>

የህወሃት አፓርታይድ አገዛዝ በይፋ ይወገዝ! (ሃራ አብዲ)

የትራይ የበላይነት አለ? የለም? የሚለው ቀልድ መቆም አለበት።  በሚለዉ ጽሁፌ ላይ በቀጣይነት ለራሴ የሰጠሁት የቤት ስራ ;
-…የትግራይ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ (አፓርታይድ ) ለመኖሩ አስረጂ ጭብጦችን ፤
-ለሃያ ሰባት አመታት የዚህን ስርአት ምንነት አጥርተን ለማወቅ ያልቻልንባቸዉን ምክንያቶች፤
-…በአንድ ድምጽ (unanimously) የስርአቱን በትክክል የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ መሆን መቀበል
ያልቻልንበት የሚመስለኝን ሃሳብ፣ ይዤ እቀርባለሁ የሚል ሲሆን፣ እስከዚያዉ …… ሃሳብ
ስታስጨብጡ የነበራችሁ ወገኖቻችን በዚህ ላይ ሃሳባችሁን ስፋት እንድትገልጡ………….. ጥሪ ላስተላልፍ እወዳለሁ» ብዬ ነበር።

ሆኖም ባስተላለፍኩት ጥሪ መሰረት ብዙ ምላሽ አላየሁም። እርግጥ የትግራይ የበላይነት አለ? የለም? የሚለዉ ክርክር የሞተ ይመስለኛል። እየደጋገመ መሞትም ያለበት ጉዳይ ነዉ። በጠበቅሁት መሰረት ግን በሀገራችንና በህዝባችን ላይ በግፍ ስለተጫነው የትግራይ የውስጥ ቅኝ አገዛዝ (አፓርታይድ) በስፋትና በጥልቀት ተጽፎ ለማየት ገና በመጠባበቅ ላይ ነኝ።

ስለዚህ፤ በዛሬዉ መጣጥፌ የቤት ስራዬን ይዤ ባልቀርብም አንዳንድ የማነሳቸዉ ተዛማጅ ሃሳቦች ግን አሉኝ። በየቀኑ ግድያ፤ ሰቆቃና መፈናቀል ያለበት ህዝብ ሰለአለን፣ በተለያዩ ርእሶች ላይ የሚጽፉ ወገኖች ሃሳባቸዉን ሰብስበዉ በዚህ ላይ ያላቸዉን ምልከታ እንዲያካፍሉን መጠበቅ የሚያስፈልግ መስሎ ታየኝ።

ዛሬም፣ ኢትዮጵያዉያን/ዉያት፣ ምሁራንን፣ የፕሬስ ባለሞያዎችን፣ በተለያዩ ሚዲያዎችና ፎረሞች የምትጽፉትን፣ የምታነቡትን፣ ለሀገራችን፣ ለተገፋዉና ኢ-ሰብአዊ ሰቆቃ ለሚፈጸምበት ህዝባችን በብዙ የምትጨነቁና በተለያየ መልኩ የዚህን አፓርታይድ አገዛዝ ዉድቀት ለማፋጠን የምትተጉትን ሁሉ «ብእራችሁ ከምን »ስል ላንቀሳቅሳችሁ እወዳለሁ።

ብዙ የማደንቃችሁና የማከብራችሁ ወገኖቼን በስም ጠቅሼ እሰዉ አይን ላስገባችሁ አልፈለግሁም ነበር። በተለይም ኢትዮጵያ የምትኖሩትን ማለቴ ነዉ። እናንተ ግን ጀግኖች ናችሁ፣ አይን አትፈሩም! ስለዚህ የአምቦዉ ወንድሜ፣(የበላይነቱ በደንብ እንዳለ የገለጽከዉ)፣ ከፍርድ ቤት የምትዘግበዉ ወንድሜ፤ (ስለአፓርታይዱ ከሚጽፉት ጥቂቶች አንዱ አንተነህ) እስኪ ይሀን ነገር አብላልታችሁ አቅርቡት። ህዝባችን ይወቀዉ፣ ግፉን ጸሃይ ይሙቀዉ። እነ ቬሮኒካ፣ እነመስከረም፣ እነ በፍቃዱ ….እነ ያሬድ…..እረ ማንን አንስቼ ማንን ልተዉ?

