>

አራቱ የኦፌኮ አመራሮች ለ2ኛ ጊዜ ተፈረደባቸው (ጌታቸው ሽፈራው)

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት የድርጅቱ አመራሮች በድጋሜ በችሎት መድፈር ተፈረደባቸው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያኖን መዝገብ የተከሰሱትን ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ እና በቀለ ገርባ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባለመነሳታቸው ችሎቱን ደፍረዋል በሚል በአራቱም ላይ የ6 ወር የእስር ቅጣት አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ካልተነሱ ማንነታቸውን መለየት እንደማይቻል በመግለፅ ጠበቆቻቸው መክረው እንዲያስነሷቸው ጠይቀዋል።

ሆኖም ተከሳሾቹ “ባለፈው በመናገራችን ተቀጥተናል” በሚል አንነሳም ማለታቸውን በጠበቆች በኩል ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ተከሳሾቹ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባይነሱም እጃቸውን ያወጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ካልተነሱ የፍርድ ቤቱን ሕግ ስላላከበሩ እርምጃ እንወስዳለነረ ብሏል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን በበኩላቸው በፍርድ ቤት ማንነትን ማረጋገጥ የሚያስፈልገው ክስ ሲነበብ እንደሆነ፣ መዝገቡ ለዛሬ ጥር 28/2010 የተቀጠረው ለክስ ሳይሆን ፍርድ ለመስጠት ስለሆነ ጠበቆቹ ከቆሙ ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም ብለዋል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ባለመቆማቸው ምክንያት የፍርድ ቤቱ ሰዓት በ30 ደቂቃ እንደባከኑና ድርጊቱንም ችሎት መድፈር መሆኑን በመግለፅ ውሳኔውን አስተላልፏል። ተከሳሾቹ ባለፈው ቀጠሮውም በችሎት መድፈር መቀጣታቸውን አስታውሶ፣ ከባለፈው አልተማሩም በሚል የ6 ወር እስር ወስኗል። ጥር 10/2010 ዓም ችሎት ደፍራችኋል በተባሉበት ወቅት በፍርድ ቤት የተናገሩት ተከሳሾቹ ስለዛሬው ውሳኔው የገለፁት ነገር የለም።

በሌላ በኩል 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ፣ 12ኛ ተከሳሽ ተስፋየ ሊበንና 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ ያልቀረቡ ሲሆን ዛሬ በችሎት መድፈር 6 ወር የተፈረደባቸውን አራቱን አመራሮች ጨምሮ በሁሉም ላይ ፍርድ ለመስጠት ለየካቲት 28/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።

Filed in: Amharic