>

«ከባዱ ምልሰት!!!» የቤተ - እስራኤላዉያኑ ጉዳይ!!! (ዶችቬሌ)

«ከባዱ ምልሰት!!!» የቤተ – እስራኤላዉያኑ ጉዳይ!!!

አዜብ ታደሰ -እና – ኂሩት መለሰ  (ዶችቬሌ)

«ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ስለ ሃይማኖት ሲነሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ጠ/ሚ ዐቢይ ክርስትያን ፤ እስላምን አንስተዉ አይሁድን ሳይጨምሩ ቀርተዉ አያዉቁም። ሃይማኖትን በተመለከተ የአይሁድን እምነት አብረዉ ይጠቅሳሉ፤ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያና ትልቁ ክስተት ነዉ።» ሲሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት አራት አምስት ዓመታት ለቤተ- እስራኤላዉያን የተመቻቸ ሁኔታ በመፈጠሩ ቤተ-እስራኤላዉያን የሃይማኖታቸዉን የሚያካሂዱበት ቤተ-እምነት ማለትም ሙክራብ መሰራቱን የነገሩን እና ስለ ቤተ-እስራኤላዉያን « አልያህ ቤት» የተሰኘ መጽሐፍ የጻፉ እና በቤተ እስራኤላዉያን ጉዳይ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ላይ የሚገኙት አቶ መስፍን አሰፋ ነበሩ።

