>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8084

ነጋሶ ጊዳዳ የእኔ CNN (ሚጢጢ ዉዳሴ)

ያኔ ( ሰሎሜ ታደሰ የመንግሥት ቃል አቀባይ በነበረችበት ዘመን) የኢሕአዴግ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስቴር በፕሬስ ጉዳይ ላይ አንድ የዉይይት መርሃግብር አዘጋጅቶ በግዮን ሆቴል ስብስባ ጠራን፡፡ ጦማርን ወክዬ ይሁን፣ ያኔ በፀሓፊነት አገለግለዉ የነበረዉን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማኅበርን ( ኢነጋማ) ወክዬ ልሂድ ባላስታዉስም መድረክ ላይ ተናጋሪ ከነበሩት ሰዎች መሐከል አንዱ ነበርኩ፡፡ የትኛዉ ብቃቴ እዚያ ላይ እንደሰቀለኝ የሎስ ይወቅ፡፡
በርካታ ታዋቂም አዋቂም ሰዎች ተሳትፈዉበታል፡፡ መድረክ ላይ ከነበርነዉ መሐከል ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አንዱ ናቸዉ፡፡ዶክተር ነጋሶ በጉባኤዉ ላይ በአደረጉት ንግግር ‹‹ የራስን ዕድል በራስ መወሰን›› የሚለዉን ነገር አንስተዋል፡፡
ይኼ ‹‹ የራስን ዕድል…›› የሚለዉ ነገር ከማይዋጥላቸዉ የኢትዮጵያ ጎምቱ ምሁራን መሐከል አንዱ ( ስም ባልጠቅስ) ሃሳቡን በማናናቅ ቅላፄ፣ ‹‹ ይኼ ‹ራስ › የሚባለዉ ነገር ማነዉ ? ዕድልን መወሰንስ ምንድነዉ? ›› የሚል ኮራ ያለ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
የጥያቄዉ ቀስት በቀጥታ የተነጣጠረዉ ወደ ዶክተር ነጋሶ ስለነበረ መልስ እንዲሰጡ ተጠየቁ፡፡ ነጋሶ፣ ‹‹ራስ››ን ለብቻ፣ ‹‹ዕድል››ን ለብቻ ወደመተንተን አልሄዱም፡፡
‹‹ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ማለት፣ ነጋሶ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነሳ ምን መልበስ እንደሚኖርበት፣ ቁርሱን ምን መብላት እንዳለበት፣ ቁርሱን እየበላ ስለምን ማሰብ እንደሚገባዉ መወሰን ያለበት ራሱ ነጋሶ እንጂ እገሌ ( የጠያቂዉን ስም ጠርተዉ) አይደለም ማለት ነዉ›› አሉ በአጭሩ፡፡ የሌሎቹን አላስታዉስም ፤ እኔ ግን ማጨብጨቤን አልረሳሁም፡፡ለጭብጨባ ባሕላችን ታማኝ መሆኔን በአጋጣሚዉ ለመግለፅ ያህል ነዉ፡፡
ስለዶክተር ነጋሶ በአደባባይ እንዳነሳ ያደረገኝ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን መኪና ሊሸልመቸዉ ወይም እንደሸለማቸዉ የተዘነነዉ ነገር ነዉ፡፡
ዶክተር ነጋሶ ከኦነግ ጀምሮ እስከ አንድነት ድረስ የነበራቸዉን የፖለቲካ ስብዕናም ሆነ የሕይወት ታሪካቸዉን የመተረክ ፍላጎትም ሆነ አቅም እንደሌለኝ ካራማዬ ይነግረኛል፡፡እናም አልሞክረዉም፡፡ ለማወቅ የሚፈልግ ሰዉ ካለ፣ ‹‹ ዳንዲ- የነጋሶ መንገድ›› የተሰኘዉን መፅሐፍ እንዲያነብ በትዕቢትና በጀብዱ እመክራለሁ፡፡
ነጋሶን በቅርብ ከአወኳቸዉ በኋላ ከተገነዘብኩዋቸዉ በርካታ መልካም ስብዕናቸዉ ዉስጥ ሳልጠቅስ የማላልፈዉ መኖሩን ለመናገር የማንም ፈቃድ አያስፈልገኝም ባይ ነኝ፡፡
