>

የህወሓት እና ኦህዴድ ፍልሚያ ያስከተለው የማቃት ስቅታ ወይስ የኃይል ጨዋታ? (ስዩም ተሾመ)

በተለይ ባለፉት ሦስት አመታት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የነበሩበትን ሁኔታ በትውስታ ስመለከት ሁለት የተለያየ ስሜት ይፈጥርብኛል። አቶ ኃይለማሪያም እንደ ሰው በራሳቸው አስበው የተናገሩትንና ያደረጉትን ነገር ሳስብ ያሳዝኑኛል፣ አንዳንዴ ደግሞ ያስቁኛል። ለምሳሌ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጠ/ሚኒስትር እንደሆኑ ከኬኒያው ፕረዜዳንት እሁሩ ኬኒያታ ጋር “ሰለሜ፥ ሰለሜ፥…” ሲጨፍሩ፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ “ጥሬ ስጋ እንደሚወዱ”፣ በተለይ ደግሞ “ስለ ታጋሹ ፖሊስ እና ግልፍተኛ ወጣት የተናገሩት ተረተረት” ደግሞ ከማሳቅም አልፎ ያሳቅቃል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ አቶ ኃይለማሪያም በራሳቸው ትክክል የመሰላቸውን ውሳኔና መመሪያ አሳልፈዋል። ለምሳሌ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “እኔ የምወስነው በተጠናቀረ መረጃ ላይ ተመስርቼ ሳይሆን ሰዎች በነገሩኝ ላይ ነው” በማለት ስለ መንግስታቸው ሥራና አሰራር እቅጩን መናገራቸው የሰዉዬውን ሃቀኝነት ያሳያል። በተመሳሳይ በ2008 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ የመንግስታቸውን የስድስት ወር አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ ጠ/ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ለተፈጠሩት አለመረጋጋቶችና ችግሮች በመንግስታቸው ስም “የኢትዮጲን ሕዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ማለታቸው ይታወሳል። አያይዘውም “በኦሮሚያና አማራ አንዳንድ አከባቢዎች ለተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሳናቀርብ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሕዝቡ ምሬት ስላለው የተፈጠረ መሆኑን ተገንዝበናል” ብለው ነበር።

ሆኖም ግን፣ በተለያዩ አከባቢዎች ዜጎች ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ቁጥር የፀጥታ ኃይሎች እንዳለፈው ግዜ መደብደብ፣ ማስርና መግደል ቀጠሉ። በግንቦት ወር 2008 ላይ ሁኔታው ያሳሰባቸው አንጋፋው የኦሮሞ መብት ታጋይ ኦቦ ሌንጮ ለታ “Who is in control of Ethiopia?” በሚል ርዕስ ባወጡት ፅሁፍ እንደገለፁት፣ የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች እና በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መመሪያ አልተቀበሉትም፣ ወይም ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት አልተንቀሳቀሱም።

በእርግጥ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደ ግለሰብ በራሳቸው አስበው የተናገሩት ሃሳብ ሆነ ያሳለፉት ውሳኔ በሙሉ ዜጎችን እንደ ቀልድ ከማሳቅ ወይም በሃፍረት ከማሳቀቅ አያልፍም። ምክንያቱም ጠ/ሚ ኃይለማሪያም በእንዲህ ያለ ፖለቲካዊ ቀውስ ለመምራት የሚያስችል ቅቡልነት (Charisma) ወይም አቅም (capacity) የላቸውም። ከዚህ በተጨማሪ፣ አቶ ኃይለማሪያም ጠ/ሚኒስትር የሆኑት በራሳቸው አስበው እንዲናገሩና በነፃነት እንዲወስኑ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ከሌሎች ሰዎች የሰሙትን እንዲናገሩ፣ በተባሉት መሰረት እንዲወስኑ ታስቦ ነው።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም ላይ የበሀገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ችግር “ምንም ምክንያት ሳናቀርብ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሕዝቡ ምሬት ስላለው የተፈጠረ ነው” በማለት የሀገሪቱን ሕዝብ ይቅርታ ሲጠይቁ ተግባራዊ አልተደረገም። ሆኖም ግን፣ ነሃሴ 24/2008 ዓ.ም “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” በማለት የሰጡት መመሪያ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ተደርጓል። ይህን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞውን ይበልጥ አባብሶታል። በመጨረሻ መስከረም 28/2009 ዓ.ም በሀገሪቱ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጇል። አዋጅም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ተደርጓል። ከዚያ በፊት ግን በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አዲሱ የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን መምጣቱ ይታወሳል።