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ማለትም ጥር ወር መገባደጃ 2011ዓ.ም ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለመሄድ ይጠባበቁ ከነበሩ ቤተ-እስራኤላዉያን መካከል ወደ ሰማንያ የሚሆኑት ፈቃድ አግኝተዉ እስራኤል ገብተዋል። ይፋ በወጣዉ ዘገባ መሰረት ወደ እስራኤል ለመሄድ ተመዝግበዉ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት ቤተ-እስራኤላዉያን ወደ 8000 ሺህ ይሆናሉ። በኢትዮጵያ የቤተ- እስራኤላዉያንን ጉዳይ የሚከታተሉ ተሟጋቾች እንደሚሉት ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ወደ እስራኤል እንሄዳለን ብለዉ የሚጠባበቁት ቤተ-እስራኤላዉያን ወደ 13 ሺህ ይሆናሉ።
በያዝነዉ ሳምንት ወደ እስራኤል የገቡት 83 ቤተ- እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል ለመግባት ረጅም ዓመታት እንዳስቆጠሩ ነዉ የተነገረዉ። ተቀማጭነታቸዉን አዲስ አበባ ያደረጉና በቤተ- እስራኤላዉያን ጉዳይ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን የሚያካሂዱት እንዲሁም ለቤተ-እስራኤላዉያን መብት በመቆማቸዉ የሚታወቁት አቶ መስፍን አሰፋ እንደተናገሩት ቤተ-እስራኤላዉያኑ ጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኝ መጠባበቅያ ቦታ ላይ ሆነዉ ነዉ ወደ እስራኤል ለመሄድ እየጠበቁ የሚገኙት።
«በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባና በጎንደር በሚገኝ መጠባበቅያ ጣብያዎች ላይ ወደ 13 ሺህ የሚሆኑ ቤተ- እስራኤላዉያን በካንፕ ዉስጥ ተቀምጠዉ ወደ እስራኤል የሚሄዱበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል የዛሬ ስድስት ወር አካባቢ አንድ ሺህ ቤተ-እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል እንዲገቡና እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዉ ሄደዋል። አሁን ደግሞ በዚህ በያዝነዉ  ሳምንት ወደ 80 የሚሆኑ ቤተ-እስራኤላዉያን እየሩሳሌም ደርሰዋል።»
እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ የኖሩ ኢትዮጵያ የተወለዱ፤ ያደጉ መሆናቸዉ ይታወቃል። ለምንድን ነዉ ካምፕ ዉስጥ የሚኖሩት?
« በአንድ ካምፕ ሲባል በአንድ መንደር አንድ ላይ ለማለት ነዉ። ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 1983 ዘመቻ ሰለሞን በሚካሄድበት ጊዜ  በርካታ ቤተ -እስራኤላዉያን ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርገዉ አዲስ አበባ ዉስጥ መሰረታዊ ነገሮች እንዲማሩ ንቃተ ሕሊና እንዲያገኙ ተደረጎ ፤ በአራት አምስት ዓመታት ዉስጥ ይወሰዳልሉ ተብሎ በነበረበት ጊዜ የመጡ ናቸዉ። በወቅቱ በደርግና በህወሃት መካከል በነበረዉ ጦርነት ምክንያት ህወሃት ወደ አዲስ አበባ እየቀረበ ሲመጣ ፤ ዘመቻ ሰለሞን አስገዳጅ ተብሎ ያኔ ለተወሰነ ጊዜ በየአንድ አካባቢ ሰብስቦ ማንቃት ማደራጀት የሚል መረሃ-ግብር ተይዞ ነበር። ያኔ የተጀመረዉ ልማድን ተከትሎ ነዉ አሁንም ቤተ-እስራኤላዉያን በአንድ አካባቢ የሚኖሩት። በዘመቻ ሰለሞን ወደ 10 ሺህ የሚሆኑ ቤተ -እስራኤላዉያን ወደ እስራኤል ሲሄዱ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነዉ የነበሩ የነሱ ዘመዶች ጋብቾች ፤ እና ተከታዮች አዲስ አበባና ጎብደር ላይ ተሰባስበዉ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተረዱ ወደ 30 ዓመት ሊሆናቸዉ ፤ ወደ እስራኤል ለመሄድ እየተጠባበቁ ነዉ።
በዘገባዉ መሰረት ባለፈዉ ሰኞ እየሩሳሌም የደረሱትም ሆነ ወደ እስራኤል እንሄዳለን ብለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በመጠባበቅ ላይ ያሉትን ዜጎች እስራኤል አይሁድ ናቸዉ ብላ እዉቅናን አትሰጥም ይልቅዬ የአይሁድ ዝርያ አልያም ዝምድና ያላቸዉ ነዉ የምትላቸዉ። ከቀናቶች በፊት እስራኤል የገቡት ቤተ-እስራኤላዉያን ይህን ሁኔታ ይቀበሉት ይሆን? አቶ መስፍን አሰፋ።
«ይህ ማለት በዘር በደም አይሁዳዉያን አይደሉም ማለት አይደለም። እነዚህ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከተሸነፉበት  ከ 13 ኛዉ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እና የኢትዮጵያ የመንግሥት ሃይማኖት የክርስትና ከሆነ ጀምሮ በስቃይና በመከራ ነበር የሚኖሩት። ተሰባስበዉ በሚኖሩበት አካባቢዎች በሙሉ የአይሁድ እምነትን እየተገበሩ ኖረዋል። በሌላ በኩል ራሳቸዉን ለማዳን በሌሎች አካባቢዎች ለስራ ሲዘዋወሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሃይማኖታቸዉን የቀየሩና ክርስትያን የሆኑ አሉ። እንደዉም እነዚህ ሰዎች «ፈላሻ ሙራ» ይባላሉ። እነዚህን ነዉ ንጹሕ አይሁዶች አይደሉም የሚሏቸዉ። ከአይሑድ እምነታቸዉ ወወደ ክርስትና ለዉጠu መልሰዉ ወደ አይሁድ እምነት ሲመለሱ ነዉ የአይሁድ እምነት የተቀየረ «ፈላሻ ሙራ» ይሏቸዋል። በዓለም ዙርያ ከሚገኙት ቤተ-እስራኤል ሁሉ ንጹሕ የአይሁድ ደም ያለዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ ተብሎ ይታመናል። »
