃ መሆን ቀላል ነገር አይደለም። የክፍል አለቆች የሚረብሹትን ተማሪዎች ሥም ይመዘግባሉ። ይሄ ትልቅ ሥልጣን ነው። ከዚህም በላይ አስተማሪያችን የሚረብሹትን ተማሪዎች ለመቆጣጠር ለአለቃ አለንጋ ታስይዛለች። በርግጥ አለቆች መጋረፍ አይፈቀድላቸውም ነበር። ነገር ግን መያዙ በራሱ ለዘጠኝ ዓመቷ ልጅ እኔ አስደሳች ነገር ነበር። የክፍል አለቃ ለመሆን በጣም ጓጓሁ። ፈተናውንም በከፍተኛ ውጤት አለፍኩ።
ነገር ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ አስተማሪያችን የክፍል አለቃ መሆን የሚችለው ወንድ ነው አለች። ይህንን ግልጽ ማድረግ እንደነበረባት ረስታዋለች። አንድ ልጅ ሁለተኛውን ትልቅ ውጤት አምጥቷል እና እሱ የክፍሉ አለቃ እሱ ይሆናል።

የሚገርመው ግን ያ ልጅ፣ ክፍሉን ልምጭ ይዞ የመጠበቅ ምንም ፍላጎት ያልነበረው በጣም ደስ የሚል ኩሩ ልጅ ነበር። እኔ ደግሞ ያንን ለማድረግ በጣም ተመኝቼ ነበር።

ነገር ግን እኔ ሴት ነበርኩ፣ እሱ ደግሞ ወንድ። ስለዚህ እሱ የክፍል አለቃ ሆነ።

ያን ገጠመኝ መቼም አልረሳውም።

አንድን ነገር ደጋግመን ካደረግነው፣ ችግር የሌለበት ይመስላል። ደግመን ደጋግመን ካየነው ትክክል ይመስለናል። ሁሌ ወንዶች ብቻ የክፍል አለቃ ሲደረጉ ካየን፣ የሆነ ግዜ ላይ፣ ሁላችንም፣ ምንም እንኳን ሳናስተውለው ቢሆንም የክፍል አለቃ መሆን ያለበት ወንድ ብቻ ይመስለናል። ወንዶች የኮርፖሬሽኖች ኃላፊዎች ሆነው ደጋግመን ካየን፣ ወንዶች የኮርፖሬሽን ኃላፊዎች መሆናቸው ‘ተፈጥሯዊ’ የሆነ ያክል እንዲሰማን ያደርጋል።

Filed in: Amharic