>
10:34 pm - Tuesday August 16, 2022

ኑ ስለ ዕትጌ ጣይቱ ብጡል ጥቂት እናውጋ!!! (ታመሩ ተመስገን)

ኑ ስለ ዕትጌ ጣይቱ ብጡል ጥቂት እናውጋ!!!
ታመሩ ተመስገን
…… የጥቁርን ህዝብ ያነገሠው የአድዋ ድል መታሰቢያ እየተቃረበ መሆኑን አስታክኬ የእትጌ ጣይቱን የአድዋ ጀብድ በጥቂቱም ቢሆን ከዚህ ዝቅ ብየ እፅፋለሁ፡፡ ሴትነትን ዳግም አነግሳለሁ…
እቴጌ ጣይቱ ምክር በሰጠችው፣ ምንጯን አስገድባ ቁልቁል እያየችው፣ የጣሊያንን መንጋ ውኃ ጥም ቀጣችው፤
ቼ በለው ኧረ ቼ በለው
ቼ በለው እንደቆላ ወፍ
ቼ በለው እንደግሪሳ
ቼ በለው ያረፈው ልቤ
ቼ በለው ደግሞ ተነሳ
…… አንቶኔሊ በተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶች ተጠቅሞ፣ የአንቀጽ 17ን ትርጓሜ እርሱ በፈለገው መልኩ ማድረግ እንዳልሆነለት ሲረዳ፣ የጣሊያን መንግሥት ፍላጎቱን በጦር ኃይል እንደሚያሣካ ከፍተኛ ንቀት በተላበሰ አነጋገር ዛተ። በአንቶኔሊ ንቀት እና ዛቻ የተገረሙት እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ እጅግ ከፍተኛ በሆነ የአገር ፍቅር እና የነፃነት ወኔ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ነፃነት ለመጠበቅ የሚመጣውን ሁሉ በቁርጠኝነት ለመጋፈጥ እርግጠኛ በሆነ አነጋገር፦
«ሂድ ጦርነቱን የዛሬ ሳምንት አድርገው። እኛም የመጣውን እናሣየዋለን። እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ። የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ፣ ሞት አይደለም። አሁንም ሂድ፣ አይምሽብህ፣ የፎከርክበትን በፈቀድክ ጊዜ አድርገው። እኛም ከዚህ እንቆይሃለን።» በማለት እርሳቸውም እቅጩን ነግረው አሰናበቱት።
ከዚህ በኋላ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መኳንንቶቻቸውን ሰብስበው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ምክር ያዙ። በምክሩም የተለያዩ ኃሣቦች ቀርበው ሲብላሉ፣ ጣይቱ የሚከተለውን ሀሳብ ሰጡ።
« እኔ ሴት ነኝ። ጦርነትን አልወድም። ሆኖም ፣ ይህንን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ፤»
በማለት በመኳንንቱ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የኃሣብ መዋዠቅ በአንድ እንዲቆም እና ለአይቀሬው ጦርነት አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ ለተደረሰበት ውሣኔ አሰባሣቢ እና ማሠሪያ ቃል ሆነ።
በዚህም የተነሣ ሁሉም ለጦርነቱ ዝግጅት ፊቱን አዞረ። ጣሊያንም እንደፎከረው የኢትዮጵያን የመረብ ወንዝ ድንበር በመሻገር እስከ አምባላጌ ድረስ ዘለቀ። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ይህንን የጣሊያኖችን ትንኮሣ ሲሰሙ፣ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም. የሚከተለውን የክተት አዋጅ አወጁ።
«እግዚብአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞት፣ ሞት የሁሉም ነውና ለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሣፍሮኝ አያውቅም። ወደፊትም ያሣፍረኛል ብዬ አልጠረጥርም።
አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ኃይማኖት የሚለውጥ፣ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሩን ከብት ማለቅ፣ የሰውን ድካም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሣልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለኃይማኖትህ ስትል በሐዘንህ እርዳኝ። ወሳልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም፣ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻየም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።»
በአዋጁ መሠረት ሁሉም በየአካባቢው ዝግጅቱን አጠናቆ ከተተ። እቴጌ ጣይቱም 3ሺህ እግረኛና 6ሺህ ፈረሰኛ ጦር አስከትለው ዘመቱ። የዐድዋ ጦርነት ማሟሻ የሆነው ጦርነት የተጀመረው ኅዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም. አምባላጌ ላይ ነበር።
.
በለው ኧረ ቼ በለው
ቼ በለው ከሳ ጠቆረ 
ቼ በለው ብለው ቢደፍሩት
ቼ በለው ያመረረ ዕለት
ቼ በለው  አይማለዱት
ይቀጥላል…
.
ኢትዮጲያዊነት ይፋፋምብን
Filed in: Amharic