>
5:18 pm - Saturday June 15, 8796

ጥቂት ስለ አቶ ለማ መገርሳና እሚመሩት ኦህዴድ (ወንድወሰን ተክሉ)

የሶሻል ሚዲያ ንቁ ተሳታፊና የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበትና በጥልቀት ከሚያዩት ውስጥ አንዱ የሆነው ዳዊት ሰለሞን «እንደ ኦህዴድ አስገድዶን እንድናደንቀው ያደረገን ድርጅት አይቼ አላውቅም» ካለ በሃላ ይቅጥልና «ቅንጅት አለ ልትሉኝ ትችላላችሁ ግን ቅንጅትን እኛ አፈቀርነው፤አደንቅነውና ይበልጥ ህዝባዊ ዓላማዎችን የሚያራምድ አድርገን ተጽእኖ ፈጠርንበት እንጂ እንደ ኦህዴድ የሚጠላና የሚወገዝ ሆኖ ግን እያደረገ ባላቸው ተግባሮቹ በግድ እንድናደቀው ያደረገን አይደለም» በማለት በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራውን ኦህዴድ አለማድነቅን አዳጋች አድርጎታል የሚል እድምታን ያስተላልፉል፡፡ብዙዎች በሃሳቡ ይስማማሉ፡፡

የሰሞኑ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ግምገማና ውጤቱ ደግሞ የአቶ ለማ መገርሳንና ጋደኞቻቸውን እርምጃና ውሳኔን ያዩ ሰዎች «አሁንስ ከአምላክ በታች የኢትዮጵያ ተስፋ ኦህዴድ አይደለምን» በማለት እንዲናገሩ አድርጓቸዋል፡፡

ሌላው አክቲቪስት ሳምሶን ባራኪ የተባለ ደግሞ«እንግዲህ ኦህዴድም በፈጣሪው ላይ አምጾ እራሱን ነጻ በማውጣት ላይ ነው» በሚል አርእስት የድርጅቱን ስርነቀል እርምጃ ያመላከተ ምስክርነትን ቸራል፡፡

ባለሙያዎቹ የኢሳት ተንታኞች እነ ኤርሚያስ፣ሲሳይና መሳይ አነጋገር ደግሞ በተለየ ሁኔታ የድርጅቱን ወሳኝ የተባሉ እርምጃዎችን እየነቀሱ በማውጣት ከላይ የቀረቡትን አስተያየቶችን መሰረት ያላቸው አመለካከቶች እንደሆኑ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲመስክሩ የታዩ ሆኖ አግኝቼያቸዋለሁ፡፡

እናም እያፈተለከ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያንም ታላቅ ተስፋ ያሰነቀ እየሆነ የመጣ ድርጅት ሆኗል፡፡

ግን ይህ ድርጅት፤ እጅግ የተናቀ፤እጅግ የተወገዘ እርባነቢስና የህወሃት አገልጋይ ባሪያ ሆኖ በተለይም የወገኖቹን የኦሮሞ ህዝብ እጅግ ያስጠቃ ድርጅት የነበረ በሚደንቅ ሁኔታ ዛሬ ይህን መሰል አስተያየትና አመለካከት በነጻው መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማግኘት መቻሉን የማንክደው እውነታ በመሆኑ በአግራሞት እያየነው ያለ እርምጃና አድናቆት ሆኗል፡፡

«ሃላኞች ፊተኞች፤ፊተኞች ይሆናሉ »እንዳለው የእግዚአብሔር ቃል በእርግጥም ማንም በነበረበት ቆሞም ይሁን ወድቆ አይቀርምና «ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የቤቱ መሰረተ ማእዘን ሆነ» እንዳለው በአዲስ ኪዳን የተናቀው ኦህዴድ ምስጋና ለእነ አቶ ለማ መገርሳና ጓደኞቹ ወደ ሀገራዊ ማእዘንነት እያመራ ይሆን ስል በግሌም በርቀት ለመመልከት መጣሬ አልቀረም፡፡

ማን ያውቃል፤ሆኖ እናይ ይሆናል፤አሊያም ቢያንስ የህወሃትን የእብሪት የበላይነትን በህወሃት በተፈጠረው ኦህዴድ ሲንኮታኮት እናይ ይሆናል ስልም አስባለሁ፡፡