እንዲህ በመሰለ ትህትና ጆሮአችሁን ከሰጣችሁኝ ዘንዳ ደግሞ ይህንንም አዳምጡኝ።

መቸም ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የተማረዉ ሁሉ የማንን ገፈሬ ሲያበጥር እንደኖረ እግዚአብሄር ይወቅ።
በስንትና ስንት ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን/ዉያት ሞልተዉን እንዴት ነዉ ቢያንስ፣ ቢያንስ በመቶ ሽሆች የሚቆጠሩት ሰለትግራይ አፓርታይድ የማይጽፉት?
– ህዝብ የማያነቁት?
-ለአለም መንግስታት ማስረጃዉን የማያቀርቡት?
-እንደ ደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ በአለም መንግስታት ማእቀብ የማያስጥሉበት?
-ለምንድን ነዉ በዉጭ ባሉ የመገናኛ ብዙሃን ዜና የማይሰሩበት? በርእሰ-አንቀጽ ሽፋን
የማይሰጡት?
-በቃለ- ምልልስ ሁለንተናዉን አብጠልጥለዉ እርቃኑን የማያስቀሩት? ለምንድን ነዉ?
የኛ ምሁራን፣ ህወሃት ሊወድቅ ነዉ፤ ሊወድቅ ነዉ፣ ሲባል በጡሩንባ ተጠራርተዉ (musical chair) መጫወት ብቻ ነዉ፣ የሚችሉት ማለት ነዉ? ሸንጎ….የሽግግር መንግስት…..እንደራደር…..የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር…. ምናምን…..

በዘመነ- ኢንፎርሜሽን የተጻፈዉን ሁሉ አንብቤያለሁ፣ የተነገረዉን ሁሉ አዳምጫለሁ የሚል እንደሌለዉ ሁሉ፣ እኔም እንደዚህ አይነት ድፍረት አይወጣኝም። ተነግረዉ ያላዳመጥኩዋቸዉ፣ ተጽፈዉ ያላነበብኩዋቸዉ፤ ህልቆ- መሳፍርት የላቸዉም። ሰለዚህም፤ በዚህ ርእስ ዙሪያ ሳላያቸዉና ሳልሰማቸዉ ያመለጡኝ እንደሚኖሩ ግልጽ ነዉ። ይሁንና ባለፈዉ የጠቀስኩት የፕሮፌሰር ግርማ ብርሀኑ « A Quiet Case of Ethnic Apartheid in Ethiopia  ‘Internal Colonialism and Uneven Effects of Political, Social, and Economic Development on a Regional Basis’» ከሚለዉ የሪሰርች ስራ በስተቀር ሌላ ወጥ ስራ አላጋጠመኝም። እንዳልምል
ግን፣ በዘ-ሃበሻ ላይ የተጻፈ አንድ ጽሁፍ ላይ መሰል ትንተና በቅርቡ አንብቤ ጮቤ ልረግጥ ትንሽ ነበር የቀረኝ። (እዚህ ላይ የዘ-ሀበሻን ጽሁፍ ምንጭ ባለመጥቀሴ ይቅርታ እጠይቃለሁ)።
ሌሎች የብእር ሰዎች ምን እያሰቡ ይሆን እላለሁ። እንደኔ ፤እንደኔ፤ በሽታችንን ሳናዉቅ መድሃኒት አናገኝም።
-የትርምሳችን መንስኤ፣
– በአንድ ያለመቆማችን ምክንያት፤
-የጎንዮሽ ፍትጊያዉ
የተቃዋሚዎች በህብረት አለመቃወም፣
-የአብዛኛዉ ህዝብ የዳር ተመልካች መሆን፣
-የአንዳንዱ፣ ትግሬ ሳይሆን ህወሃትን መደገፍ
-«ኦሆዴድ ረግጦ ይዉጣ፣ እከሌ ለህዝቡ የቆመ አይደለም….»
የሚለዉ ፤ከዚህም ከዚያም የሚወረወር የሃሳብ ሚሳይል፤ ህወሀት የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር እንዳሸከመን ካለመገንዘብ የመጣ ይመስለኛል። ህዝባችን ባርነት ይጠላል። ጣልያንን መንገድ ሰራልን ብሎ ያልማረዉ ህወሃት መንገድ ሰራልን ብሎ አይምረዉም። ህወሃት ስር ለመስደድ ፣ለአፍታ እድል ፈንታ አያገኝም ነበር።

