«ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ስለ ሃይማኖት ሲነሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ጠ/ሚ ዐቢይ ክርስትያን ፤ እስላምን አንስተዉ አይሁድን ሳይጨምሩ ቀርተዉ አያዉቁም። ሃይማኖትን በተመለከተ የአይሁድን እምነት አብረዉ ይጠቅሳሉ፤ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያና ትልቁ ክስተት ነዉ።» ሲሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት አራት አምስት ዓመታት ለቤተ- እስራኤላዉያን የተመቻቸ ሁኔታ በመፈጠሩ ቤተ-እስራኤላዉያን የሃይማኖታቸዉን የሚያካሂዱበት ቤተ-እምነት ማለትም ሙክራብ መሰራቱን የነገሩን እና ስለ ቤተ-እስራኤላዉያን « አልያህ ቤት» የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉ እና በቤተ እስራኤላዉያን ጉዳይ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ላይ የሚገኙት አቶ መስፍን አሰፋ ነበሩ።
በያዝነዉ ሳምንት ወደ እስራኤል የገቡት 83 ቤተ- እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል ለመግባት ረጅም ዓመታት እንዳስቆጠሩ ነዉ የተነገረዉ። ተቀማጭነታቸዉን አዲስ አበባ ያደረጉና በቤተ- እስራኤላዉያን ጉዳይ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሂዱት እንዲሁም ለቤተ-እስራኤላዉያን መብት በመቆማቸዉ የሚታወቁት አቶ መስፍን አሰፋ እንደተናገሩት ቤተ-እስራኤላዉያኑ ጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኝ መጠባበቅያ ቦታ ላይ ሆነዉ ነዉ ወደ እስራኤል ለመሄድ እየጠበቁ የሚገኙት።
«በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና በጎንደር በሚገኝ መጠባበቅያ ጣብያዎች ላይ ወደ 13 ሺህ የሚሆኑ ቤተ- እስራኤላዉያን በካንፕ ዉስጥ ተቀምጠዉ ወደ እስራኤል የሚሄዱበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል የዛሬ ስድስት ወር አካባቢ አንድ ሺህ ቤተ-እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል እንዲገቡና እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዉ ሄደዋል። አሁን ደግሞ በዚህ በያዝነዉ ሳምንት ወደ 80 የሚሆኑ ቤተ-እስራኤላዉያን እየሩሳሌም ደርሰዋል።»
« በአንድ ካምፕ ሲባል በአንድ መንደር አንድ ላይ ለማለት ነዉ። ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1983 ዘመቻ ሰለሞን በሚካሄድበት ጊዜ በርካታ ቤተ -እስራኤላዉያን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርገዉ አዲስ አበባ ዉስጥ መሰረታዊ ነገሮች እንዲማሩ ንቃተ ሕሊና እንዲያገኙ ተደረጎ ፤ በአራት አምስት ዓመታት ዉስጥ ይወሰዳልሉ ተብሎ በነበረበት ጊዜ የመጡ ናቸዉ። በወቅቱ በደርግና በህወሃት መካከል በነበረዉ ጦርነት ምክንያት ህወሃት ወደ አዲስ አበባ እየቀረበ ሲመጣ ፤ ዘመቻ ሰለሞን አስገዳጅ ተብሎ ያኔ ለተወሰነ ጊዜ በየአንድ አካባቢ ሰብስቦ ማንቃት ማደራጀት የሚል መረሃ-ግብር ተይዞ ነበር። ያኔ የተጀመረዉ ልማድን ተከትሎ ነዉ አሁንም ቤተ-እስራኤላዉያን በአንድ አካባቢ የሚኖሩት። በዘመቻ ሰለሞን ወደ 10 ሺህ የሚሆኑ ቤተ -እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል ሲሄዱ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነዉ የነበሩ የነሱ ዘመዶች ጋብቾች ፤ እና ተከታዮች አዲስ አበባና ጎብደር ላይ ተሰባስበዉ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተረዱ ወደ 30 ዓመት ሊሆናቸዉ ፤ ወደ እስራኤል ለመሄድ እየተጠባበቁ ነዉ።
