>
5:13 pm - Wednesday April 19, 3076

የአማራ ክልል በይፋ ባልታወጀ  ኮማንድ ፖስት ስር ወድቋል!!! (ነዋሪዎች - ለኢትዮ 360)

የአማራ ክልል በይፋ ባልታወጀ  ኮማንድ ፖስት ስር ወድቋል!!! -ነዋሪዎች
ኢትዮ 360 
የአማራ ክልል በይፋ ባልታወጀ ኮማንድ ፖስት ስር ወድቋል ሲሉ የክልሉ ነዋሪዎች ለኢትዮ 360 ገለጹ።
ይህንን ተከትሎም በክልሉ ተወላጆች በተለይም በወጣቱ ላይ የሚደርሰው አፈና፡ማሳደድና ማሰር ተጠናክሮ ቀጥሏል።
እንዲህ አይነቱ ተግባር ደግሞ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲሉ የክልሉ ነዋሪዎች ያሳስባሉ
ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 እንዳደረሱት መረጃ ከሆነ ማን አዛዥና ማን ታዛዥ እንደሆነ በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቿ በተለይም ወጣቱ እየተሳደደ ነው ያለው ።
እነሱ እንደሚሉት የአማራ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅኑ በሙሉ እየተሳደዱ በመታሰር ላይ ናቸው።ግማሾችም አካባቢያቸውን ጥለው ወደ ጫካ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።
ክልሉን ይመራል የሚባለው አዴፓ በክልሉ ነዋሪዎችና በወጣቱ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ስላለው ግፍ ምንም ያለው ነገር የለም ይላሉ ነዋሪዎቹ ።
በአጠቃላይ ክልሉ በይፋ ባልታወጀ ኮማንድ ፖስት ስር ወድቋል ሲሉም በእርግጠኝነት ይናገራሉ።
የክልሉ ሕዝብ የቁርጥ ቀን የሚባሉና ስለመብቱ የሚከራከሩለትን መሪዎቹን ባጣ ማግስት በክልሉ ነዋሪዎች በተለይም በወጣቱ ላይ እየደረሰ ያለውን የአደባባይ ግፍና በደል አዴፓ መብቱን ተጠቅሞ ሊከላከልለት አልቻለም ብለዋል ለኢትዮ 360 ድምጻቸውን ያሰሙት ነዋሪዎች።
የሃይማኖት አባቶች የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎች አካላት አውግዙ ሲባሉ ማውገዝ እንጂ ስለእውነት ቆመው ለክልሉ ተወላጆች ሲከራከሩ አይታይም።- ይሄ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ነው ይላሉ።
የሌላ ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ ክልሉ የራሱን ችግር ከራሱ ህዝብ ጋር መክሮ ይፈታል የሚል አካልን ማግኘት አልተቻለም ሲሉም ይወቅሳሉ።
እነሱ እንደሚሉት ሃገሪቱን አስተዳድራለሁ የሚለው አካል የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጉ ደግሞ መረጃ የማግኘት መብታችንን ከመግፈፉም ባለፈ በክልሉ እየተፈጸመ ላለው ኢሰብአዊ ደርጊት ተባባሪ ሆኗል።
መንግስት ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝ ማፈኑ የተፈጠሩትን ሁኔታዎች ከማርገብ ይልቅ በውሸት መረጃ ሃገር እንድትበጠበጥ አድርጓል ሲሉም ከሰዋል።
ከክልሉ አልፎም በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች አማራ በመሆናቸው ብቻ ለከፋ አደጋ ተጋልጠዋል ብለዋል::
በሱሉልታ ብቻ 20 የሚሆኑ ባለሃብቶች አማራ በመሆናቸው ብቻ ለእስር መዳረጋቸውን በማሳያነት ያቀርባሉ።
በሌሎች አካባቢዎች የሚፈጸመው ድርጊትም ተመሳሳይ ነው ይላሉ።
አዴፓ እንደ አዴፓ መስማት የሚችል ከሆነ በክልሉ በህገወጥ መንገድ የገባውን የፌደራል ሃይል በ24 ሰአት ውስጥ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ያድርግ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ በተለይ በወጣቱ ላይ የሚደርሰውን ማሳደድና እስር እንዲቆም ስልጣኑን ይጠቀም የአማራ ህዝብ የቁርጥ ቀን አመራር መሆኑን ያስመስክር የአማራ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅኑ አካላት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ያውግዝ የሚሉና ሌሎች ለአዴፓ የአስቸኳይ ጊዜ የቤት ስራ ነው ያሏቸውን ጥያቄዎችም አቅርበዋል።
ኢትዮ 360ም የነዋሪዎቹን ጥያቄ ይዞ ወደ ሚመለከታቸው የክልሉ አመራሮች ያደረገው የስልክ ጥሪ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም።
Filed in: Amharic