>

የህዝባችን ትግል ሰራዊቱ ውስጥ ግለት ፈጥሯል (መሳይ መኮንን)

ጉዳዩ ከሚገባው በላይ መጦዙ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ደጋፊዎችና የፌስቡክ ሰራዊት ሰርግና ምላሽ የሆነላቸውን የሰሞኑን ፍጥጫ እናርግበውና ወደ ዋናው ስቱዲዮ እንመለስ። አንድን ጉዳይ ደጋግሞ ማኘክ ለውጥ አያመጣም። ከዚህ በላይ እንዲሄድ መፍቀድ የለብንም።

ትግል ከባድ ነገር ነው። ውስብስብ ነው። ማናችንም ገጻችንን ከፍተን ስሜታችንን እንደምንገልጸው አይነት ቀላል ነገር አይደለም። ውጣ ውረድ የበዛበት፡አባጣና ጎርባጣ የበረከተበት፡ ጠመዝማዛ መንገድ የሞላበት፡ መውደቅና መነሳት የማይጠፋው፡ ወዳጅ የሚንሸራተትበት፡ ጠላት የሚማረክበት፡ ስህተት የሚሰራበት፡ ስህተትን የሚተራረሙበት፡ ሰፊና ጥልቅ የህይወት መስክ ነው – ትግል። የተጀመረው ፍጻሜ ማግኘት አለበት። ትግሉ ከዳር መድረስ ግድ ይለዋል። ኢትዮጵያ ትጠብቀናለች። ጊዜ የለንም።

አራት ነገሮችን ላንሳ። የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራው መንግስት የኮሚኒኬሽን ቀውስ ውስጥ መግባቱን አምኗል። መንግስት ውስጥ ያሉ አካላትና መዋቅሮች መግባባት እንዳልቻሉ ሰሞኑን የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ በይፋ ገልጸዋል። በክልልና ፌደራል መንግስት መሀል መግባባት የለም። ቋንቋው ተለያይቷል ነው የሚሉን ሰውዬው። ይህ ትልቅ ጉዳይ ነው። አንድ ስርዓት እዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ ከገባ አደገኛ ነው። እርስ በእርሱ የመበላላት እድሉ ሰፊ ነው።

ሰዎቹ ለምን መግባባት አቃታቸው? መልሱ ቀላል ነው። የህዝብ ትግል ውጤት ነው። በስርዓቱ መሀል ሁለት አካላት መኖራቸውን ያመለክታል። የህዝብ ትግል ሙቀቱ ሲጨምር አሰላለፋቸውን ከህዝብ ጋር ያደረጉ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ያሳያል። እነኚህ ወገኖች ቋንቋቸውን ቀይረዋል። መረጃ ሲያቀብሉ አዛብተው ነው። የኮሚኒኬሽን ቀውስ መፍጠር ችለዋል። ይህ ለአንድ ስርዓት ፍጻሜ ሁነኛ ምልክት ነው። ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

