>
5:09 pm - Sunday March 3, 4735

"ከጠቅላይ ሚንስትሩ በላይ ያሉ አጠቃላይ ሚኒስትሮች  ሥልጣን ይልቀቁ" (አባይነህ ካሴ)

እንዲህ ዓይነት ቁልፍ ስልጣን የያዘ ሰው ስልጣን ለቅቆ ከፌስ ቡክ ፌዝና ተረብ ውጭ አንድም ስሜት የሚሰጠው ሰው  በእውነትም ሐገራችን ትልቅ ችግር ውስጥ እንዳለች የሚያሳየን ነው፡፡ 
ድሮም ቢኾን ጠቅላይ ሚንስትሩ የአደባባይ (Ceremonial) እንጅ እውነተኛ ባለ ሥልጣን አልነበሩም፡፡ እርሳቸው የሚለቁት ሥልጣን ቢኖር መጠሪያውን ብቻ ነው፡፡ አማናዊ ጠቅላይ ሚንስትሮች ሌሎች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ብቻ ሳይኾኑ አጠቃላይ ኾነው ሀገርን የሚያንከላውሱ እነርሱ ከጀርባ አሉ፡፡ መውረድ ያለባቸው እነርሱ እንጅ ኃይለ ማርያም ደሳለኝማ ራሳቸው ከእስር እንደተፈቱ ይወቁት፡፡ ቀድሞ ያልነበረን ሥልጣን ለቀቅሁ ማለት እንደምን ይቻላል?
ለሀገር የሚበጀው መፍትሔ ከተፈለገ አሁንም አያያዙ ጉልቻ በመለዋወጥ ወጡን ለማጣፈጥ ከመድከም ከፍ ሊል ይገባዋል፡፡ ሰው ባለባት አገር ሰው አልባ መኾን አይገባም፡፡ ቅንነት ካለ ዐዋቂዎች በኢትዮጵያ ምድርም ኾነ በአጥናፈ ምድር ከተበተኑት ወገኖቻችን መካከል ሞልተውናል፡፡ ዕውቀት ያሰከናቸው፣ መማር ዐይን የኾናቸው፣ የሀገር ፍቅር ልብ የኾናቸው ብዙ የብዙ ብዙ አሉን፡፡ እነርሱን ይዞ መምከር ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ሜዳ ውስጥ የአንድ ቡድን ተጫዋቾች ሁሉም ግራኝ ከኾኑ ለውጤት አይበቁም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ቁመና ያመጣው ግራ ተጫዋቾች ብቻ የተሰለፉበት ቡድን ሥልጣን ላይ መቆየቱ ነው፡፡
ከቤተ እምነቱ እስከ ቤተ መንግሥቱ ግራኞች ናቸው፡፡ ከፓርላማው እስከ ፍርድ ቤቱ በአንድ ዓይነት ፋብሪካ የተሠሩ ሰዎች ብቻቸውን ይዘውታል፡፡ ከሥራ አስፈጻሚው እስከ ተራ አስከባሪው የአንድ እግር ተጫዋቾች ይራኮቱበታል፡፡ ሀገር ቀኝ ያልበቀለባት እስክትባል ወላድም ለቀኝ የመከነች እስክትመስል ድረስ!
ልዩነት ጌጥ ሳይኾን መቆረጥ የኾነባት ሀገር እስክትፈጠር ተደርሷል፡፡ 

የቀኝ እግር ተጫዋቾች አደገኛ ጠላቶች ተብለው ሲፈረጁ ኖረዋል፡፡ ተፈጥሮ ሲያስኮንን ከርሟል፡፡ የቀኝም የግራም ባለ ተስጥኦዎች ቁጭ ብለው አንድ ቡድን የሚመሠርቱባት ሠዓት ይህች ናት፡፡ እግዚአብሔር ልቡና እንዲሰጠን በራችን ክፍት ከኾነ ያለፈውን በደል የምንረሳበት አዲስ ልብ ይሰጠናል፡፡ አዲሱን ወይን በአዲስ አቁማዳ እንጅ በአሮጌ አቁማዳ ለማብላላት አንሞክር፡፡ አሮጌው አቁማዳ የማይችለው አዲሱ ወይን አፍለኛ ነው፡፡ ስለዚህም አሮጌውን ሰው እናውልቅ፡፡ አዲሱን ሰው እንልበስ፡፡
አዲሱ ሰው ልቡም፣ አስተሳሰቡም፣ አኗኗሩም፣ አካሔዱም ኩለንታው አዲስ ነው

