>
5:14 pm - Friday April 30, 8094

የሰሞኑ ግድያ አንድምታና ሥጋቶች በአዴፓ አመራሮች አንደበት!!! (ከድር እንድርያስ)

የሰሞኑ ግድያ አንድምታና ሥጋቶች በአዴፓ አመራሮች አንደበት!!!
ከድር እንድርያስ
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ማንም ሊገምተው ያልቻለ ቅፅበታዊ ጥቃት የአማራ ክልልን በሚያስተዳድሩ አመራሮች ላይ ተከፍቶ የክልሉ ፕሬዚዳንት አምባቸው መኰንን (ዶ/ር)፣ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴና የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ በሥራ ላይ እንዳሉ ተገድለዋል፡፡
ግድያው ከተፈጸመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ባወጡት መግለጫ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት የክልሉ መንግሥት የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና በእሳቸው ተዋቅሮ የሚታዘዝ ቡድን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ግድያው በተፈጸመበት ወቅት በአሜሪካ ይገኙ የነበሩት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ የተገደሉት የፓርቲው አመራሮች ግብዓተ መሬት በተፈጸመበት ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ያደረጉት በሲቃ የተሞላ ንግግር ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ እንደነበሩ አመላካች ነበር፡፡
ለሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ከማቅናታቸው ከሰዓታት በፊት በተከፈተባቸው ድንገተኛ ጥቃት ሕይወታቸውን ካጡት ከሦስቱም አመራሮች ጋር በተከታታይ መከናወን ስላለባቸው ቀጣይ ሥራዎች፣ እንዲሁም በሚካሄደው የውጭ አገር ጉዞ ሊያከውኗቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ምክረ ሐሳቦችን በስልክ እንደተለዋወጡ አቶ ደመቀ  አስታውሰዋል፡፡
‹‹የሄድኩበት አገር ገና ከመድረሴ የተቀበልኩት የመጀመርያ የስልክ ጥሪ ግን ለማመን የሚከብድ፣ ሰውነትን በድንጋጤ የሚያርድ፣ ልብን በሐዘን የሚሰብር እኩይ መልዕከት የያዘ ነበር፤››  ሲሉ ሳግ በተቀላቀለበት የሐዘን ስሜት ገልጸዋል፡፡
ሞት ለሰው ልጅ የተለመደና ተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆንም ሁልጊዜም ግን አዲስ ሆኖ የቅርብ ሰዎችን እንደሚያሳዝን የተናገሩት የአዴፓ ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፣ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ክህደትን የተላበሰና የከፋ ጭካኔ ሲፈጸም፣ እጅግ መራርና ከአዲስም አዲስ ነው፤›› ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በአማራ ክልል ለመጣው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ለውጥ በግንባር ቀደምትነት ለታገሉ መሪዎች ምላሹ ጥይት መሆኑ እንቆልሽ እንደሆነባቸው፣ ድርጊቱም የእናት ጡት ነካሽነት ከማለት በስተቀር ሌላ ቃል ሊገልጸው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
አቶ ደመቀ ባደረጉት በዚህ ንግግር በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልሉ አመራሮች ይፋ ከተደረገው የገዳይ ማንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ምንም አላሉም፡፡
ከዚህ ዕለት በኋላም ቢሆን ግድያው የተፈጸመበትን ምክንያትና ዓላማ በተመለከተ ለሚመሩት ክልል ሕዝብም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለኅትመት እስከገባንበት ዓርብ አመሻሽ ድረስ ያሉት ነገር የለም፡፡
በጥይት የተገደሉት አመራሮች ግብዓተ መሬት በተፈጸመበት ዕለት ያስተላለፉት መልዕክት አመዛኙ ይዘት ግን፣ የግድያውን አንድምታ የተመለከተ ነበር፡፡
