>
5:13 pm - Thursday April 19, 3590

ለዓላማችን ፣ ለባንዲራችን አብረን መስዋዕትነት ከፍለናል ስለዚህ ይቅርታ ባለመጠየቃቸው ደስ ብሎኛል (የአበበ ቀስቶ እናት)

~ አንደበተ ርቱዑ ፖለቲከኛ አቶ አንዱዓለም አራጌና አንጋፋው እና አይበገሬው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ፣ የቅኔ ማኅሌቱ መሪጌታ ብርሃኑ ተክለ ያሬድና የጽናትና የቆራጥነት ጥግ የተባለው አበበ ቀስቶ ፣ ከዚህ በፊት ባልሠራው ወንጀል ለልጁ ሲል ይቅርታ ጠይቆ ዐማራ በመሆኑ ብቻ ይቅርታ የተነፈገው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ፣ በፌስቡክ ላይ የህዝቡን የመብት ጥያቄ ደግፈህ ጽፈሃል በሚል ተልካሻ ምክንያት ለእስር የተዳረገውን ወጣቱ ፖለቲከኛ ዮናታን ተድፋዬንና እነ አህመዲን ጀበል የሚገኙበት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ጨምሮ 746 የኅሊና እስረኞች በነገው ዕለት እንደሚለቀቁ ማምሻውን ከወደ አዲስ አበባ ተሰምቷል ።

~ የመንግሥቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እሊህ የህሊና እስረኞች እንደሚፈቱ በራሱ የዜና አውታሮች እና በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ካስለፈፈ በኋላ በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባትና በተለይም የህወሓት ደጋፊዎች እንዴት ተደርጎ ይፈታሉ ? ለምንስ በዚህ ወቅት ይፈታሉ ? እንዲያውም በሥራ አስፈፃሚው ስብሰባ ወቅት ያልተነሳ ጉዳይ ነው የሚል ጉትጎታ በመጀመራቸው ምክንያት መንግሥት ሃሳቡን ቀይሮ ተጠርጣሪዎቹን #የግንቦት_ሰባት አባላት ነን ብላችሁ ፈርሙልኝና ነው የምለቃችሁ ፤ ያለበለዚያ አትወጧትም እንዳላቸው ይታወቃል ።

የኅሊና እስረኞቹ ግን ” ንክች አናደርጋትም ፣ አንፈርማትምም ” መጀመሪያስ እኛ መች ፍቱን አልናችሁ ። ከፈታችሁ መፍታት ነው ። ያለበለዚያ ንኩት ብለው በአቋማቸው መጽናታቸው ተነግሯል ። በተለይ የአበበ ቀስቶ እናት በትናንትናው ዕለት ለአሜሪካ ድምጽ የሰጡት ቃለመጠይቅ አንጀት አርስ እንደነበር በሁሉም ኢትዮጵያዊ አድናቆት ተችሮታል ። የአበበ ቀስቶ እናት እንዲህ ነበር ያሉት፦

” መንግሥት የካቲት 1 እፈታለኹ ብሎ ለመላው ዓለም ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጭምር ተናግሮ በ2 እነሱን ተጠያቂ አድርጎ ግንቦት 7 ነኝ በሉ ብሎ ቃሉን ማጠፉ ያሳፍረኛል።

~አንፈርምም ባሉት #ተደስቻለኹ ።#ጀግኖች ናቸው። ይቅርታ የሚፈርመው ሃሰት ነገር ያደረገ ከሆነ ነው።

~ እኛም መስዋዕትነት ከፍለናል። 6 ዓመት ከ 6 ወር እስር ቤት በመመላለስ።

#ለዓላማችን ፣ #ለባንዲራችን መስዋዕትነት ከፍለናል። ስለዚህ ይቅርታ ባለመጠየቃቸው ደስ ብሎኛል።

#ጀግና_ያለው_በኢትዮጵያ_ቃሊቲ_ላይ_ነው። #ቅሊንጦ ነው። #ዝዋይ ነው።

~ልጄ ቢሞት አላዝንም።እውነትን ይዞ ነው። ለሀገር መታገል ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የመጣ ነው ። አዲስ ነገር አይደለም።” ነበር ያሉት የፖለቲከኛው አበበ ቀስቶ እናት ።

~ የእኚህን እናት ወኔ ስሰማ እኔ ጥፍሬ ውስጥ መደበቅ ነበር የቀረኝ ። ጀግና የጀግና እናት እኮ ታስታውቃለች ።

የነገውን ዐይተን ደግሞ ለተነገ ወዲያ እንጠይቃለን ።

~ በተለይ ለዋልድባዎቹ አባቶች ለእነዚያ መነኮሳት ለእነ አባ ገብረ ኢየሱስ ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ድምጹን ከፍ አድርጎ ለማሰማት ይዘጋጅ ። እነ አቡነ ማትያስ እንደሁ ጉዳያቸው አይደለም ። ምክንያቱም ታሳሪዎቹ መነኮሳት ነገዳቸው ከዐማራ ስላልሆነ ግድ አይሰጣቸውም ። ክፉ የዘር በሽታ አምጥተውብን መከራ ያበሉናል ። መነኮሳቱ ገዳም አይፍረስብን ዋልድባ አይታረስብን ባሉ ነው ተይዘው ፍዳቸውን የሚበሉት። በጨለማ ቤትም የሚማቅቁት ። እናም የተዋሕዶ ልጆች እንዘጋጅ ። በኅብረት ድምጻችን ለማሰማት እንዘጋጅ ። በእነዚህ አባቶች ጉዳይ እስላም ክርስቲያን ሳንል በአንድነት ልንጮኽ ይገባል ።

የነገ ሰው ይበለን ። ብቻ ነገ ደግሞ ሌላ ጣጣ አምጥተው አንፈታቸውም ብለው እንዳያሳቅቁን ። መቼም እነሱ እንደሆነ መንገድ ካልተዘጋ ፣ እ የጎማ ጭስ ካልሸተታቸው ፣ የሰውም ደም ፈሶ ካላዩ የሚሰሙ አይነት ሰዎች አይደሉም ።

እባካችሁ እናንት ኢህአዴጎች እነ እስክንድርንም ሀተታ ፣ ገተታ ሳታበዙ ፍቷቸው ። እነ በቀለ ገርባን ለመፍታት ጋሽ እሸቱ እንዳለው ” ወላ የተሃድሶ ስልጠና የለ፣ ወላ ችሎት መድፈር ዝባዝንኬ የለ፣ ወላ የይቅርታ ቦርድ ስብሰባ የለ ፣ ወላ ኦነግ ነኝ ብለህ ፈርም የለ ፤ #እዛው_ውስን_እዛው_ፍትት ። ቄሮ ነዋ!!!!! አቦ ቄሮ አንጀቴን አራስከው ” ። ወይ ቄሮ ።

Filed in: Amharic