>
5:33 pm - Monday December 5, 1949

ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል! (አበበ ገላው)

ዘመኑ የሶሻል ሚድያ ዘመን ነው። ይህ ማለት ደግሞ ማንም ሰው መልካሙንም ክፉውንም ሃሳብም ይሁን መረጃ አንዲት ትንሽ ዘመናዊ ስልክ በመጠቀም ብቻ በቅጽበት በአለም ዙሪያ ማሰራጨት ይችላል። በመሆኑም ዛሬ አንዲት ቃል በብዙ መንገድ ተተርጉማ፣ ተተንትና፣ ተቃንታም ይሁን ተዛብታ አለምን እየደጋገመች መዞሯ የተለመደ ክስተት ነው።
በዚህ ነገሮችን ለማቀጣጠልና ለማጦዝ በጣም ቀላል በሆነ ጊዜ የምንጠቀምባቸው ቃላት እኛ ካሰብነው በተቃራኒው ቢተረጎም ብዙም አያስገርምም። በተለይ ደግሞ እንደኛ እንደ ኢትዮጵያውያን ወሳኝ በሆኑ አገራዊ እሴቶች እና ጉዳዮች ሳይቀር እንዳንግባባ ገዢዎቻችን ብዙ ኢንቨስት ያደረጉበት ህዝብ ትንሽ ይበቃዋል።
ሰሞኑን አርበኞች ግንቦት 7 ከደህሚት ጋር በጋራ ባወጣው መግለጫ ዙሪያ ብዙ አስተያቶች ተሰንዝረዋል። እነዚህንም አስተያየቶች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንዱ ወገን ከቅንነት ስህተቱ ሊታረም ይገባዋል የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ ይህን ህዝባዊ ድርጅት ማንቋሸሽና ማጥላላት ላይ ያተኮረ ነው። በሁዋለኛው ረድፍ በዋናነት የተሰለፉት የህወሃት የስሙኒ ሰራዊት አጋፋሪ እና የጦር አበጋዞች ናቸው። የእነሱ አላማ በግልጽ ልዩነትን ማስፋትና ማናቆር ስለሆነ ብዙም ግዜ አጥፈተን ልንተነትነው የሚገባ ጉዳይ አይደለም።
ለማንኛውም በጫጫታው መሃል ሃቁ እንዳይዘነጋ ያስፈልጋል። አርበኞች ግንቦት ፯ ጠላቱን ለይቶ ታግሎ የሚያታግል የህዝብ ድርጅት ነው። ከትግሉ ውስብስብነት አንጻር የገጠመው ፈተና ቀላል እንዳልሆነ ለማንም የተሰወረ ሃቅ አይደለም። ከዚህ አንጻር ድርጅቱ ጠንካራ ጎኑን የበለጠ እያጎለበተ ያሉበትን ክፍተቶች እና ችግሮች እያረመ መዝለቁ ወሳኝ ነው። ዛሬ ትግሉ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ድርጅቱ ያበረከተው ጉልህ አስተዋጾ እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም ግልጽ ነው።
እኔ በበኩሌ ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ዘረኛውን እና ፋሺስታዊውን የህወሃቶች አንባገነናዊ ስርአት የሚፋለሙ ድርቶችም ይሁኑ ቡድኖች መጠናከራቸውንና የጋራችን በሆነው የነጻነት ራእይ ስር በአንድነት ተሰልፈው ሲፋለሙ ማየት ከሚፈልጉ ዜጎች አንዱ ነኝ። ስለዚም በዚህ የፈተና ክረምት ትልቅ ጋራ የሚያህል ጠላን አስቀምጠን መሰረታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እየተወዛገብን ጊዜ ማጥፋት አያዋጣንም። እንኳን ታልቅ ህዝባዊ መሰረትና እራሳቸውን የሰጡ መሪዎች እንዲሁም ቆራጥ አባላት በአለም ዙሪያ ያሉት ትልቅ ድርጅት ይቅርና በፋሺስቶቹ ላይ ጠጠር የሚወረውሩ ግለሰቦች እንኳን እንዲጠፉ ሳይሆን ጠንክረው እንዲወጡ የተቻለንን ያህል ልንደግፋቸው ይገባናል።
ማፍረስ ቀላል ነው፣ መገንባት ግን እጅግ ከባድ ነው። ስለዚህም ትግሉን ከዳር ለማድረስ ጥንካሬን የበለጠ እያጎለበትን መታረም ያለበትን እያረምን መዝለቃችን ለትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል እጅግ ወሳኝ ነው።
ትላንት ከሚመለካታቸው ሁለት የአርበኞች ግንቦት ፯ አመራር አባላት ጋር ገንቢ ውይይት አድርጊያለሁ። ሁለቱም ለምን በአደባባይ ተተቸን አላሉም። ከሁለቱም የተረዳሁት ጉዳይ ክፍተቶችን ገምግሞ በአስቸኳይ ለማረም ቁርጠኝነት መኖሩን ለመረዳት ችያለሁ። ወንድም ነአምንም በግልጽ በጹሁፉ ያስቀጠው እውነታም ይሄንኑ የሚያንጸባርቅ ነው።
ምንም እንኳን በኛ የፖለትካ ባህል ያልተለመደ ቢሆንም አግባብነት ያላቸው ትችቶች ተቀብሎ እርምት ለማድረግ መንቀሳቀስ የበለጠ ለድርጅቱም ይሁን ለደጋፊዎቹ ብርታትን የሚሰጥ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ጠቢባን እንደሚሉት ፖለቲካ 95 ፐርሰት ኮሚውኒኬሽን 5 ፐርሰንቱ ደግሞ ተግባር ነው። ስለዚህም የህዝብ ግንኙነቱን በሰው ሃይልም ይሁን በግብአት የበለጠ ማጠናከር ወሳኝ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በነገራችን ላይ ሃሳብን በስድብ ለመመከት የምትሞክሩ ሁሉ እራሳችሁን ለትዝብት ትዳርጋላችሁ።ለስድብ መደራጀት አያስፈልግም። ለውጥ ለማምጣት ከስድብ የተሻለ ራዕይ ያስፈልጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Filed in: Amharic