ቅን፣ የዋህና ሰዉ አክባሪነታቸዉን አደንቃለሁ፡፡ በጎበዝ አንባቢነታቸዉ አሁንም ድረስ እቀናለሁ፡፡ በ1997 ምርጫ ወቅት ጠዋት ጠዋት ስልክ እየደወሉ ‹‹ እንትናን አንብበሃል ?የሄራልድን ርዕስአንቀፅ አይተሃል ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ ላይ ( የኢሕአዲግ ልሳን) ስለተቃዋሚዎች የተፃፈዉን አስተያየት እንዴት አየኸዉ…? እስቲ ለእነመረራም ንገራቸዉ…›› እያሉ ማለዳ ስለአነበቡት እየነገሩኝ ስንቴ በሀፍረት አሸማቀዉኛል፡፡ ምክንያቱም፤ ለወጉ እኔ ‹‹ጋዜጠኛ›› ተብዬዉ ነበርኳ ማለዳ ተነስቼ ሀገሩን ጋዜጣ መገረብ የነበረብኝ፡፡ እናም በነጋሶ አጋባሽ አንባቢነት እቀና ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ያኔ በአሜሪካ ላይ የደረሰዉ የሴፕቴምበር 11 መዓት ሲነሳ በአእምሮዬ የሚመጡት ነጋሶ ናቸዉ፡፡ዜናዉን መጀመሪያ የሰማሁት ከእሳቸዉ ነዉ፡፡ የእኔ CNN ነበሩ፡፡
በአካል የተገናኘነዉ ከፕሬዚዳንትነት ለቀዉ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በተሰጣቸዉ ቤት ዉስጥ እያሉ ነዉ፡፡ ቤቱ ግድግዳዉ በሁሉም ጥግ ላይ ተሰነጣጥቆ ዝናብ እያስገባ ብዙ ነገር አበላሽቶባቸዉ እንደነበር አይቻለሁ፡፡ ዘግበንበታልም፡፡
በኋላ ሳር ቤት አካባቢ ሌላ ቤት ተሰጣቸዉና እዚያ ሲገቡ በሰፊዉ ለመገናኘት በቃን፡፡ አሁን መጥቀስ በማያስፈልጉን የተለያዩ በጎ ምክንያቶች ከሌሎች የማከብራቸዉ ሰዎች ጋር ጭምር ቤታቸዉ ዉስጥ ተገናኝተን አያሌ ቁምነገር አዉግተናል፡፡ ስንቱን አዉጥተን አዉርደን፤ ስንቱን ቀድደን ሰፍተን…‹‹ሆድ ይፍጀዉ›› አለ ጥላሁን?
የቤተመንግሥት አስተዳደር የመደበላቸዉ አራት የጥበቃ ሠራተኞች፣ ሁለት መኪኖች፣ የሰለጠኑ የቤት ሰራተኞች፣ ሹፌሮች እንደነበሩዋቸዉ አይቻለሁ፡፡ተጋሩዎቹ ዘቦች አርቦሼ ሆነዉ ነበር፡፡ ሁሉም ስለሚመሳሰሉ በስም አላዉቃቸዉም፡፡
በግላቸዉ በምርጫ ዉስጥ ለመሳተፍ ሲወስኑ፣ ‹‹ሕግ ጥሰሀል፤ ቀይ መሥመር አልፈሃል›› ተባሉና ጥበቃዉም ተነስቶ መኪኖቹም ተወስደዉባቸዉ ሕፃኗን ተሊሌን ግርክ ስኩል ለማድረስ መኪና ችግር በሆነበት ጊዜ አብሬያቸዉ እንደነበርኩ መናገር ዉሸትም ጉራም አይመስለኝም፡፡ ለክብራቸዉ በማትመጥን በዚያች አሮጌ መኪናችን ባለቤታቸዉ ወይዘሮ ረጊና ከጀርመን ስትመጣ ቦሌ ድረስ ሄዶ መቀበል የግድ የነበረበትን ጊዜ አስታዉሳለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ በወቅቱ የሚከራይ መርሰዴስ መኪና የነበረዉ ወዳጄ ነብዩ የእኔ መኪና እንደማትመጥናቸዉ አዉቆ ያለአንዳች ክፍያ በራሱ መኪና ሲረዳቸዉ እንደነበር አለመናገር የነብዩን ዉለታ መርሳት ይሆንብኛል፡፡ ዶክተር ነጋሶም ዉለታዉን ይዘነጉታል የሚል ድፍረት አይኖረኝም፡፡ ጥሩ አክባሪያቸዉ የነበረ ቀንደኛ የቡና ደጋፊ ነዉ ነቢዩ ማለት፡፡ምስጋናዬን እንካማ…
አዘዉትረን ከእርሳቸዉ ጋር የምንገናኝ አንዳንድ ጓዶች ገንዘብ አዋጥተን መኪና ልንገዛላቸዉ ከተነጋገርን በኋላ በሰበብ በአስባቡ ተዝረክርከን ሳይሳካልን እንደቀረ ነጋሶ እስከዛሬም የሚያዉቁት አይመስለኝም፡፡ እንኳንም ቀረባቸዉ፡፡