፡፡ አዲሱ ሰው ሕዝብ ነው፡፡ የቀኝም የግራም ተሰጥኦ ያለው፡፡ በአንድ ሞልድ ያልተጨፈለቀ፣ ልዩነትን ፈርጥ ጌጥ ያደረገ፣ አንድነቱን በልዩነቱ፣ ልዩነቱን በአንድነቱ ያሸበረቀ፡፡
አዲሱ ሰው የፍቅር ልብ አለው፣ አዲሱ ሰው የሰላም በሮቹ ሁልጊዜ ክፍት ናቸው፣ አዲሱ ሰው በጥላቻ ፖለቲካ አያምንም፣ አዲሱ ሰው አዲስ የአንድነት ጉልበት አለው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ ሚንስትሮች ፈቀቅ በሉ፡፡ አዲሱ ሰው መጥቷልና! እናንተ ሳትወርዱ አዲሱ ሰው አይመጣም፡፡ እናንተ ሥልጣን ሳትለቅቁ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለቀቁ ማለት አይቻልም፡፡ ትናንትም እናንተ ዛሬም እናንተ ናችሁ! ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ለቀቁ የምንለው እናንተ ዘወር ስትሉ ብቻ ነው፡፡

ኢህአዴግ የምር አፍንጫውን ተሰንጎ ተይዟል።

አሁን እንደቀድሞው ጉዳዩ በሚስጥር ተይዞ ሳምንት ከተብላላ በኋላ አይደለም ለሕዝብ ጆሮ የሚደርሰው። ጠ/ሚ/ሩ ትላንት ወስነው ትላንት መልቀቅያቸውን አስገብተው ዛሬ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ራሳቸው መግለጫ ሰጡበት።
እሳቸው ሆነው እንጂ ይህ እኮ በሌላው ዓለም ትልቅ ነገር ነው። አስቡት እስቲ ኬንያ ውስጥ ኬንያታ የስልጣን መልቀቅያ ቢያስገባ? ኬንያ ባንድ እግሯ አትቆምም?
ሐገር ቤት የደወልኩላቸው አንድ ሁለት ሰዎች የሐማደን የስልጣን መልቀቅያ ልክ የአንድ ወረዳ ሊቀመንበር ስልጣን መልቀቅ ያህል ስሜት እንዳልሰጠ ለመረዳት ችያለሁኝ። እስከማስታውሰው ጠ/ሚ/ሩ በሕገ መንግስቱ የጦር ሐይልም ዋና አዛዥ ነው። እና እንዲህ ዓይነት ቁልፍ ስልጣን የያዘ ሰው ስልጣን ለቅቆ ከፌስ ቡክ ፌዝና ተረብ ውጭ አንድም ስሜት የሚሰጠው ሰው ሲጠፋ በእውነትም ሐገራችን ትልቅ ችግር ውስጥ እንዳለች የሚያሳየን ነው።
አሁን አንገብጋቢው ጥያቄ ማን ይተካዋል? የሚለው ሳይሆን የጠ/ሚ/ሩ ቦታ ልክ ሐማደ በነበረበት ጊዜ እንደነበረው አሻንጉሊት የሚቀመጥበት የማይረባ ስልጣን አልባ ቦታ እንደሆነ ይቀጥላል ወይንስ ቆፍጠን ያለ ሰው አግኝቶ የሐገሪቷን ማርሽ ይለውጣል ወይ ነው…
ፌስቡክ ላይ የሚደረገውን «እገሌ ይተካቸዋል!» ትንበያን በተመለከተ ከብዛቱ የተነሳ እኔም ራሴ ተስፋ ይኖረኝ ይሆን ብዬ እያሰብኩኝ እገኛለሁኝ።
ለማንኛውም ለሐይለማርያም ደሳለኝ «እንኳን ደስ አልዎት» ለማለት እፈልጋለሁኝ። አዎ ይህን ከሚያክል ስልጣን በጥይት ተመትቶ ከመውረድ አሊያም እንደ ብዙ ሐገራት መሪ ወደ ስደት ከመውጣት በመጨረሻዋም ሰዓት ብትሆን ራስን በክብር ማሰናበት ትልቅ ነገር ነው። የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ታሪክ ደገሙት ለማለት ባልደፍርም (ወደፊት የኢህአዴግ ተቃዋሚ ሆነው አይዎታለሁኝ የሚል ግምቴ 0% ስለሆነ) ቢያንስ ይህ በራሱ ለእርስዎ ትልቅ ድል ነው!
ለኛስ? እንግዲህ የሚያመጣውን ዳር ይዘን ማየት ነው። ኢህአዴግ ያስራል፣ ኢህአዴግ ይፈታል፣ ኢህአዴግ ይገድላል፣ ኢህአዴግ ስልጣን ይለቅቃል፣ ኢህአዴግ የለቀቅኩትን ስልጣን ለሕዝብ ጥቅም ስል ተመልሼበታለሁኝ ……… ይላል። እኛ እሱን እየተከተልን ነገር ማራገብ ብቻ ሆነናል። ስለዚህ አሁንም ቀጣዩን አጀንዳ እስኪሰጡን መጠበቅ ብቻ ነው።

Filed in: Amharic