በድሮ ጊዜ አንድ በትልቅ በትንሹ ዱላ መምዘዝና ያገኘውን ሁሉ መቀጥቀጥ የሚቀናው ሞገደኛ ሰው ነበረ፡፡
ታዲያ ይሄ ሰው በአንድ ወቅት በአለቆቹ ክፉኛ ተበሳጭቶ ቤቱ ሲገባ ለፆም መያዥያ የገዛትን ቅንጣቢ ስጋ ያስቀመጠበት ቦታ ላይ ያጣት ይመስለውና በጣም ይናደዳል፡፡
ንዴቱ ከቁጥጥረ ውጪ ሲሆንበት ግዜ ስጋዬን ቅርጥፍ አርጎ በመብላት ፆም መያዥያ ያሳጣኝ ይሄ ከይሲ ድመት ነው በሚል በርና መስኮቱን ጥርቅም አርጎ በመዝጋት ያሳደገውን ምስኪን ድመት መቀጥቀጥ ይጀምራል፡፡
ያልጠበቀው ድንገተኛ መዓት የወረደበት ምስኪን ድመት ጌታው እንደማይራራለት በማወቁ ማምለጫ ፍለጋ ከጥግ እስከጥግ ቢራወጥም ጭላንጭል የምታሳይ ቀዳዳ እንኳን ያጣል፡፡
ሞገደኛው ሰውዬም ዱላውን ገታ አርጎ ለድመቱ ፋታ ከመስጠት ይልቅ አንድ ምት ባሳረፈ ቁጥር እልሁና ንዴቱ እየጨመረ ድመቱን ክፉኛ ይቀጠቅጠዋል፡፡
በመጨሻም ምስኪኑ ድመት ዱላው ሲበረታበትና ማምለጫ ቀዳዳ ሲያጣ ግዜ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንፈስ ጥፍሮቹን አሹሎ ሞገደኛው ሰው አንገት ላይ በመጠምጠሙ ጌታውን ይዞት ይወድቃል፡፡
ከአፍታ ቆይታ በኋላ የሞገደኛው ሰውዬ ባለቤት ቅንጣቢዋን አብቃቅታ የሰራችውን ጥብስና ቀይ ወጥ በመያዝ በሩን ከፍታ ስትገባ በሏ አንገት ላይ ተጠምጥሞ የነበረው ድመት እግሬ አውጪኝ ብሎ እየሮጠ ይወጣል፡፡
ሚስቲቱ ያየችውን ማመን አልቻለችም፡፡ የፆም መያዥያ ምግቡን ጥላ በመሮጥ ባሏ ደረት ላይ ብትጠመጠምም ሞገደኛው ሰው ግን በህይወት የለም፡፡ ይቺን አለም እስከመጨረሻው ተሰናብቶአት ሄዷል፡፡
ብልህ ሰው በዚህ ወቅት የግብዙን ሰው የሞኝ መንገድ በመከተል ዱላውን ማበርታት ሳይሆን በጥበብና በማስተዋል የማሪያም መንገድ ነው መፈለግ ያለበት ነው የሚመስለኝ