በኋላ እኒያ የተባረኩ ባለኮሌጅ ወዳጃቸዉ መኪና በቋሚነት አዋሱዋቸዉና የትራንስፖርት ችግራቸዉን ለማቃለል እንደተቻለ አዉቃለሁ፡፡ ለእኒህ ሰዉም የእኔ ምስጋና ሲያንሳቸዉ ነዉ፡፡
ነጋሶ የሀብት ድሀ ናቸዉ፡፡ የወዳጆች ድሀ ግን አልነበሩም፡፡ ለምርጫ ሲወዳደሩ ፖስተር ያዘጋጁላቸዉንና ያሳተሙላቸዉን ወዳጆቻቸዉን የሚረሱዋቸዉ አይመስለኝም፡፡ ባለታሪኩ በሕይወት እያለ ስለእርሱ መመስከር ዉሸትን ካለመናገር ያቅባል፡፡
ነጋሶ ይክፋም ይልማም፣ ‹‹ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት›› የሚል ትልቅ ስም ነበራቸዉ፡፡ አብዛኞቹ የፓርቲ ጓዶቻቸዉ መሬትን ሲቀራመቱና ሲያቀራምቱ እርሳቸዉ ስንዝር መሬት አልወሰዱም፡፡ የራሳቸዉ የሆነ ቤት አልሰሩም፡፡ የጥቅም ሰዉ እንዳልነበሩም ጠላትም ሆነ ወዳጆቻቸዉ እንደሚመሰክሩ አምናለሁ፡፡ ለግል ጥቅም ያልቆሙ፣ ለሚያምኑበት ነገር ፊት ለፊት ከመጋፈጥ የማይመለሱ ሰዉ በመሆናቸዉ ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡
በኦነግ ዉስጥ አብረዋቸዉ ስለነበሩትም ሆነ አሁንም ስላሉት ታጋዮች አንድም ቀን ክፉ ሲናገሩ ሰምቼ አላዉቅም፡፡ በትግል መንገድ ምርጫ በመለያየታቸዉ የተነሳ ስብዕናቸዉን ሲወቅሱ፣ መስዋዕትነታቸዉን ሲያሳንሱ ጨርሶ አትሰሙም፡፡ አክብሮት ከመስጠት ዉጪ፡፡
በወቅቱ ዳባ( Dhaabaa) ደበሌን የመሰሉ ዘርጣጭ አፈቅዶች ከነበሩበት የኦሕዴድ ባለሥልጣናት ዉስጥ ለሟቹ ዓለማየሁ አቶምሳ ልዩ አክብሮት እንዳላቸዉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምቼ አዉቃለሁ፡፡ ዳባ ደበሌ የእርሳቸዉን ከኢሕአዴግ መላቀቅ አስመልክቶ ፓርላማ ስብስባ ላይ( ይመስለኛል) በተናገረዉ ነገር አፍሮ አንገቱን የሚደፋበት ቀን ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወደደም፤ ጠላም፡፡
ከዶክተር ነጋሶና ከሌሎች የማከብራቸዉ ሰዎች ጋር ለሀገራችንና ለሕዝብ ይጠቅማሉ ብለን ያፈለቅናቸዉ ሐሳቦች፣ የወጠናቸዉ ነገሮች፣ የጀመርናቸዉ ተግባራዊ እርምጃዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከግብ ባይደርሱም በእነዚያ በጎ ጥረቶቻችን ዉስጥ ዶክተር ነጋሶ ኮከብ እንደነበሩ በዚህ አጋጣሚ የመናገር የኅሊና ግዴታ እንዳለብኝ አምናለሁ ፡፡
በአንዱ ወይም በሌላ ምክንያት ስለእርሳቸዉ የተለየ አተያይ ያላቸዉን ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች እምነት ወይም አቋም እያከበርኩ በኦቦ ለማ መገርሳ የሚመራዉ ኦሕዴድ፣ ዶክተር ነጋሶ ከመለስ ሰዎች ጋር ባለመስማማታቸዉና ከግል ጥቅም ይልቅ የሕዝብን ጥቅም በማስቀደማቸዉ ለደረሰባቸዉ ጉዳት ካሳ ሊሆን የሚችል እርምጃ በመዉሰዱ በተለይ በዚህ ጉዳይ ደስ ካላቸዉ ሰዎች መሀከል አንዱ መሆኔን ለመናገር አላፍርም፡፡ ይህን በጎ ሐሳብ ያመነጩትንም እያመሰገን፣ሌሎች ባለዉለታዎችንም የማስታወስ የሚያስችል ልቦና እንዲሰጠን እንደምንፀልይ ስናገር፣ በአሁኑ ሰዓት ያለወንጀላቸዉ በእስር እየማቀቁ የሚገኙ ወገኖቼን በማሰብ ጭምር ነዉ፡፡
Cheers Abbaa Ibsaa!

Filed in: Amharic