>

ቀላል መንገድ እያለ ጠመዝማዛውን ለምን እንመርጣለን? (ደረጀ ገረፋ ቱሉ)

የኦህዲድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በግልፅ በሀገር ውስጥ ላሉትም ሆነ ከሀገር ውጪ ላሉት የተደራጁም ይሁን ያልተደራጁ ወገኖች የአብረን እንስራ ጥር አቅርቧል።
ኦህዲድ በመግለጫው የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቅ ጨምሮ ሌሎች የኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ የወሰናቸው ውሳኔዎች ሳይሸራረፉ ስራ ላይ እንዲውሉ እንደሚታገል ግልፅ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ ትላንት ማታ በ OBNቀርበው የኦህዲድ ምክትል ሊቀመንበር እንደገለፁት የአሁኑ የኦህዲድ አመራር የኦሮሞ ህዝብ ትግል ውጤት እንደሆነ እና የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ደግሞ ከማንም በላይ ኦህዲድ የታገለለት እንደሆነ ግልፅ አድርገዋል።እንዲሁም የእስረኞች መፈታት ጉዳይ በኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ደረጃ እንደተወሰነ እና ይህ ውሳኔ ይቀለበሳል ብለው እንደማያምኑ በማከል እንደዚያ ዓይነት አዝማሚያ ካለ ድርጅታቸው እንደሚታገል አስረድተዋል።
እነዚህን ነጥቦች በማያያዝ አሁን የOFC ሊቀመንበሩን ጨምሮ የድርጅቱ ወጣቶች ሊግ በኦህዲድ እና በህዝቡ ትግል ከእስር ተፈተው በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ብዙ ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ አቀባበል እያረገላቸው ነው።ሰሞኑንም ሌሎች ተጨማሪ እስረኞች ይፈታሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኦህዲድ በቀረበው ግልፅ የአብረን እንስራ ጥር መሰረት ዶር መራራ በእስረኞቹ አለመፈታት ጉዳይ ኦህዲድ በቂ ጥረት አላደረገም ብለው ካሰቡ በአንድ የስልክ ጥር አቶ ለማን ወይም ዶር አቢይን ስጋታቸውን ልገልፁላቸው እና ከዚህ በላይ ጥረት እንዲያደርጉ ግፍት ማድረግ እንደሚችሉ በጣም እርግጠኛ ነኝ።ምክንያቱም አብሮ መስራት ለዚህ ካልሆነ ምን ያደርጋል?በዚሁ አጋጣሚም OFC የኦህዲድ አመራሮችን የአብረን እንስራ ጥር መፈተኛ እድል ያገኛሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ዶር መራራ እና ሌሎች የ OFC መሪዎች ኦህዲድ እስረኞቹን ለማስፈታት እያደረገ ያለው ጥረት በቂ አይደለም ብለው ከመኑ እና ኦህዲድ ከዚህ በላይ እንድንቀሳቀስ ጫና ማሳረፍ ብፈልጉ በአንድ ቀን የሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ጥያቄ ቢያቀርቡ ያለ ምንም ቅድማ ሁኔታ ሰላማዊ ሰልፉ እንደሚፈቀድላቸው እና ህጋዊ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በጣም እርግጠኛ ነኝ።ስለዚህ አሁን በህቡዕ የገበያ እቀባ እና የስራ ማቆም አድማ የጠሩ ወገኖች ይህ መንገድ እንዲሞከር አድርገዋል?
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስረኞች መፈታት በኦህዲድ በኩል የተዘነጋ ነገር አይደለም።ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ኦህዲድ በግልፅ በኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ደረጃ አቋም ይዞ ተከረክሯል።ተሳክቶለትም ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቷል።ይህንንም ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በስብስባው ላይ በግልፅ በአመራሩ በኩል ተገልፆላቸዋል።ከዚህ በተጨማሪ ማዕከላዊ ኮሚቴው በአቋም መግለጫው የኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ (የእስረኞች መፈታትን ጨምሮ) ሳይሸራረፍ በስራ ላይ እንድውል ጥር አድርጓል።
የእስረኞች መፈታትን በተመለከተ ምንም እንኳን በተፈለገው ፍጥነት ባይሆንም መፍታቱ ቀጥሏል።ሰሞኑን እንኳን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ እንደገለጸው 746 እስረኞች ሊፈቱ ነው።ከነዚህ መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና እና አንዷለም አራጌ እንዳሉበትም ተገልፃል።በእርግጥ አሁን እንደተገለፀው በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሳ ውዝግብም አለ።ሆኖም ግን ይህ ውዝግብ ተፈቶ እስክንድር እና አንዷለም እንደሚፈቱ አሁንም ተስፋው አለኝ ።ነገር ግን ይህ ውዝግብ ሊፈተ የሚችለው በሌላ ውዝግብ እና ግርግር ሳይሆን በንግግር እና በዲፕሎማስ ነው።
