>

እውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከርእሰ መመስተዳርነት ተነስተው አምባሳደር ሊሆኑ ነውን? (ውብሸት ሙላት)

በእንተ ገዱ ንቁም በበኅላዌነ- ስለ ገዱ ባለንበት ጸንተን እንቁም!
እውን ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሆኗል ወይም ሊሆን ነውን?
እውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከርእሰ መመስተዳርነት ተነስተው አምባሳደር ሊሆኑ ነውን?
በተለይ ትላንትና እና ዛሬ ኢትዮጵያን እጅግ በርካታ ዜናዎች አጨናንቀዋታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው  ለቀቁ! የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ! እነ ኮሌነል ደመቀ ዘውዱ፣እነ ንግሥት ይርጋ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስራት ሊፈቱ ነው! ሌሎችም ሌሎችም!
በእዚህ መካከል የተሰነቀረች አንዲት ወሬ፣ብዙም እውነት በማውራት ከማትታወቅ አካባቢ የመነጨች ሐሜትም አብራ በዜና መልክ እየተራባቻች ትገኛለች፡፡ ወሬዋም፣የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር እና የብአዴን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሥልጣናቸው ተነስተዋል፤በምትካቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ የምትል ወሬ ለሕዝብ ሻጥ ተደረገች፡፡ አንግዲህ የሕዝቡን የሙቀት እና የልብ ትርታ መለኪያ መሆኗ ነው፡፡
ስለ አቶ ገዱ፣ በመሠራጨት ላይ ያለችው ወሬ ግን እውነትነት የራቃት ናት፡፡ ስለምን ካለችሁ መልሱ እንዲህ ነው፡፡ አንድም  “ጠላቶቼ (አሳዳጆቼ) በእኔ ላይ ስለምን  በረቱ?” እንዲል የመጽሐፍ ቅድሱ  ነብዩ ዳዊት ስለምን ሰዎች በአቶ ገዱ ላይ ዘመቱ ብለን እንድንጠይቅ ስለሚያስገድደን ነው፡፡
ልብ በሉ! ስለ ሊቀመንበሩ ፣አቶ ደመቀ መኮንን፣ ወይም ስለ ድርጅት ጉዳዩ ስለ አቶ አለምነው መኮንን፣ ሳይወራ አቶ ገዱ ስለምን አጀንዳ ሆኑ?
 “አለ ነገር አለ ነገር
ቁልቁለቱን ወርደን ወንዙን ሳንሻገር” አለ አቅራሪ! ነገር ቢኖር እንጂ አቶ ገዱ ለምን ይሔን ያህል ተወራባቸው?
 ሌላ ነጥብ ለመጨመር ያህል፡-  አቶ ገዱን በተለያዩ ጊዜያት የተባሉትን አስታውሱልኝማ! “ልጆቹን እና ባልተቤቱን ይዞ ከአገር ወጣ፤ኮበለለ፤ከዳ”  ወዘተ መባሉንም ከግምት አግቧት! ስለምን ይህ ሁሉ ወሬ አስፈለገ?  ከስንት ጊዜ በኋላ ስለምን የወሬ ርእስ አንዲሆን ተፈለገ? ከዓመት በፊት ሰናይት መብራሃቱ ስለ አቶ ገዱ ከሥልጣን መነሳትና መባረር የነዛችውን የሐሰት ወሬም  ከወሬ ዱሏት! ወይም እንድታጣሩ ብቻ እጋብዛለሁ! አሁንም የዜናው ምንጭ ማን እንደሆነ አጣሩ! እስክትደርሱበት ድረስ ግን “ባለንበት ጸንተን እንቁም!”
ሌላም ምክንያቶችን መጨመር እችላለን! ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሊሆን ነው ተብሎ መወራት ከጀመረ ቢያንስ አንድ ወር ይሆነዋል፡፡ አቶ ገዱ ደግሞ “አውስትራሊያ ቤት ተገዘቶለታል፣እዚያው አውስትራሊያም አምባሰደርም ይሆናል” እየተባለ ነው፡፡ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግን የአቶ አባይ ወልዱ ባልተቤት መሆናቸውን፤ እንዲሁም መንግሥት በምን አግባብ ለገዱ ቤት ሊገዛ እንደሚችልም አብሰልስሉት፡፡ መቼም ውሽት በዚህ ደረጃ ሲሆን መጠርጠር ደግ ነው ብዬ ነው፡፡
ለነገሩ ሌላም አለ፡፡ ወሬዋ የተለቀቀችው የብአዴን ስበሰባ ሳይጠናቀቅ እንደውም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢሕዴግ ሥራ አስፈጻሚን  ስበሰባ ስለጠሩ እንዲሁም በማግስቱም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በመኖሩ ምክንያት የብአዴን  ስብሳባ ሊቀጥል በማይችልበት ሁኔታ እንዲሁም እነ ኮሌኔል ደመቀ ዘወዱ፣ንግሥት ይርጋ፣እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ክሳቸው ተቋርጦ እና በይቅርታ በተለቀቁበት ቀን ስለ ገዱ ይችን ነጠላ ዜማ መልቀቅ  የምር  ውሸት መሆኗን  እንዲሁም ለነገር መሆኗን ያሳብቅባታል::
እንደው ብዙ ማለት ይቻል ነበር፡፡ ግን፣የብአዴን ስብሰባ ሳይጠናቀቅ ምናልባትም ከሰኞ በፊት ምንም ነገር ማለት በማይቻልበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት የውሸት እና የማደናገሪያ ነጠላ ዜማ መልቀቅ ብዙ ነገርን እንድናውጠነጥን ያስገድዳል፡፡ ለማንኛውም በተረዳ ነገር፣ ምንጩ ካልታወቀ ውስጥ ሰው እንደተረዳነው ስለ አቶ ገዱ የተወራው ውሸት በመሆኑ ቢያንስ እስከ ሰኞ ባለንበት ጸንተን እና ተረጋግተን እንቆይ፡፡
ሰኞ ወይም ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ቀናት “ሽልም ከሆነ ይገፋል፤እንትንም ከሆነ ይጠፋል፡፡”  ግን እንደው አቶ ገዱን አሳዳጆቹ ስለምን በዙ? አምባሳደርነቱንም የአቶ አባይ ወልዱ ባልተቤት ካሉበት ለምን አደረጉት? ወደፊት የማስለቀቅ ሥልጣን ያለው ሰው ይሆን ይችን ነፋስ የለቀቃት? እኔ እምለው አውስትራሊያ ለአቶ ገዱ ምንድን ናት?
ለማንኛውም፡-
ዶ/ር ጥላዬ ጌጤም  (የትምህርት ሚኒስቴሩ) ርእሰ መስተዳድር አልሆኑም፡፡ ዶ/ር ይናገር ደሴም ምክትል ርእሰ መስተዳድር አልሆነም፡፡ ይኼው ነው እውነታው!
ደግሞ፣ አቶ አለምነው መኮንን የሚባለው ሰውዬ  የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ ዘንድ ሊመጣ ነው  ተብሏል!
እኔ የምለው “የሰሜኑ ቋያ” የት ገባ? የእሱ ድምጽ ባይጠፋ ይህ ሁሉ ሐሜት አይሠለጥንብንም ነበር!
እናም ባለንበት ጸንተን እንጠብቅ!
Filed in: Amharic