ዛሬም ሆነ ትላንት የሀገሪቱን የፀጥታ ኃይሎች በመጠቀም የሕዝቡን ጥያቄ በኃይል የማዳፈን ፀረ-ለውጥ አቋምና አመለካከት ያለው ህወሓት ነው። የሀገሪቱ የደህንነት፥ የፖሊስና መከላከያ ሰራዊት በዋናነት የሚመራው በህወሓት አባላትና የቀድሞ ታጋዮች እንደሆነ ግልፅ ነው። እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ ለፈፀሙት ግፍና በደል ጠ/ሚኒስትሩ በራሳቸው ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል። ነገር ግን፣ ይቅርታውም ሆነ ይህን ተከትሎ የሰጡት መመሪያ በህወሓቶች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ከስድስት ወራት በኋላ ጠ/ሚኒስትሩ “ሁሉም የፀጥታ ኃይሎች የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ አዝዣለሁ” የሚል መመሪያ ሲሰጡ ግን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የተደረገው ሃሳብና ውሳኔው የህወሓቶች ስለሆነ ነው።

እስከ 2008 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የጠ/ሚኒስትሩ መመሪያ ተግባራዊነት የሚወስኑት ህወሓቶች ነበሩ። የራሳቸውን የበላይነት ለማስቀጠል የሚያስችል ማንኛውንም ዓይነት መመሪያ ለጠ/ሚኒስትሩ ያቀርባሉ። ነገር ግን፣ በተለይ ከ2010 በኋላ የህወሓትን የበላይነት ለማስወገድ በግልፅ የሚታገል የፖለቲካ ኃይል በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ ተፈጥሯል። ይህ ኃይል የኦህዴድ አዲሱ አመራር ነው። በዚህ ረገድ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አከባቢ ተግባራዊ ሊደረግ የነበረው “የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት” እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

“የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት” የተቋቋመው በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ላይ እንደ አዲስ ሊጣል የነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከኦህዴድ በኩል በገጠመው ጠንካራ ተቃውሞ ምክንያት ውድቅ በመደረጉ ምክንያት ነው። በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የተቋቋመበትን መሰረታዊ ዓላማና ግብ ማሳካት የተሳነው ከኦህዴድና ብዓዴን በኩል በገጠመው ጠንካራ ተቃውሞ ምክንያት ነው። ከፖለቲካ እስረኞች መፈታት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው እስጣ-ገባም በዋናነት በኦህዴድና ህወሓት መካከል ያለው ትንቅንቅ ነፀብራቅ ነው።

ጠ/ሚኒስትሩ በራሳቸው አስበው የተናገሩት ሃሳብ እና የወሰኑት ውሳኔ ተግባራዊ አለመደረጉን ለምደውታል። ቢያንስ ግን እስካለፈው አመት ድረስ ከህወሓቶች የሰሙትን ሃሳብ መናገር እና የተሰጣቸውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይችሉ ነበር። በተለይ ከ2010 ወዲህ ግን ከህወሓቶች ከሰሙትና ከተሰጣቸው ተቃራኒ የሆነ ሃሳብና መመሪያ ኦህዴድ ይዞ ይመጣል። በመሆኑም የህወሓቶችን ፀረ-ለውጥ አቋምና መመሪያ ኦህዴዶች ውድቅ ለማድረግ ይንቀሳቀሳሉ። የኦህዴዶችን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመግታት ህወሓቶች ያለ መታከት ይታትራሉ።

በዚህ መሃል በድርጅቱና በሚመሩት መንግስት ውስጥ ከፍተኛውን የስልጣን እርከን የያዙት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሳንድውች ሆነዋል። በለውጥና ፀረ-ለውጥ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭትና ፍጭት ጠ/ሚኒስትሩን ግራና ቀኝ እያጋጨ፥ እየፈጨ፥ እየጨመቀ፥ እያስጨነቀ፥… መላወሻ፥ መተንፈሻ፥ መሸሸጊያ ጥጋት ሲያሳጣቸው ከኃላፊነታቸው ለመውረድ መልቀቂያ አስገቡ።