ወደ እነ በቀለ ገርባ ጉዳይ ስንመለስ ኦህዲድ የ OFCአመራርን ከእስር መፈታት ከመጀመሪያው ጀምሮ በልተለመደ መልኩ በግልፅ ያረመደው አቋሙ ነው።ይህንን አቋሙን በኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ላይም በድብቅ በመድገም የሌሎች ኢህአዲግ እህት ድርጅቶች ድጋፍም ታክሎበት አጀንዳው ፍሬ አፍርቶ የ OFC አመራርን ከማስፈታት በላይ በመግዘፍ ሁሉንም እስረኞች በመፍታት ማዕከላዊ እስከ መዝጋት እና የፍትህ ስርዓቱን እስከማሻሻል ድረስ ዘልቋል።ስለዚህ የነበቀለ ገርባ በመጀሪያው ዙር ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር መውጣት ምንም ጥርጥር አልነበረውም።ሆኖም ግን እነ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት ስቀርቡ የኦህዲድ ከፈተኛ አመራርን ጭምር ያስደነገጠ እና ያበሳጫ ነገር ተከሰተ።እነ በቀለ ገርባ ላይ ፍርድቤቱ የዲስፕልን ቅጣት ጣለ።ስለዚህ ነገሮች ሌላ መልክ ያዙ።የነበቀለ ጉዳይ እንደተባለው ከነ ዶር መረራ ጋር ክስ በማቋረጥ ብቻ ልያልቅ እንደማይችል ተወቀ።ነገሮች በተራ እልህ ይሁን በተጠና መልኩ ተወሳሰበ ።የኦህዲድ አመራሮች ግን ምን አገባን ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም።ነገሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ጭምር እንደተነጋገሩበት መረጃዎች ያሳያሉ።ይህንን የኦህዲድ አመራሮችን ጥረት እነ ዶር መራራም ያውቃሉ ቢዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ነገር ግን አሁንም በዲስፕልን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ቅጣት ጣለ።በእርግጥ ይህ ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ አስደንጋጭ ባይሆንም አስገራሚ ነበር።የማያስደነግጠው ችግሩ ከመጀመሪያው ጋር በተመሳሳይ መልኩ መፍትሄ የሚያገኝ ነገር ስለሆነ ነው።የሚያስገርመው ደግሞ እልህ መርፌ ያስውጣል የሚባለው በተከበረው ፍርድ ቤት ደጃፍም መደገሙ ነው።
ረጅሙን ነገር ለማሳጠር የነበቀለ ገርባና የሌሎች እስረኞች ጉዳይ አሁንም እየተሰራበት እንደሆነ ግልፅ ነው።ግን ደግሞ መላቅጡ በወጣው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እስረኛን ማስለቀቅ ምዕራብ ሀገር ቁጭ ብሎ Facebook ላይ ፅሁፍ እንደመልቀቅ ቀላል አይደለም።ስራ ይፈልጋል።መረጋጋት እና የተለያዩ ፍላጎቶችን ማስታመም ይጠይቃል።
በዚህ ሁሉ ጥረት መሃል የሶስት ቀን የገበያ እቀባ እና የስራ ማቆም አድማ መጥራት ምን ለመጨመር ነው? እስረኞቹን ለማስፈታት ወይስ ነገሮችን አውሳስቦ ሌላ እስረኛ ለመጨመር?
ከላይ እንደገለፅኩት የ OFC አመራሮች ኦህዲድ እስረኞቹን ለማስፈታት ያደረገው ጥረት በቂ አይደለም ብለው ካመኑ የኦህዲድ አመራሮችን በስልክ ወይም በክብር በአካል ተገናኝተው ማነጋገር እና ግፊት ማድረግ እየቻሉ፥በዚህም ካልተሳካ መግለጫ በመስጠት በአንድ ቀን ውስጥ የክልሉን መንግስት በማሳወቅ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራት እየቻሉ በህቡዕ የገበያ እቀባ እና የስራ ማቆም አድማ መጥራት ምን ማለት ነው? እስረኞቹ እንዲፈቱ ግፍት ለማሳደር ነው ወይስ እስረኞቹን ለማስፈታት ጥረት እያደረጉ ያሉትን የኦህዲድ አመራሮች ጫና ውስጥ በመክተት እስረኞች የማስለቀቅ ጥረታቸውን ተስፋ ቆርጠው እንዲያቆሙ ለማስደረግ ነው?
ለመሆኑ ወጣቶች ይህንን የተጠራውን ማዕቀብ ስራ ላይ ለማዋል ስንቀሳቀሱ ግጭት ውስጥ ብገቡ ምን እናገኛለን? እንደተለመደው የክልሉ መንግስት ፀጥታ አርፎ እንኳን ቢቀመጥ ሌሎች አካላት ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ በደንብ ተገምግሟል? እንደያው አያድርገው እና አንዳንድ ወገኖች የገበያ እቀባውን ሰይቃበሉ ቀርተው ብንቀሳቀሱ እና ወጣቶች በንብረት ላይ አደጋ ብያስከትሉ ፤ከዚያም ሌላ ነገር ብከተል ትክክል ነው?
እዚህ ላይ የሆነ ነገር ስለሚከተል ሰው መብቱን አይጠቅ እያልኩ አይደለም።ነገር ግን በአሁኑ ሁኔታ ምንም ሳይከተል( ምንም የንብረት ውድመትም ሆነ የሰው ጉዳት ሳይከተል ) ከዚህ በተሻለ መልኩ መጠየቅ እየቻልን ለምን ውስብስቡን መንገድ እንመርጣለን?
በመጨረሻም በኦህዲድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት የኦህዲድ አመራሮች እና የ OFC አመራሮች በሚያግባባቸው ነገሮች ላይ አብሮ ለመስራት መነጋገር ወይ ጀምረዋል አሊያም በቅርቡ እንደሚጀምሩ መረጃዎች ያሳያሉ።እንዳገኘሁት መረጃ ከሆነ ግን እንቅስቃሴዎች በእርግጠኝነት ተጀምረዋል።
ስለዚህ የኛ በህቡዕ የአድማ ጥር ማቅረብ በዚህ የትብብር መንፈስ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል?
በአጭሩ በቀላሉ የተሻለ ነገር ማድረግ እየቻልን ለምን እናጦዘዋለን?

Filed in: Amharic