>

“ክርስቲያኗ” አሜሪካ የውጭ ፖሊሲዋን በ“ደጉ ሳምራዊ” መርህ ቀርጻ አታውቅም (ፋሲል የኔዓለም)  

የአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ወደ አሜሪካ ለመኮብለል የሚጣደፈውን ባለስልጣን ቁጥር ይጨመረዋል። ጌታቸው አሰፋ የባለስልጣናትን ጉዞ የሚያግድ ህግ ሊያወጣ ይችላልና አስቡበት። ለኩብለላም ጊዜው አሁን ነው።

መግለጫው አሁን ያለውን የኢኮኖሚ ቀውስ ይበልጥ የሚያባብሰው ይሆናል። ባለሃብቶች ሃብታቸውን ለማሸሽ ባንኮችን ማጨናነቃቸው አይቀርም። ብሄራዊ ባንክ ከባንክ የሚወጣውን የገንዘብ መጠን የሚወስን ህግ ሊያወጣ ይችላል። ባንክ ቤት ውስጥ ገንዘብ ያስቀመጡ ሰዎች ገንዘባቸውን አውጥተው ፍራሽ ስር ቢደብቁት ተመራጭ ይሆናል። እገዳ ከተጣለ በሁዋላ ገንዘብ እንደ ልብ ማውጣት ላይኖር ይችላል። ዲያስፖራውም ዶላር ልኮ ቅጠል ታቅፎ እንደሚቀር በመገንዘብ፣ ዶላር ከመላክ ቢቆጠብ ካልታሰበ ኪሳራ ይድናል። የመሬትና የቤት ዋጋም ይወድቃል። በተለይ ኪራይ ለመብላት ሲሉ በባንክ ብድር ህንጻዎችን የሰሩ ሰዎች፣ ከፊታቸው ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

ህወሃት ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የገንዘብ ግሽበት እና የዶላር እጥረት በአፍጢሙ ሊደፋው ሲቃረብ 20/80 ….40/60… ምናምን …የሚባሉ ማጭበርበሪያዎች አምጥቶ ትንሽ ተንገዳገደ ፡ አሁን የፖለቲካውም ቀውስ ተደርቦበት የመውጪያ መንገዱን ማሰቢያም ግዜ የላቸውም አሁን ሁሉም ለፍርጠጣ አቆብቁቦ ነው ያለው ከአገር ቤት እንደሚሰማው ብር ወደ ዶላር የመለወጥ ሩጫው ተጧጡፏል ለኢትዮጵያ ገንዘብ ያበደሩ አገሮች ሁሉ “ገንዘባችን” የሚሉበት ወቅት ላይ ነን፤ ለእነሱ የሚከፈለው ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ የሚያውቀው፣ አንድዬ ብቻ ነው። ድሮ ከየትም ቀፍሎ ዶላር የሚያመጣውና የወያኔን ጓዳ ሸፍኖ የጭንቁን ጊዜ የሚያሳልፈው አላሙዲን ዛሬ የለም። ወያኔ በዚህ ሁሉ መሃል፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት በራሱ ላይ የሞት አዋጅ አውጇል።

በተያያዘ-  የትግሉ አላማ ፣ በህዝባዊ ምርጫ፣ አንዱን ስርዓት በሌላ ስርዓት ለመተካት ነው

ወገኖቼ! የምንታገለው አንድን ሰው በሌላ ሰው ለመተካት አይደለም። የትግሉ አላማ ፣ በህዝባዊ ምርጫ፣ አንዱን ስርዓት በሌላ ስርዓት ለመተካት ነው። መስዋዕትነት የተከፈለበትም የሚከፈልበትም ለዚህ አላማ ነው። ዘላቂ ሰላምና ያልተቋረጠ እድገት የሚገኘውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው። መሪዎቹን የመምረጥ መብቱን ለህዝብ እንተውለት። ” አውቅልሃለሁ” ከማለት አዙሪት እንውጣ ። እናውቃለን ካልንም፣ አዋቂነታችን አንድ ነጻ የምርጫ ስርዓት ከመመስረት አይለፍ። ለማ ይመቸኛል፣ በቀለ ይመቸኛል፣ አንዱአለም ይመቸኛል፣ ሌሎችም ብዙ የሚመቹኝ ሰዎች አሉ፣ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች፣ በግልም ይሁን በቡድን፣ ያለ ነጻ ምርጫ ስልጣን ቢይዙ አልቀበላቸውም። በህዝብ ተመርጠው ስልጣን በያዙ ጊዜ ግን ለአንድ ቀንም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ መስቀል አደባባይ ላይ እስክስታ ከሚወርዱት መሃል እሆናለሁ። በህዝብ ዘንድ በጣም “የሚጠላው” በረከት እንኳን በኢትዮጵያ ህዝብ ተመርጦ ስልጣን ቢይዝ አይከፋኝም፤ ዲሞክራሲ የምትወደውን ብቻ ሳይሆን የማትወደውንም እንድትቀበል የሚያስገደድ አስደሳችም አናዳጅም ስርዓት ነውና እያለቀስኩም ቢሆን በረከትን በመሪነት ለመቀበል አላቅማማም። ብርሃኑም( ፕ/ር) መትረጊሱን ወድሮ፣ አንዳርጋቸውም ከእስር የተፈቱ ጓደኞቹን ሰብስቦ ያለ ምርጫ ስልጣን እንይዛለን ብለው ቢሞክሩ፣ የመጀመሪያ የወዳጅ ጠላታቸው የምሆነው እኔ ነኝ። አላማችን የተወሰኑ ሰዎች የወደዱትን የሚሾሙበት የጠሉትን ደግሞ የሚሽሩበት ስርዓት ለመፍጠር ከሆነ፣ የተከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ በዜሮ ተባዛ ማለት ነው። የሊህቃን ምርጫ በህዝብ ምርጫ እስካልተተካ ድረስ እውነተኛ ለውጥ ሊኖር አይችልም። አሁን አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ከዚህ ቀውስ የሚያወጣት ማንም ሳይሆን በነጻ ምርጫ ስርዓት የመጣ ግለሰብ ብቻ ነው። ሁላችንም የተወደደውንም ይሁን የተጠላውን የምንሾምበት ነጻ ስርዓት እስኪመሰረት ድረስ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል።
Filed in: Amharic