>
5:28 pm - Monday October 9, 7651

ሰሞነኛ የሕወሐት/ኢሕአዴግ የኢትዮጵያዊነት ትርክት ግርግርና ስሌቱ!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

ሕወሐት/ኢህአዴግ ባልተለመደ ሁኔታ በ26 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያዊነት ቀን አክብሯል፡፡
በሕወሐት/ኢሕአዴግ ህገ መንግስት በኢትዮጵያ የስልጣን ባለቤት ዜጎች ሳይሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው፡፡ ይህ
አስተሳሰብ ከመሰረቱ ሳይለወጥ በድንገት የኢትዮጵያዊነትን ቀን ለማክበር እንዴት ወሰኑ? የሚለውን ጥያቄ ከህወሀት/
ኢህአዴግ ድርጅታዊ ባህሪ አንፃር ሲታይ ግራ የሚያጋባና ትኩረት የሚሻ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ለመጣው የተፈጥሮ ሞትና መከፋፈል ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች የህልውና
ማስጠበቂያና ከውስጥ ሽኩቻው አሸንፎ ለመውጣት ኢትዮጵያዊነትን እየተንጠላጠሉበት ይመስላል፡፡
1. ሕወሐት ከትግራይ ውጭ ባሉ ፖለቲከኞች ዘንድ በመጠላቱና ኦህዴድና ብአዴን በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተነሳው
ህዝባዊ ንቅናቄ ተገደው ወደ ህዝብ የመቅረብ አዝማሚያ በማሳየታቸውና ከሎሌነት ለማምለጥ እየዳዳቸው ስለሆነ
ሕወሐት የኢትዮጵያዊነት ትርክትን ከፍ አድርጎ በመያዝና ወደ ህዝብ በመቅረብ የበለጠ ተቀባይነት በማግኘት የበላይነትን
ለመውሰድ ይመስላል፡፡
2. ኦህዴድ ከዚህ ቀደም ሲከተለው ከነበረው የፖለቲካ ሀሳብና እምነት መቼና አንዴት እንደተለወጠ /መለወጡም
ሳይረጋገጥ/ ሳይታወቅ አሁን የመጡት አመራሮቹም በድርጅቱ ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ሲሰሩ የቆዩ ቢሆኑም በግንባሩ
ውስጥ ያለውን ሽኩቻ በተለይም የሕወሐትን የበላይነት ለመቀነስና የኦሮሞን ሕዝብ የስልጣን ባለቤትነት ያለገደብ
ለማስፈን እንዲረዳቸው የኦሕዴድና የአብዛኛው የኦሮሞን ፖለቲካ በሌላው ኢትዮጵያዊ እይታ የተገንጣይነትና የመነጠል
ጥርጣሬ በማለዘብ ሲቻልም የሕወሐትን ተፅዕኖ ለማሳሳትና የኦህዴድን ተቀባይነት ለማጉላት ሲሉ በስልት ደረጃ
ኢትዮጵያዊነትን ባልተለመደ ሁኔታ ከፍ አድርገው መያዝ የጀመረ ይመስላል፡፡
3. ደኢሕዴንም የግንባሩ አባል ድርጅቶች ኦህዴድና ብአዴን በተፈጠረው ህዝባዊ ንቅናቄ ተገደው ወደ ህዝብ ለመቅረብ
በመሞከራቸውና በአብዛኛው ተቃዋሚ ሃይሎችም በአማራና ኦሮሞ መካከል ህብረት ለመፍጠር የፖለቲካ ግፊትና ቅስቀሳ
በመኖሩ ምክንያት ከግንባሩም ሆነ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመገለል መንፈስ ስለተሰማው ይህንን ለመከላከልና
ወደ ህዝብ ለመግባት ሲል ኢትዮጵያዊነት ላይ ለመንጠልጠል ሲጣጣር ይስተዋላል፡፡
4. ብአዴን እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለቱ በትምክህት ሲተች ከኖረ በኋላ ባላሰበው ሰዓት የአማራ
ማንነት ፖለቲካን የሚደግፉና የሚሰብኩ ሰዎች በመፈጠራቸው ከሚመራው ህዝብ እንደሚነጠል ሲያውቅና በግንባሩ
ውስጥ ያለው ተፅዕኖ እንደሚደበዝዝ ሲገነዘብ የፖለቲካ ይሁንታ ለማግኘትና በግንባሩ ውስጥ ያለውን ተፅዕኖ
ለመጨመር በሁለት ወገን ተሰንጎም ቢሆን ኢትዮጵያዊነትን እንደ ስልት ለመቀበል ተገዷል፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሕወሐት/ኢሕአዴግ በአጠቃላይና የግንባሩ አባላት በተናጥል በተደቀነባቸው የተፈጥሮ
ሞትን የሚያፋጥን የውስጥ ሽኩቻ ለመዳን ሲሉ ምንም ዓይነት የአስተሳሰብ ሽግሽግና የፕሮግራም ለውጥ ሳያደርጉ
ለጊዚያዊ የድርጅት ፖለቲካ ትርፍ ሲሉ በእምነት ሳይሆን በስልት ብቻ ኢትዮጵያዊነት ላይ ተንጠልጥለው እየተውተረተሩ
ይገኛሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሕወሐት/ኢሕአዴግ በህዝብ ማዕበልና በተፈጥሮ ሞት ግብዓተ መሬቱ ሲጠናቀቅ በእምነት
ሳይሆን ለድርጅት ጥቅም ሲሉ በይስሙላ የያዙት ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከፈለግን በአገዛዙ ጊዚያዊ
የአስመሳይነት ፕሮፓጋንዳ ሳንዘናጋ የአገዛዙ መሰረታዊ እምነትና የኢትዮጵያዊነት ጠንቅ የሆነውን ጎሰኝነት አምርረን
በመታገል ኢትዮጵያዊነትን አጥብቀን መያዝ ያለብን ይመሰለኛል፡፡
ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደማይገኝ ሁሉ በጎሰኝነት ተቧድኖ እርስ በእርሱ የሚሻኮት ስብስብ ኢዮትጵያዊነትን
ሊያጠናክር አይችልም፡፡

Filed in: Amharic