በዛሬዉ ጽሁፌ እሼቱ ቶኩማን አበጀህ ልለዉ እፈልጋለሁ። «በኢትዮጵያ ነፃ አውጭ እንጂ  መንግሥት አለ?!? (እሸቱ ቶኩማ) »  እሸቱ፣ ስርአቱን በስሙ መጥራት ብቻ ነዉ እንጂ የቀረዉ፣ ነገረ-ስራዉንና አካሄዱን ሁሉ አሳምሮ ገልጦታል። የገለጣቸዉ ነገሮች የህወሃትን ለኢትዮጵያ ህዝብ ባእድ መሆንና የጭካኔዉ አይነትም የአንድ ሀገር ዜጋ ፣ በሌላዉ ወገኑ ላይ ሊያዳርግ ከሚችለዉ በላይ መሆኑን አመላክቶአል። ይህ ማለት ደግሞ፣ ህወሀት በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመጫኑ አንዱ ማረጋገጫ ነዉ።«እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ?» ሲል ጠይቆአል።

እሸቱ ፣ በጽሁፉ በዝርዝር ያቀረባቸዉ ነጥቦች ቆም ብለን እንድናስተዉል ያደርጉናል። ህወሃት ለምን ጠረፍ አካባቢ ያለዉን የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ ለባእድ ይሰጣል? ይህን ያህል ዘመን ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ ስር አድርጎስ ለምን ስሙን እስከዛሬ አልቀየረም? ህወሃት የትግራይ ነጻ አዉጭ ነኝ ሲል ለምን አናምነዉም… እያለ እሸቱ ያስደምመናል። ልክ ነዉ። ህወሃት ኢትዮጵያን በዉስጥ ቅኝ ግዛት ነዉ በመግዛት ላይ ያለዉ። ኢትዮጵያን መግዛት የማይችልበት ጊዜ ሲደርስ የቀድሞ አላማዉን ለማሳካት እስከዛሬ የሚጠራበትን የትግራይ ህዝብ ነጻ አዉጪነቱን እንደያዘ ትግራይን ገንጥሎ ይሄዳል።

ታዲያ እኛ ኢትዮጵያዉያን/ዉያት፣ ምን ነክቶን ነዉ ይህን የአፓርታይድ አገዛዝ በስሙ ጠርተን ፣ከዳር እዳር ተጠራርተን ፣ሆ፣ ብለን ካላያችን ላይ ማራገፍ ያቃተን?

እስኪ እንደሀገር ልጆች፣ እንደ ወንዝ ልጆች በሀቅ እንነጋገር።የህወሃትን የአፓርታይድ ስርአት ለምን በተገቢዉ መጠን አልተወያየንበትም?
-ፈርተን ነዉ? ህወሃት በቅኝ ገዢነቱ ቢታወቅ ህዝብ ይተላለቃል፣ ትግሬዎች ኢላማ ይሆናሉ ብለን ነዉ?
-ኮርተን ነዉ? እነዚህ በችጋር ሲጠበሱ ያደጉ መሰረተ-ድሆች እንዴት አፓርታይድ መሰረቱብን እንላለን ብለን ነዉ?
-ጭንቀት ነዉ? የትግራይ አፓርታይድ መኖር ከተነገረ፣ የትግራይ ሰዎች ግልብጥ ብለዉ ህወሃትን ይወግናሉ ነዉ?
-ጠፍቶን ነዉ? የአንድ ዘር የበላይነትን መሰረት አድርጎ የሚመሰረት የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ
(የአፓርታይድ ስርአት) የሚገለጥባቸዉ ሁኔታዎች በሙሉ በሀገራችን መሬት የነከሱ እዉነታዎች መሆናቸዉ ጠፍቶን ነዉ?
-ለዉጥ አያመጣም ነዉ? የአፓርታይድ ስርአቱ በህዝባችን መካከል በግልጽ መታወቁ ህወሃትን ለማስወገድ በምናደርገዉ ትግል ላይ ለዉጥ አያመጣም ነዉ?
ከምንወያይባቸዉ ጉልህ ርእሶች መካከል እስኪ ፣ የትኛዉ ምክንያት ነዉ፣ የትግራይ አፓርታይድ ነገር ውሾን ያነሳ ዉሾ ይሁን ያስባለዉ? ባለፈዉ ጽሁፌም እንደገለጽኩት፣ ይህን ህዝባችን ሲረዳ ያለ ጥርጥር በፍጥነት የሚቀየሩ ነገሮች ይኖራሉ።የህወሃት አፓርታይድ አገዛዝ በይፋ ይወገዝ።

ነጻነትዋና አንድነትዋ ተጠብቆ፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች

Filed in: Amharic