እሳቤዬም፡ምኞት ሳይሆን ድርጅቱ እያደረጋቸው ባሉት ወሳኝ የሚባሉ እርምጃዎች ላይ ተመርኩዤ ነው፡፡

እስቲ ከእነዚህ ወሳኝ እርምጃዎች ጥቂቱን ላስፍር፤

**ለመጀመሪያ ግዜ ድርጅቱ በድርጅታዊ፣ክልላዊ፣ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ላይ ውሳኔ ማስተላለፉ

** ለመጀመሪያ ግዜ ድርጅቱ በኦሮሞ ጉዳይ ላይ ከቄሮ ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በጋራ ተባብሮ እንደሚሰራ መግለጹ

** ድርጅቱ ለመጀመሪያ ግዜ የኢኮኖሚውን ሁኔታ ፖሊሲውን ጥቂት ሃይሎች ስልጣንን መከታ በማድረግ ከድንበር ድንበር እየዘለሉ የተቆጣጠሩበት ብልሹ አካሄድ ነው ብሎ በአቋም ደረጃ ይፋ ማድረጉና በርካታ በህወሃት፤አዜብ መስፍን የተያዙ ንግድ ተቋሞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ

**በድርጅቱ ውስጥ በህወሃት ፈረስነታቸው የታውቁትን እነ ሙክታር፣አስቴርና ሶፊያን አህመድን ጨምሮ አስር አመራሮችን ከማእከላዊ ማባረር መቻሉ (በእርግጥ አሁንም የቀሩና የታለፉ አሉ ወርቅነህ ገበየሁ፣አባዱላ ገመዳ፣ኩማ ደመቅሳና ግርማ ብሩ የተባሉ የህወሃት አገልጋይ ፈረሶች ቢቀሩም በአንጻራዊነት ግን እነሱን አቅመቢስ አድርጎ የተገኘበትን የበላይነት አከማችቶ ይዟል)

**በሀገር ቤት አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነትን እያቀነቀነ የነበረውና በቅርቡ በህወሃቱ ዘራይ አስግዶም እርምጃ ተወስዶበት መዳከም የጀመረውን ኦቢኤንን በነጻነት ያገለግል ዘንድ ጥበቃ እንዲደረግለት ማለቱ

**የፌዴራሉን ህግና ትእዛዝ ለምሳሌ ቄሮውን አደገኛ ብሎ የመፈረጅና ምርመራ የማካሂድን ውሳኔን እና የፌዴራል ፖሊስና መከላከያው በኦሮሚያ ቁጥጥር እንዲያደርግ የታዘዘውን ውሳኔ ያልተቀበለና የሻረ ማስተላለፉና ወዘተ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን መብትና ክብር የማስጠበቁ ውሳኔም ሌላው የህወሃትን ኢፍትሃዊ ውሳኔና በቀልተኝነትን ያከሰመበት እፍምጃው አድርጌ አይቼዋለሁ፡፡

ዶ/ር ነጋሶ የህወሃት ፕሬዚዳንት የነበሩ ሳለ ግን መስመር ለቀው ከህዝብ ወግነዋል በማለት እንደ አሮጌ ቁና አሸቀንጥሮ በመጣል የተዘባበተባቸው ሰለባ ነበሩ፡ ዛሬ መብትና ክብራቸው በኦህዴድ ተመልሶላቸዋል፡፡

በእስረኞች ጉዳይ ላይ በይበልጥ እየሰሩ እንደሆነ አስቀምጠዋል፡ ግን እንደነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ላይ በፌዴራል የተያዘ ከመሆኑ አንጻር አፋጣኝ እርምጃ ሊወስዱ አይቻላቸውም፤ለግዜው፡፡

እናም በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቀው ህወሃት ግን በስልጣኑ ተጠቅሞ ከድንበር ድንበር እየዘለለ ኢኮኖሚውን ያግበሰበሰበት ዘራፊውን ኤፈርት በኦሮሚያ ላይ ያለውን መጠነ ሰፊ ብዝበዛና ዘረፋ ተነጠቀ ማለት የድርጅቱን አቅም አከርካሪ የሚያወላልቅ ተግባር እንደሚፈጥር መግለጽ ይቻላል፡፡

እናም እነዚህን ሰዎች በአድናቆት ከማየት የሚያግድ አካሄድ ሳይሆን እያደረጉ ያሉት በጥርጣሬ ያለንን አስገድዶ እንድናደቅ ያደረገ አካሄድ ላይ እንዳሉ ሁኔታዎች ይገልጻሉ፡፡

እናም፤ ኦህዴድ የሀገር ተስፋ ይሆን ? በአቶ ለማ መገርሳና ጓደኞቻቸው አመራር ቢያንስ ፍላጎትና ዓላማው እንዳላቸው እያየን ሲሆን ተግባሩን እንጠብቃለን ስል ሃሳቤን እደመድማለሁ፡፡

Filed in: Amharic