>
5:21 pm - Tuesday July 20, 9430

የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርና የወያኔ ድርድር በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተቃጣ ሴራ!

ከታማኝ ምንጮች እንደተረዳነው በወያኔና በኦብነግ መካከል ሲካሄድ የቆየው ውይይት በመጠናቀቅ ላይ ነው:: በናይሮቢ ተጀምሮ በዱበይ ከተማ ሲካሔድ ቆይቶ አሁን እንደገና ወደ ናይሮቢ ተመልሶ ፍፃሜ ላይ መድረሱን ምንጮቻችን ገልፀዋል:: ይህ ሤራ ወያኔ ኢትዮጵያን ረግጦ  ገዝቶ ለመኖር ካልቻለ ኢትዮጵያን ሽብር  ውስጥ  ከቶ ትግራይን ለመገንጠልና የትግራይን ሪፑብሊክን ለማቋቋም ያለውን ግልፅ አቋም በተግባር እየተረጎመ መሆኑን ያሳያል::

የኦብነግ አላማ ከስር መሰረቱና እስካሁን ድረስ  ኦጋዴንን ለመገንጠል መሆኑን በብዙ ጥናቶች ተጠቁሟል:: በቅርቡም በሻለቃ ዳዊት ተፅፎ በድህረ ገፆች ላይ የተለጠፈውን ጥናት ይህንኑ  ጠቋሚ ነው::

የኦብነግ አላማ ከወያኔ አላማ ጋር ተመሳሳይነት አለው:: ኦብነግ ኢትዮጵያን አዳክሞ : ኦጋዴንን ከኦሮሞ ከአማራ  እና ከሌሎችም ብሔረሰቦች ነፃ አድርጎ በተዳከመችና ሽብር ላይ በምትኖር ኢትዮጵያ ላይ ነፃነቱን ለማወጅ ነው :: ይህ ሊሆን የሚችለው ወይ ከወያኔ ጋር በመተባበር ፤ አለያም  ደግሞ በኢትዮጵያ  ሕዝብ ትግል የወያኔ የጦር ሀይል ተዝረክርኮና ተዳክሞ የኦጋዴንን ተገንጣይ ሀይል ለመቋቋም  አቅም የማይኖረው ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው:: ኦብነግ በዚህ ከሕዝብ ጀርባ ከሕወሓት የጦር አዛዦች ጋር የሚደረግ ድርድር ላይ መገኘቱ ፤ ከወያኔ ጋር መተባበር ቀላሉና ፍላጎቱን ለማሳካት አቋራጭ  እድል አድርጎት ይሆናል::

ዛሬ የአማራና የኦሮሞ መተባበር ወያኔን ከባድ ሥጋት ላይ ጥሎታል:: ወያኔ የኦሮሞንና የአማራን መተባበር ሲከላከልና   በመሀላቸው ነዋሪና ዘላቂ ልዮነቶችና ግጭቶች እንዲኖር ያላደረገው ነገር አለመኖሩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል:: የሁለቱ ሕዝቦች መተባበር የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት እንዲሁም የወያኔን የበላይነት የሚደመስስ መሆኑን ስለተረዱት ብዙ ሤራዎች ሸርበው: ብዙ ግድያዎች ፈፅመው : ለብዙ ሕዝብ መፈናቀልና መሰደድ ምክንያት ከሆኑ በሗላ ዛሬ ማጠፊያው አጥሯቸው እራሳቸው ባዘጋጁት ማነቆ ውስጥ ገብተዋል::

ኦሮሞና አማራው ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተኑ ሀይሎችን ሁሉ ለመዋጋትና ለመታገል ዝግጁ መሆኑን አገር አቀፍ በሆነ ንቅናቄው እያሳየ ይገኛል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነቱ ላይ ያለውን የማይናወጽ አቋም ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ  እያስተጋባ ነው ::

ይህ ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደኃላ የሚመልሰው ምንም ሀይል አለመኖሩን ወያኔ ስለተረዳ የሕዝቡን ድምፅ እድምጦና ተረድቶ የሽግግር መንግስት አቋቁሞ ሁኔታዎችን ከማረጋጋት ይልቅ ወደ ተፀነሰበት ትግራይን የመገንጠል አላማ እየተጓዘ መሆኑ በመሬት ላይ የሚታዩ እርምጃዎቹ ይጠቁማሉ::

የወያኔ አላማ የኦብነግን ሰራዊት በመጠቀም በኦሮሞ: በአማራውና በደቡብ ህዝቦች ላይ በመዝመት በዚህ ትርምስ ውስጥ የኦጋዴንና የትግራይን መገንጠል ዕውን ለማድረግ ነው:: ( ታላቁ ሴራ በሚል ርዕስ ወያኔ ኢትዮጵያ ሊገባ ሲል የተፃፈውን ማንበብ ይጠቅማል)

ይህ የወያኔና የኦብነግ ሰራዊት አንድነት መፍጠር ኢትዮጵያን ወዳልታሰበ ፍፁም አደገኛ ወደሆነ ሌላ ትርምስ ውስጥ ሊከታት እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊረዳው ይገባል::

ኦህዴድ እና ብአዴን እንደ ድርጅት እስከዛሬ የወሰዳችሁትና እየወሰዳችሁት ያለው አወንታዊ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው: በሰከነ ልቦና ይህንን ሴራ መርምራችሁ በየድርጅቶቻችሁ ሕልውናና በምትወክሉት ህዝብ ላይ የተቃጣውን ዘመቻ በትብብርና በአንድነት ለመቋቋም በአጣዳፊ መዘጋጀት ሁኔታው ግድ ይላል::

ለኢትዮጵያ አንድነት የቆማችሁ ሁሉ ዛሬ ዘር ፤ ሐይማኖት ፤ የፓለቲካና     የቋንቋ ልዩነት ፤ ሳይለያያችሁ ይህንን አደገኛ ሃገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ የተጀመረውን ትግል ማጠናከር አለባችሁ::

ይህ ለጥቂቶች የማይተው እውነተኛ  አገር አድን  ዘመቻ ነው::

በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የምታምኑ ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ፤ የሀይማኖት ኣባቶች ፤ በተሰማራችሁበት ዘርፍ ተቃውሞአችሁን አሰሙ ::

ለኢትዮጲያ አንድነት የቆማችሁ የሶሻል ሚዲያ የሬዲዮ : የጋዜጣ : የቴሌቭዥንና የድህረ ገፅ ሚዲያዎች ሁሉ ያላችሁን መድረክ ወገን ሳትለዩ ለዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ውይይት አውሉት::

ይንንም ኢሳትን ኦኤምኤን: ገበታ ሚድያ ሕብር ሬድዮ የአማርኛና የኦሮሚኛ የቴሌቭዥንና ሬድዮ ፤ ጣቢያዎችን ያጠቃልላል::

በዚህ አጋጣሚ የሃገራችንና የሕዝባችን ሕልውና  የከፋ አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት ፤ ሁሉም በየመስኩ ሁኔታውን እየተከታተለ በአንድ የኢትዮጵያዊነት ድምጽ ትግሉን ያስተባብር :: የምንዘላለፍበት ፤ የምንሰዳደብበት እና የምንወቃቀስበት ጊዜ አይደለም:: በታሪክ እንደታየው ታላቅ ፈተና ሲመጣ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ ነው::

ዶ/ር ዲማ ነገዎ
ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው
ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ

Filed in: Amharic