>

አወዳደቃችሁን አሳምሩ! (ዘውድአለም ታደሰ)

ኢህአዴግ ሆይ!!! መቼም ከዚህ በኋላ እንደምንም ብለህ ጥቂት ግዜ ትገዛ ይሆናል እንጂ ያ ህዝብ ላይ የምታላግጥበት ፣ ያሻህን እያሰርክ የምትኮፈስበት ፣ ያሻህን ህግ አውጥተህ በማግስቱ የምትሽርበት ፣ ህዝብ በረሃብ እያለቀ የማይረባ የቁጥር ድርድር እያስቀመጥክ ኢኮኖሚህ አድጓል ብለህ የምትቀልድበት ፣ አመፅን በተኩስ የምታበርድበት ፣  ያለፈው ስርአት መልሶ ላይመጣ እንደተገረሰሰ ታውቃለህ!!! ከዚህ በኋላ ከዚህ የህዝብ እምቢተኝነት ማምለጥ ፈፅሞ የማይታሰብ ነው።
አሁን ሁለት አይነት አማራጭ አለ!!! በክብር መውረድና በአመፅ መውደቅ። ያው በርግጥ ሁለቱም መውደቅ ነው። ግን አወዳደቅህን ምትወስነው አንተ ነህ!! ብሔራዊ እርቅ አውጀህና ሃጢአትህን አስደምስሰህ በጀግንነት ስልጣንህን አሳልፈህ በፈቃድህ ትሰጣለህ። ወይም ህዝብ የቱኒዚያ ፣ የሊቢያ ፣ የግብፅን ታሪክ ይደግማል!! ሁለተኛው ምርጫ እናንተን ዘልአለማዊ የታሪክ ተወቃሾች ፣ ህዝቡንም አላስፈላጊ መስዋእትነት ከፋይ እንዲሆን ያደርገዋል።
ዛሬ መንግስቱ ሃይለማሪያምንና አብዛኞቹ የደርግ ባለስልጣናትን ተመልከቱ። ስማቸው ሲጠራ በኩራት «አቤት» ሚሉት ስንቶቹ ናቸው? ብዙዎቹ ወህኒ ወድቀዋል ፣ ብዙዎቹ በየሀገሩ ተበትነው ራሳቸውን ደብቀው ለመኖር ተገድደዋል። አዎ አብዛኞቹ ያለፈ ታሪካቸውን ቀድደው ቢጥሉትና ያለፈ ውሳኔያቸውን መለወጥ ቢችሉ ደስታቸው ነው። ግን አቅም የላቸውም። አወዳደቃቸው የጀግና አልነበረምና እንደጀግና አንገታቸውን ቀና አርገው ለመኖር አልታደሉም።
እናንተስ ከነሱ ምን ትማራላችሁ? እንኳን ሚሊዮኖች አደባባይ ወጥተው እየተቃወሟችሁ ፣ እንኳን ህዝባዊ እንቢተኝነቱ እዚህ ደርሶ ይቅርና ከዚህ ያነሰ አመፅም አንድን ስርአት ለመናድ በቂ ነው። መንግስቱ ሃይለማርያም አንድ ወቅት አንዲህ ብለው ነበር
«እኛ የሃይለስላሴን መንግስት የጣልነው መሳሪያ ስለነበረን ነው። ያ መሳሪያ የያዘ ሃይል ሲከፋው ወደኛ እንደማይዞር ምን ዋስትና አለን?»
በክብር ህዝብ ለሚመርጠው አካል ስልጣን ካልሰጣችሁ ይህ ስርአቱን እንዲጠብቅላችሁ በራሳችሁ የፖለቲካ አይዲዎሎጂ ቅርፅ ያስያዛችሁት ወታደር የወገኑን ድምፅ ሰምቶ ብረቱን ወደናንተ እንደማያዞር በምን እርግጠኛ ናችሁ? እንኳን ምድራዊ ወታደር መላእክም እንደሚከዳ በሰይጣን አይተናል። እና ያ የታጠቀ ኦሮሞና አማራ ወታደር ፣ ያ የታጠቀ ደቡብና ሶማሌ ወታደር ፣ ያ የታጠቀ ትግሬ ወታደር ዘልአለም ታምኖ ለስርአቴ ዘብ ይቆማል ማለት ሞኝነት አይደለም?
አሁን ግዜው አብቅቷል። ዘልአለም የምትታወሱበትን ታሪክ ስሩ። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ በህዝብ ለተመረጠ አካል ስልጣናችሁን አስረክባችሁ ቀሪ ዘመናችሁን የምትኮሩበትን ታሪክ ፈፅሙ። መውደቃችሁ ካልቀረ እንደጥሩ በረኛ አወዳደቃችሁን አሳምሩ!! ይሄ ህዝብ የዋህ ነው። ዛሬ ከጎኑ ብትቆሙለት ያለፈ ሃጢአታችሁን ይቅር ይላል!!
 የደቡብ አፍሪካን አርአያ ተከትላችሁ national reconciliation አውጁ! በውጪም በውስጥም ካሉ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ተደራደሩ። ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ይቋቋም። እናንተ ራሳችሁን ያገለላችሁበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይደረግ። ከዚያ በህዝብ ለተመረጠው አካል ለሌሎች የአፍሪካ መንግስታት ምሳሌ በሚሆን መልኩ ስልጣናችሁን አስረክቡና ነፃ ውጡ!! ይሄ ለሁሉም የሚጠቅም። ሁሉንም የሚያስደስት ታሪካዊ ፍፃሜ ይሆናል!
Filed in: Amharic