በማኅበረሰብ ጥናት በብሪታንያ ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ያጠናቀቁና ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዉ በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት በማስተማር ላይ የሚገኙት ፕሮፊሰር አበበ ዘገየ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ አይሁዳዉያን ወደ እስራኤል ለመሄድ ያለባቸዉ ፈተና ብሎም ከሄዱ በኋላ ስለሚገጥማቸዉ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን የሚያሳይ፤ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት « THE IMPOSSIBLE RETURN» «የማይቻለዉ ምልሰት» ወይም «የማይቻለዉ መመለስ» አልያም «ከባዱ ምልሰት» እንደማለት ነዉ ፤ በእንጊሊዘኛ መጽሐፍ አሳትመዋል። ይኸዉ መጽሐፋቸዉ ወደ አማርኛ እየተተረጎመ እንደሆነም ተናግረዋል።
«ለመጽሐፉ ይህን ርዕስ የሰጠሁበት ምክንያት ቤተ- እስራኤላዉያኑ ከኢትዮጵያ ይመለሳሉ ብሎ ያሰበ ስላልነበረ ነዉ። በኢትዮጵያ ዉስጥ ክርስትና እስልምና እንዲሁም የአይሁድ እምነት ከጥንት ጀምሮ እጅግ የታወቁ እና አንድ ላይ ሆነዉ የሚታዩ ናቸዉ።
ቤተ-እስራኤላዉያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ሲጓዙ ከ30 ዓመት በላይ ሆኖታል። እስካሁን ከ 60 እስከ 70 ሺህ ቤተ-እስራኤላዉያን እስራኤል መግባታቸዉ እንደሚገመት የተናገሩት አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸዉ እስራኤል ዉስጥ በአሁኑ ወቅት ወደ 110 ሺህ ቤተ- እስራኤላዉያን ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልፀዋል።
« ምንም ጥበቃ አይደረግለትም። ቤተ-እስራኤላዉያኑ በአብዛኛዉ ከጎንደር፤ ከሰሜን ወሎ እና ከደቡብ ትግራይ አካባቢ የሄዱ ናቸዉ። ስለዚህ ከሄዱባቸዉ አካባቢዎች ጠቅላላ የአይሁድን እምነት ኦሪታዊ ስርዓታቸዉን ተገለዉ በኖሩባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ያካሂዱ ስለነበር ሲወጡ ጥለዋቸዉ ነዉ የወጡት። ከዚያም በዚያዉ አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ቤተ- እስራኤላዉያን እና ቤተ እስራኤላዉያን ባልሆኑ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ቁሳቁሱ ግልጋሎት ላይ ይገኛል።
ለምሳሌ ከጎንደር ወጣ ብሎ በሚገኝ እነሱ በሚኖሩበት አካባቢ ላይ ሌሎች ቤተ-እስራኤላዉያን ያልሆኑ ማኅበረሰቦች እነሱ ይጠቀሙበት የነበረዉን መሳሪያ በመገልገል እነሱ ይሰሩበት የነበሩትን የተለያዩ መሳርያዎች ይገለገሉባቸዋል።
ፕሮፊሰር አበበ ዘገየ እስራኤል የሚኖሩት ከኢትዮጵያ የሄዱት አይሁዶች ቤተ እስራኤላዉያን የሚል ስያሜን ያገኙት ዋናዉ ምክንያት ከኢትዮጵያ በመሄዳቸዉ ነዉ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት አበክረዉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የጺዎናዉያን ጉዳይ ተከታታይ የሆኑት አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላዉያን ከማኅበረሰቡም ሆነ ከመንግሥት ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ ጠይቀዋል። ቃለ-ምልልስ የሰጡን በ«DW» ስም በማመስገን ሙሉ ስርጭቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!