ሁለተኛው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር(ትህነግ) በወታደራዊ ሹመት ሰራዊቱን እያንበሸበሸ መሆኑ ነው። ባለፈው ዓርብ ካጠለቀለቀው የጄነራልነት ሹመት በተጨማሪ ለአብዛኛው የሰራዊቱ አባላት በየደረጃቸው ማዕረግ ሊሰጣቸው መሆኑ ተሰምቷል። በዚህኛው ዙር ማዕረግ የማያገኝ የሰራዊቱ ክፍል እንደሌለ ይነገራል። ገንዘብና ስልጣን የሌለው ባዶ ሹመት መሆኑ እርግጥ ነው። ጥያቄው ትህነግ አሁን የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት በማዕረግ ማጥለቅለቅ ለምን ፈለገ የሚለው ነው። መልሱ አጭር ነው። በሰራዊቱ ውስጥ ጫፍ የደረሰው ምሬትና ብሶት ነው። የህዝባችን ትግል ሰራዊቱ ውስጥ ግለት ፈጥሯል። ከላይ በአንድ ብሄር ተወላጆች የበላይነት የተያዘው የሰራዊቱ ክፍል ሲቀር ከመካከለኛው እስከ ታች ያለው ብዙሃኑ የሰራዊቱ አባላት ውስጥ መከፋቱ ከገደብ አልፏል።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራው አገዛዝ በህዝብ ተተፍቷል። በዙሪያ በጥቅም ከተሰባሰቡ ጥቂት አገልጋዮቹ በቀር ከዳር እስከዳር ተቃውሞ ተነስቶበታል። ህልውናው የቆመው በደህንነቱና መከላከያው ነው። መከላከያው ውስጥ የተፈጠረው የሰራዊቱ ምሬትና ብሶት በዚሁ ከቀጠለ ወደ ህዝብ የተነጣጠረው አፈሙዝ ወደ አገዛዙ መዞሩ አይቀርም። ይህ መሆኑ አገዛዙን ከነጥቁር ታሪኩ ከኢትዮጵያ ገጽ ላይ የሚፋቅበትን አጋጣሚ ይፈጠራል።

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የሰራዊቱ ብሶትና ምሬት እንዲዳፈን እየተሯሯጠ ነው። ሰራዊቱ አንድ ላይ ለብዙ ጊዜ እንዳይቆይ(ከቆየ የአመጽ ሴራ ይጎነጉናል ከሚል ፍራቻ) በየቀኑ የመበታተንና የማጓጓዝ ዘመቻ ላይ ተጠምዷል። ከዚህ በተጨማሪ ገንዘብና ስልጣን በሌለው ሹመትና ማዕረግ የሰራዊቱን አፍ ለማዘጋት በሰፊው መንቀሳቀስ ጀምሯል። ሰሞኑን የወታደራዊ ሹመቶች ዜና በሽ ይሆናል። በዘመቻ ማዓረግ ይሰጣል። ከንቱ ድካም ነው። ሰራዊቱ የደረሰበት የምሬት ደረጃ በውሸትና ባዶ ማዕረግ የሚዳፈን አይደለም። የህዝብ ትግል በሰራዊቱ ውስጥ የፈጠረው ግለት የሚበርድ አይሆንም። እናም ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

ሶስተኛው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር የሚመራው አገዛዝ የተደቀነበት የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ነው። ሀገሪቱ ቀጥ ብላ ቆማለች። ወደፊት መሄድ አልተቻለም። የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ብቻውን የትህነግን አገዛዝ ወደ ውድቀት ሊወስደው እንደሚችል ምልክቶች እየታዩ ነው። ከአዲስ አበባ የሚወጡ መረጃዎ እንደሚያመለክቱት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ባንኮችን ጾም እያሳደራቸው ነው። ስራ የለም። ጠዋት በር ይከፈታል። ሲመሽ ይዘጋል። ምንም የለም። አገዛዙ ጭንቀት ሲይዘው የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ነገሮች ፍለጋ እየማሰነ ነው። የአሰሪና አገናኝ አዋጅ ላይ ጥሎ የነበረውን እገዳ ያነሳው ዶላር ፍለጋ ነው። ዕቃ ያለቀረጥ እንዲገባ የፈቀደውም የምንዛሪው እጥረት የፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ ነው። በየሀገራቱ ያሉ ኤምባሲዎች ከእንግዲህ ከአዲስ አበባ የሚላክ ደምወዝ አይኖራቸውም። እዚያው በተለያዩ መንገዶች ዶላር ፈልገው ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ ውስጣዊ ሰርኩላር ማሰራጨቱ ይነገራል። የተበደረውን ገንዘብ የሚክፍለው በማጣት ከአበዳሪዎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል። በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው።