በዚህ ምክንያት ህወሓትና ኦህዴድ ከእጅ አዙር ፍልሚያ ወጥተው ፊት ለፊት ተፋጥጠዋል። ህወሓት ወታደራዊ ድጋፍ ሲኖረው ኦህዴድ ህዝባዊ ድጋፍ አለው። ህወሓት ከተወሰኑ የትግራይና የሶማሌ ክልል ልሂቃን ጋር ባለው የጥቅም ትስስር ድጋፍ ያገኛል። ኦህዴድ ከአብዛኛው የኦሮሞና አማራ ልሂቃን በመርህ ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ያገኛል። ህወሓት የበላይነቱን፣ ኦህዴድ ደግሞ እኩልነቱን ለማረጋገጥ የሚያድርጉት ፍልሚያ የመጨረሻው ዙር ላይ ደርሷል። የህወሓት የበላይነት የሚረጋገጠው የኦህዴድን እኩልነት ንቅናቄ በኃይል በማዳፈን ነው። የኦህዴድን እኩልነት ማረጋገጥ የሚቻለው የህወሓትን የበላይነት በማስወገድ ነው። ለሁለቱም ፍልሚያው የሕልውና ጉዳይ ነው።

በዚህ መሰረት፣ ዛሬ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ መልቀቂያ በህወሓትና ኦህዴድ መካከል የሚካሄደው የመጨረሻ ዙር ፍልሚያ ያስከተለው “የማቃት ስቅታ” ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ፍልሚያ ከምክንያትነት አንፃር ብቻ ማየት ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም፣ የጠ/ሚኒስትሩ ውሳኔ የፍልሚያውን ውጤት መሰረት ያደረገ ሊሆን ይችላል። ይህ ሲሆን የጠ/ሚኒስትሩ ውሳኔ ከማቃት ስቅታ ይልቅ የኃይል ጨዋታ ይሆናል።

ጠ/ሚኒስትሩ እስካሁን ድረስ በነበራቸው የሥልጣን ቆይታ የህወሓት መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም። ወደፊትም ቢሆን የህወሓትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት የሚያረጋግጥ ካልሆነ በስተቀር በራሳቸው አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ውሳኔ ማሳለፍና ማስፈፀም አይችሉም። ከዚህ በተቃራኒ፣ የህወሓትን የበላይነት ማስወገድ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ የኃይል መጋራት እንዲኖር ያስችላል።

በመሆኑም ጠ/ሚኒስትሩ ሆኑ የድርጅታቸው ደህዴን አዲስ በሚመሰረተው መንግስት ውስጥ የሚገባቸውን የፖለቲካ ስልጣን ያገኛሉ። ይህ ስልጣን እንደ አሁኑ የህወሓት መጠቀሚያ ሳይሆን በሀገሪቱ ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የመወሰን የሚያስችል ስልጣን ይሆናል። ስለዚህ በጠ/ሚኒስትርነት የህወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል መጠቀሚያ ከመሆን ስልጣኑን በመልቀቅ የኃይል ሚዛኑን ወደ ኦህዴድ እንዲያዘነብል ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር የጠ/ሚኒስተሩ መልቀቂያ የኃይል ሚዛኑን የተከተለ ጨዋታ ይሆናል።

በመሰረቱ የህወሓት ባላንጣ የሆነው አዲሱ የኦህዴድ አመራር የጠ/ሚኒስተርነት ቦታውን አጥብቆ ይፈልገዋል። በተቃራኒው ህወሓት እንደ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ያለ የራሱን አጀንዳ የሚያስፈፅምበት ባለስልጣን ከቶ አያገኝም። በመሆኑም የጠ/ሚኒስትሩ መልቀቂያ ለኦህዴድ የሚፈልገውን ቦታ ክፍት አድርጎለታል፣ ለህወሓት ደግሞ ሲጠቀምበት የነበረውን ቦታ አሳጥቶታል። ስለዚህ የጠ/ሚኒስትሩ መልቀቂያ የማቃት ስቅታ ሆነ የኃይል ጨዋታ የኃይል ሚዛኑን ወደ ኦህዴድ እንዲያዘነብል አድርጎታል።

Filed in: Amharic