>

«ኢህአዴግን ማመን ቀብሮ ነው!»  (ዮናስ ሀጎስ)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ያህል ታውጇል። (ስድስት ወራት ሙሉ! በፈጣሪ…»
በእርግጥ በአፍሪካ ሐገራት ውስጥ ጠ/ሚ/ርን ያህል የጦር ሐይሎቹ አዛዥ የሆነ ሰው ስልጣን መልቀቅ እፈልጋለሁኝ ሲል የሐገሪቷ ቁልፍ ስልጣን ወደ ኤታማጆር ሹሙ ስለሚሄድና የስልጣን ሹክቻም ስለሚኖር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አስፈላጊ መሆኑ አይቀርም። ኢህአዴግ ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደባለፈው ጊዜ የእስረኞችን ቁጥር ለማብዛት ከተጠቀመበት በራስ ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ስለሚሆን የስልጣን ሽግግር የተባለው ነገር ከኢህአዴግ ወደ ኢህአዴግ ሳይሆን ከኢህአዴግ ወደ ተቃዋሚ ሐይሎች እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። ግን አሁን ያለውን ውጥረት ለማረጋጋት «ፋታ ፋታ!» የሚባለውን የነ ልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ ዓይነት ጩኸት ዓይነት ፍለጋ ከሆነ ተስፋ ሊኖረው ይችላል። የጠ/ሚ/ሩን ክፍት ቦታ በተገቢው ሰው ቶሎ ከመተካት ጀምሮ የጀመረውን እስረኛ የመፍታት ተግባሩን ከመቀጠል ቀጥሎ ሐገር ውስጥ መስዋዕትነት እየከፈሉ ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይ የምርጫ ሂደት እንዴት ከ100% ጨዋታ የፀዳ እንደሚሆን እውነተኛ የምክክር መድረክ ከፈጠረ ኢህአዴግም የለውጡ አካል መሆን የማይችልበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
•°•
አሁን ግን በዋነኝነት ላወራ የፈለግኩት ስለ ተቃዋሚዎቻችን ነው። ተቃዋሚዎቻችን ትላንት አስረግጬ እንደፃፍኩት የኢህአዴግን አጀንዳ ተቀብሎ ከማራገብ አልፈው ተርፈው ለኢህአዴግ ሊቀመንበር እስከማማረጥ ድረስ የገቡበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። እስረኞች መፈታታቸውን እንደ ትልቅ ድል ለሚቆጥሩ የተፈቺዎቹን የራሳቸውን «ይሄ አይደለም ዋናው ግብ…» ንግግር ላስታውሳቸው እፈልጋለሁኝ። ዋናው ግብ ስርዓት የመቀየር ጉዳይ ነው። ሕዝቡ ከተቃዋሚዎች የሚጠብቀው የተሻለ ስርዓት በሚመጣበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ እንጂ ቀጣይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ማን እንደሚሆን እንዲጨቃጨቁ አይደለም። አንዳንድ «ተቃዋሚዎች»ማ ስም እየጠሩ «እገሌ የማይመረጥ ከሆነ…  ዋ!» ዓይነት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ያስተዛዝባል። እገሌ የሚሉት ሰው የራሳቸው ብሔር ስለሆነ ይሁን የተሻለ ነገር ኢህአዴግ ውስጥ ይፈጥራል ብለው አስበው ይሁን ፈጣሪ ነው የሚያውቀው። ዋናው ነገር ግን ተቃዋሚዎች ለመርህ መገዛት እንዳለባቸው ማመን አለባቸው። መርሃቸው ኢህአዴግ ሊሻሻል ይችላል ብሎ የሚያምን ከሆነ የኢህአዴግ የአባልነት ካርድ ሳይውል ሳያድር ወስደው ኢህአዴግን ከውስጥ ሆነው መታገል ነው። አይ ኢህአዴግ ራሱ የለውጡ አካል ለመሆን የሚፈልግ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች በግልፅ እስኪያሳይ ድረስ ግን እንደኔ «ኢህአዴግን ማመን ቀብሮ ነው!» ብለው የሚያምኑ ከሆነ ደግሞ በሚገኙ ጥቃቅን ድሎች ሳይዘናጉ ወደ ዋናው ግባቸው ማተኮርና መስራት ይጠበቅባቸዋል። የነ እስክንድር፣ በቀለ ገርባ ኮሎኔል ደመቀ መፈታት ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ካለው ፋይዳ ውጭ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለው ፋይዳ በጣም ኢምንት ነው። እነዚህ ሰዎች ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍቶላቸው በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ውጤታማ ሆነው ሕዝብ መጥቀም ካልጀመሩ የመፈታታቸው ትርጉም ለሕዝቡ ኢምንት ነው። እንግዲህ ያሁኖቹን ለማየት ገና ቢሆንም ከዚህ በፊት በ«ይፈቱልን!» ጩኸት የተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች ግማሾቹ ወደ ስደት ወጥተው በዛው ሲቀሩ የተቀሩት ደግሞ ከፖለቲከኛነት ወደ አክቲቪስትነት ተቀይረው እንደኛው ፌስቡክ ላይ ተጠምደው እንደሚውሉ ነው ያየነው። ስለዚህ ተቃዋሚው ሐይል የእስረኞች መፈታት ችግሩ ያመጣው ሌላ ችግር እንጂ ዋናው ችግር አለመሆኑን መረዳትና ለዋናው ችግር በጊዜ ወደ ሕብረት መጥተው መፍትሔ መፈለግ መጀመር ነገ ዛሬ ሊባል የማይገባው ነገር መሆኑን ሊረዱ ይችላሉ።
•°•
በነገራችን ላይ የኢህአዴግን ባላውቅም ኢቢሲ ግን የለውጡ አካል ለመሆን መፈለጉን ዛሬ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በነበረው ዜና ላይ የሆነ ፍንጭ አይቻለሁኝ። ኢቢሲ ስለ አቶ ሐይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በፌስ ቡክ በዘገብነው ዜና ላይ የተሰጡ ኮመንቶች ብሎ ከአርባ ሁለት ሺህ በላይ ኮመንቶች እያሉለት ይህን ኮመንት አፅንዖት ሰጥቶት አቅርቦታል።
«የአቶ ሐይለማርያም ስልጣን መልቀቅ ምናልባት የተወሰነ መረጋጋት ይፈጥር እንደሆነ እንጂ ዋናውን ችግር አይፈታውም። ስለዚህ ኢህአዴግ ለዋናው ችግር በአስቸኳይ መፍትሔ ቢፈልግ የተሻለ ይመስለኛል…»
•°•
ወላሂ ነው የምላችሁ ይህ የ«አንዳንድ የአዲሳባ ነዋሪዎች» ኮመንት በጣም ነው የተመቸኝ። ኢቢሲም እንኳን ልብ ገዝቶ ለዋናው ችግር መፍትሔ እንፈልግ እያለ ባለበት ሰዓት ጠ/ሚ/ር የምታማርጡ ሰዎች አደብ ብትገዙ ምን ይላቹሃል?
Filed in: Amharic