ይህ አንድም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት ዘመቻ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ ላይ እቀባ እንዲያደርጉ የተከፈተው ዘመቻ አንድ ወር ሆኖታል። ውጤት እያሳየ ነው። ከብሄራዊ ባንክ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ዘመቻው ከተከፈተ ወዲህ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ መጠን ቀንሷል። ይህም ስርዓቱን አስደንግጧል። እናም ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

አራተኛው የአሜሪካን መንግስት ሰሞኑን ቀነ ገደብ አስቀምጦ ለትህነግ አገዛዝ ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ ነው። ኤች አር 128 የተሰኘው ረቂቅ ህግ ለኮንግረስ ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ከጫፍ ደርሷል። ረቂቅ ህጉ ከጸደቀ ለትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አገዛዝ ትልቅ አደጋ ይሆናል። በተለይ የአገዛዙ ባለስልጣናት ላይ የሚጣለው ገደብ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ የሚደረግበት ነው። የትህነግ አገዛዝ ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ እንዳይቀርብ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ሎቢስቶችን በመቅጠር የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ገብቷል። በአንጻሩ ኢትዮጵያውያንም ከምንግዜውም በላይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ዘመቻውን አጠናክረው ገፍተውበታል።

ባለፈው ሀሙስ የአሜሪካን መንግስት ለትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አገዛዝ ማስጠንቀቂያ ልኳል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ኢትዮጵያ ገብተው ያለምንም ገደብና ክልከላ በፈለጋቸው ቦታና ጊዜ ምርመራ እንዲያከናውኑ እንዲፈቅድ ፡ ይህንንም እስከ የካቲት 28 ድረስ ምላሽ እንዲሰጥ አሜሪካ አሳስባለች። በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የትህነግ አገዛዝ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ እንደሚቀርብ የኮንግረሱ አብላጫ ወንበር የያዘው የሪፑብሊካን መሪ አስጠንቅቀዋል። ረቂቅ ህጉ ለኮንግረስ ከቀረበ የማለፍ አድሉ ሰፊ እንደሆነ ይነገራል። ያ ከሆነ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር(ትህነግ) አገዛዝ ዶላሩም፡ የፖለቲካ ድጋፉም ይነጥፍበታል። በሂደት ባለስልጣናቱ በግል የመዘዋወር መብታቸው ገደብ ይጣልበታል። ዘርፈው ከሀገር ያሸሹት ሀብትና ንብረታቸው ይታገዳል። ይህ ህዝባችን እያደረገ ላለው ትግል ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እናም ይህ እንዳይቀለበስ ወደ ስራችን እንመለስ።

መሀል ላይ ነን

እኛ ኢትዮጵያውያን መሀል ላይ ነን። መንገድ ላይ። ነጻነትን ፍለጋ ወጥተናል። መድረሻችን ከሀገራችን ነጻነት ነው። መሀል ላይ ብዙ ነገሮች ይገጥማሉ። ወጀብ ይኖራል። ማዕበል አይጠፋውም። እሳት፡ ነጎድጓድ፡ ይገጥማል። መሀል ላይ መከራው ብዙ ነው። ስቃዩ አይጣል ነው።  መሀል ላይ ብናጠፋ አይፈረድብንም። ብንሳሳት ሃጢያት ሆኖ አይቆጠርብንም። መሀል ላይ ባለ አይፈረድም። መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ንጉስ ዳዊትም መሀሉ ላይ አትብላ የተባለውን የካህን እንጀራ በልቷል። መሀል ላይ የሚሆነው አይታወቅም። የሚገጥመንንም እንደዚያው። ለነጻነት መውጣታችን፡ መዳረሻችንም የት እንደሆነ ማወቃችን እንጂ በመሃል መንገድ ላይ የሚሆነውን አናውቅም። ጉዙአችን ይቀጥላል። ወጀቡን አልፈን፡ ማዕበሉን ተሻግረን፡ እሳቱን ዘለን ለመዳረሻችን የኢትዮጵያ ነጻነት እንበቃ ዘንድ ወደ ስራችን እንመለስ።

Filed in: Amharic