>

አገራችን ዛሬ የሚያስፈልጋት ፍቱን መድሀኒት እንጂ ማስታገሻ አይደለም (ዳንኤል ክብረት)

መንግሥት መረራ ጉዲናን፣ እስክንድር ነጋን፣ አንዱዓለም አራጌን፣ በቀለ ገርባንና ሌሎችንም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታቱ አንድ ርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ቢያንስ ያንዣበበውን የሥጋት ደመና ይገፈዋል፡፡ የሀገሪቱንም ዜና ከ‹ታሠሩ› ወደ ‹ተፈቱ› ይቀይረዋል፡፡ የተስፋ ብልጭታም በሕዝቡ ላይ ይጭራል፡፡ ከታሠሩት ጋር አብሮ ለታሠረውም ወገን ትልቅ እፎይታ ነው፡፡ አብሮ ግን ሁለት ነገሮች ተያይዘውና ቀጥለው መምጣት አለባቸው፡፡
1. መፈታት ያለባቸውን ወገኖች ጨርሶ መፍታት፡– የክስ ዐንቀጻቸው ምንም ይበል ምን በሕዝቡ ዘንድ በፖለቲካዊ ሐሳባቸውና ሥራቸው የታሠሩ መሆናቸው የሚታመንባቸው ብዙ ዜጎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የሚታወቁ በመሆናቸው በየማኅበራዊ ሚዲያው ስማቸው ይነሣል፤ ሌሎቹ ደግሞ የሚጮኽላቸውም ሆነ የሚሰለፍላቸው የሌላቸው ናቸው፡፡ መንግሥት ሁለቱንም በመፍታቱ ያተርፋል እንጂ አይከስርም፡፡ አሁን እንደምናየው በሕዝቡ ላይ ሥጋት አንዣቧል፡፡ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንኳን ሳይቀር ፍርሐት እየነገሠ መሆኑን በቀላሉ ለማየት ይቻላል፡፡ መንገድ ሊዘጋ ነው፣ ነዳጅ ሊጠፋ ነው፣ እህል ሊወደድ ነው፣ ችግር ሊፈጠር ነው፣ የሚለው ወሬ ጉዳቱ ከኢኮኖሚው በላይ ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ ሦስት ጊዜ ማሰብ እየጀመሩ ነው፡፡ እነዚህን ውጥረቶች ለማርገብ አንዱ መፍትሔ የታሠረውን የሕዝቡን ስሜት መፍታት ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ርምጃ አሁን በተጀመረው መንገድ ሌሎችንም መፍታት ነው፡፡
ለምሳሌ የዋልድባ መነኮሳትን እንመልከት፡፡ የዋልድባን ጉዳይ ሙስሊም ከክርስቲያኑ ያውቀዋል፡፡ የተመሠረተባቸው ክስ ምንም ይሁን ምንም ከገዳሙ መሬትና ከስኳር ፋብሪካው ጋር የተያያዘው ጉዳይ ግን በሕዝቡ ልብ ውስጥ ቁርጥ ያለ መልስ ሳያገኝ እንደተንጠለጠለ ነው፡፡ እነዚህን አባቶች በየጊዜው ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት በማመላለስ፣ ልብሳችሁን አውልቁ አታውልቁ በመነታረክ፣ እየሰማናቸው ያሉትን አሳዛኝ ድርጊቶች በእነርሱ ላይ በማከናወን መንግሥት ፖለቲካዊም፣ኢኮኖሚያዊም፣ ሃይማኖታዊም ትርፍ አያገኝም፡፡ ጉዳያቸው የ35ሺ አድባራት፣ የ400ሺ ካህናት፣ የ1100 ገዳማት ጉዳይ ሆኗል፡፡ በየሰንበት ትምህርት ቤቱ የሚያገለግሉ የ15 ሚሊዮን ወጣቶች ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከዚያም አልፎ የመላ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህች ሀገር ጉዞ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የማይነኩት የማኅበረሰብ ክፍል የለም፡፡ 98 በመቶ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት ዋና ጉዳያችን ነው ማለታቸውን ጥናቶቹ እየነገሩን ነውና፡፡ ፍቱ፤ እነዚህን አባቶች ፍቱ፤ የሚጮህላቸው ቤተ ክህነት ባይኖራቸውም ፍቱ፣ ለሀገሪቱ ደኅንነት ስትሉ ፍቱ፤ የአቡነ ዘበሰማያት ጦር ሲወጋ እንጂ ሲወረወር እንደማይታይ በቅርቡ ከዋልድባ ጋር በተያያዘው ታሪካችን አይተናልና ፍቱ፤ ምናልባትም ይህ ሁሉ ድብልቅልቅ የእነርሱ ኀዘን ውጤት ይሆናልና ፍቱ፤
2. ቀጥሎስ? ቀጣይ የፖለቲካ ሥራዎችን ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም፣ ማንንም በማያገል፣ ያለፉ ችግሮችን በሚፈታ፣ ሌሎች ችግሮችን በማያስከትልና ተአማኒና ግልጽ በሆነ መንገድ ማከናወን ነው ከባዱ ሥራ፡፡ እያሠሩ መፍታት ለችግሩ ማስታገሻ እንጂ መፍትሔ አይሆንም፡፡ የሕዝቡ እንቅስቃሴ አሁን ባለው መንገድ ከቀጠለም ወደ አንድ፣ ሁሉን አስማሚና አሳታፊ ወደሚሆን ግብ መድረሱ ያጠራጥራል፡፡ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ለሁሉም የማይጠቅም ነገር ከመከሠቱ በፊት መሥራት ያለብንን ነገር መሥራት ያለብን አሁን ነው፡፡ ‹ማንም ሊሠራባት የማይችል ሌሊት ትመጣለች› እንደተባለው እንዳይሆን፡፡ እንደ ሠፈር ልጅ ብሽሽቅ፣ እንደ ጎረምሳ ትንቅንቅ፣ እንደ እንደ ጅል እየሠሩ ማፍረስ፣ እንደ እብድ ያለ ውጤት መገሥገሥ አያዋጣም፡፡ የናዳው ምሳሌ እየተተገበረ ነው፡፡ ናዳው እየወረደ ነው፡፡ ወሳኙ ከናዳው ለማምለጥ መሮጥ አይደለም፡፡ የሚሮጠው ሰው ናዳውን በሚቀድም ፍጥነት ካልሮጠ መሮጡ ብቻዉን አያድነውም፡፡ ናዳው ይደርስበታልና፡፡ የሚያዋጣው ከናዳው ፍጥነት በፈጠነ ፍጥነት ለመሮጥ መቻል ነው፡፡
ከማስታገሻው ወደ መፈወሻው እንሂድ፡፡ ሀገሪቱ ታማለች፡፡ የሚያስፈልጋት ፍቱን መድኃኒት እንጂ ማስታገሻ (pain killer) አይደለም፡፡ ነገሩ ካለቀ በኋላ መድኃኒቱን ብናመጣው አይጠቅመንም፡፡
አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ
እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ
ይሆናል ነገሩ፡፡
Filed in: Amharic