በማኅበረሰብ ጥናት በብሪታንያ ኦክስፎርድ ዩንቨርስቲ ያጠናቀቁና ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዉ በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት በማስተማር ላይ የሚገኙት ፕሮፊሰር አበበ ዘገየ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ አይሁዳዉያን ወደ እስራኤል ለመሄድ ያለባቸዉ ፈተና ብሎም ከሄዱ በኋላ ስለሚገጥማቸዉ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን የሚያሳይ፤ ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት « THE IMPOSSIBLE RETURN» «የማይቻለዉ ምልሰት» ወይም «የማይቻለዉ መመለስ» አልያም «ከባዱ ምልሰት» እንደማለት ነዉ ፤ በእንጊሊዘኛ መጽሐፍ አሳትመዋል። ይኸዉ መጽሐፋቸዉ ወደ አማርኛ እየተተረጎመ እንደሆነም ተናግረዋል።
«ለመጽሐፉ ይህን ርዕስ የሰጠሁበት ምክንያት ቤተ- እስራኤላዉያኑ ከኢትዮጵያ ይመለሳሉ ብሎ ያሰበ ስላልነበረ ነዉ። በኢትዮጵያ ዉስጥ ክርስትና እስልምና እንዲሁም የአይሁድ እምነት ከጥንት ጀምሮ እጅግ የታወቁ እና አንድ ላይ ሆነዉ የሚታዩ ናቸዉ።
በሌላ ሃገራት ግን ይህ ሁኔታ የተለመደ አይደለም። በኢትዮጵያ ሦስቱም ሃይማኖቶች ማለትም የክርስትና የእስልምና እንዲሁም የአይሁድ እምነቶች የተሳሰሩ ናቸዉ። ማኅበረሰቡም አብሮ የሚኖር አብሮ የሚበላ አብሮ ባህሉን የሚተገብር ነዉ። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የሚገኙት ቤተ-እስራኤላዉያንም ሆነ የክርስትና እምነት ተከታዮች እስራኤልን እንደ ቅድስት ሃገር ስለሚቆጥሩ ሁሉም እስራኤልን የመርገጥ ህልም ነበራቸዉ፤ አላቸዉም። እና ይህን መጽሐፍ ስፅፍ እነሱ ቤተ- እስራኤል የሚያደርጋቸዉ  ኢትዮጵያዊነታቸዉ ብዬ  ነዉ ። ኢትዮጵያዊነታቸዉ ነዉ በጣም መታወቅ ያለበት። አሁንም ቢሆን ባይመለሱም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸዉ ግንኙነት መጠናከር አለበት። አለበለዝያ ቤተ-እስራኤል መሆን አይችሉም።»
ቤተ-እስራኤላዉያን ከኢትዮጵያ  ወደ እስራኤል ሲጓዙ ከ30 ዓመት በላይ ሆኖታል። እስካሁን  ከ 60 እስከ 70 ሺህ ቤተ-እስራኤላዉያን  እስራኤል መግባታቸዉ እንደሚገመት የተናገሩት አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸዉ እስራኤል ዉስጥ በአሁኑ ወቅት ወደ 110 ሺህ ቤተ- እስራኤላዉያን ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልፀዋል።
ቤተ-እስራኤላዉያኑ ወደ እስራኤል ሲሄዱ ለዓመታት ይኖሩበት የነበረዉ ቤታቸዉ የባህል ማእከላቸዉ አልያም የፀሎት ቤቶቻቸዉ ማለትም ሙክራቦቻቸዉ፤ ብሎም የሥራ እቃዎቻቸዉ በቅርስንነት ምን ያህል ጥበቃ ይደረግለት ይሆን። የቤተ- እስራኤላዉያንን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ መስፍን አሳፋ መልስ አላቸዉ።
« ምንም ጥበቃ አይደረግለትም።  ቤተ-እስራኤላዉያኑ በአብዛኛዉ ከጎንደር፤ ከሰሜን ወሎ እና ከደቡብ ትግራይ አካባቢ የሄዱ ናቸዉ። ስለዚህ ከሄዱባቸዉ አካባቢዎች ጠቅላላ የአይሁድን እምነት ኦሪታዊ ስርዓታቸዉን ተገለዉ በኖሩባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ያካሂዱ ስለነበር ሲወጡ ጥለዋቸዉ ነዉ የወጡት። ከዚያም በዚያዉ አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ቤተ- እስራኤላዉያን እና ቤተ እስራኤላዉያን ባልሆኑ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ቁሳቁሱ ግልጋሎት ላይ ይገኛል።

ለምሳሌ ከጎንደር ወጣ ብሎ በሚገኝ እነሱ በሚኖሩበት አካባቢ ላይ ሌሎች ቤተ-እስራኤላዉያን ያልሆኑ ማኅበረሰቦች እነሱ ይጠቀሙበት የነበረዉን መሳሪያ  በመገልገል እነሱ ይሰሩበት የነበሩትን የተለያዩ  መሳርያዎች ይገለገሉባቸዋል።
ፕሮፊሰር አበበ ዘገየ እስራኤል የሚኖሩት ከኢትዮጵያ የሄዱት አይሁዶች ቤተ እስራኤላዉያን የሚል ስያሜን ያገኙት ዋናዉ ምክንያት ከኢትዮጵያ በመሄዳቸዉ ነዉ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት አበክረዉ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የጺዎናዉያን ጉዳይ ተከታታይ የሆኑት አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላዉያን ከማኅበረሰቡም ሆነ ከመንግሥት ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ ጠይቀዋል። ቃለ-ምልልስ የሰጡን በ«DW» ስም በማመስገን ሙሉ ስርጭቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

Filed in: Amharic