‹‹ጥቃቱ  በሕይወትና በማኅበራዊ ገጽታው ሲታይ በቤተሰቦቻቸውና በትግል አጋሮቻቸው ላይ የሚፈጥረው ሐዘን እጅግ የከበደ ቢሆንም፣ አንድምታው ግን ከዚህ እጅግ የጠለቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪክ የማይመጥንና በጭካኔ የታጀበ አረመኔያዊ ጥቃት መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ፣ ‹‹ድርጊቱ በአገራችን ከሥልጣንና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የነበሩ የመጠፋፋት ባህሎችን በአገር አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው ለውጥ ምክንያት ተሻግረናቸዋል ያልናቸውን ወደ ኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱንና እንደዚህ ዓይነት የመጠፋፋት ልማዶችን ሁሉም በፅናት ሊታገለውና ሊያወግዘው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚህ ዘመን የአገሪቱን ሕዝቦች ጥያቄዎች በመመለስ፣ የሕግ የበላይነትን በማስከበርና የኢኮኖሚ ማነቆዎችን በመፍታት ልማትን ለማፋጠን የሚቻልባቸው ብዙ ዕድሎች እያሉ፣ በተግባር ግን ከዕድሎቹና ከበጎው መንገድ በመራቅ የአገሪቱን ችግሮች ዕድሜ ማራዘም ላይ መገኘት እንደሚያሳስቸባውም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ አዙሪት ለመወጣት ከስሜታዊነት፣ ከጀብደኝነት፣ ከግለኝነትና ራስን ብቻ ከማዳመጥ መውጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
በአዴፓ አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ያስደነገጠ ብቻ ሳይሆን፣ ፖለቲከኞችንና ልሂቃንን መደናገር ውስጥ የከተተና ለተለያዩ የሴራ ትንተናዎች ያጋለጠ ስለመሆኑ ከሚሰጧቸው አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡
የግድያ ፈጻሚውን ቡድን አስመልክቶ በመንግሥት የተሰጡ መግለጫዎችን አምነው የተቀበሉ የመኖራቸውን ያህል፣ መግለጫውን ያልተቀበሉትም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህንን በተመለከተ ግድያው በተፈጸመበት ወቅት ሕይወታቸውን ካጡ አመራሮች ጋር ስብሰባ ላይ የነበሩ የአዴፓ ማዕካላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑ የክልሉ አመራሮች፣ ስለሁኔታው በክልሉ የብዙኃን መገናኛ ቀርበው አስረድተው ነበር፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው፣ የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ አብርሃም አለኸኝና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በጋራ በሰጡት ማብራሪያ፣ ከተገደሉት አመራሮች ጋር ስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት በድንገት ያልተለመደ የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ ማየታቸውን፣ ወደነበሩበት ክፍል ዘልቀውም በጥይት ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን ለማምለጥ ባደረጉት እንቅስቃሴም ግድያውን በማቀነባበርና በመምራት የተጠረጠሩትና በኋላም ለማምለጥ ሲሞክሩ መገደላቸው የተገለጸው የክልሉ የፀጥታና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው፣ የፀጥታ ኃይሎችን ግድያው በተፈጸመበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲያሰማሩ እንደተመለከቷቸው አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡
ግድያውን በማቀነባበርና በመምራት የተጠረጠሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው  ድርጊቱን ለመፈጸም ሊያነሳሳቸው የሚችል ሁኔታ ስለመኖሩ፣ ምናልባትም የተሰጣቸውን የክልሉን ፀጥታና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ቀደም ብሎ የተገመገመበት የአመራር ጉድለት ስለመኖሩ ተጠይቀውም ግለሰቡ ላይ ያነጣጠረ ጉድለት በግምገማ ላይ ፈጽሞ አለመኖሩን፣ ዘርፉን አስመልክቶ በቀደሙት ቀናት ግምገማዎች ተደርገው የነበረ ቢሆንም በፓርቲው መርህ መሠረት ግምገማዎች ግለሰብ ላይ እንደሚያተኩሩ፣ ይልቁንም ምን ታቅዶ ምን ጎደለ? ምን ተፈጸመ? ክፍተቱ እንዴት ይሞላ? በሚሉት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡
ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ድርጊቱን ለመፈጸም በምክንያትነት የሚጠቀስ ገፊ ምክንያት ከጥቃቱ በፊት በነበሩ ግምገማዎች አለመኖራቸውን፣ በግል በሚገናኙበት ወቅትም በግለሰቡ ላይ ምንም ዓይነት ቅሬታ ዓይተው እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡
ተጠርጣሪው ድርጊቱን ለመፈጸም የገፋቸው ምክንያት በእነዚህ አመራሮችም ሆነ በሌላ መንገድ፣ እንዲሁም በምርምራ እስካሁን አለመታወቁ የአገሪቱ ልሂቃንና ተራውን ማኅበረሰብን ጨምሮ በተለያዩ የሴራ ትንታኔዎችና ይህንን መሠረት ባደረጉ ጥርጣሬዎች እንዲጠመዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም በአዴፓ ውስጥም ሆነ በአማራ ክልል ብሎም በመላው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋት መደቀኑ ይነገራል፡፡
ይህንን የተረዱ የሚመስሉት ከግድያው የተረፉ የአዴፓ አመራሮች የክልሉ ሕዝብ ጥንቃቄ እንዲያደርግና እየቀረቡ ያሉ የተለያዩ አሉባልታዎችን ከመቀበል፣ ከመንግሥት የሚወጡ መረጃዎችን ብቻ እንዲያምን አሳስበዋል፡፡
የክልሉን የፀጥታ መዋቅር ለመከፋፈል የሚነዙ አሉባልታዎች መኖራቸውን በመግለጽ፣ ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰቡት አቶ መላኩ ናቸው፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ አብርሃም በበኩላቸው፣ የአማራ ሕዝብ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅና እንዲከፋፈል ለማድረግ የሚነዙ መረጃዎችና ጥረቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ ሁሉም የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በዚህ በከፋ ወቅት የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ብቻ እየሠሩ መሆኑን ሕዝቡ እንዲረዳና እምነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ደመቀ መኰንንም፣ በአመራሮቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ሥጋት የተረዱ ይመስላሉ፡፡
‹‹ከዚህ አዙሪት ለመውጣት ከስሜታዊነት፣ ከጀብደኝነትና ግለኝነት ወጥተን ወደ ከፍታ የሚወስዱን ጥበቦችን ማለትም ምክንያታዊነትን፣ በሌላው ጫማ ላይ ሆኖ ማሰብን፣ ሕግና ሥርዓትን፣ እንዲሁም አርቆ ተመልካችነትን መላበስ ይኖርብናል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ አኳያም የአማራ ሕዝብ አቃፊነቱን አጉልቶ በመላው ዓለም ላይ ጭምር ተከባብሮና ከፍ ብሎ የመኖር ባህሉን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው፣ ከዚህ ውጪ የሚራመዱ ሐሳቦችና አስተምህሮዎች ግን የአማራን ሕዝብ ከከፍታ የሚያወርደው መሆናቸውን በመገንዘብ በጥንቃቄ መመልከት እንደሚገባ አክለዋል፡፡
የሰሞኑን የአማራ ክልል ሁኔታን በተመለከተ ከአማራ መገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የተፈጸመውን ድርጊት በማውገዝ አሁን ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልገው ሰላም ማስፈን መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ሰላም ለማስፈን ደግሞ የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ከአሉባልታና ከተሳሳቱ መረጃዎች ራሱን በመጠበቅ ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል ከተፈጠረው አደጋ ጋር በተገናኘ 212 ተጠርጣሪዎች ትጥቃቸውን ፈትተው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ የፀጥታና የፍትሕ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባና በባህር ዳር የተፈጸሙ ጥቃቶች ግንኙነት እንዳላቸው ለማወቅ የሚደረገው ምርመራ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡
Filed in: Amharic