>

ህገ-መንግስቱ አይነካ" ወይም "ህገ-መንግስቱ ጥቅሜን አይወክልም" የሚሉ ሃይሎች ዋልታ ረገጥ ናቸው!!!”- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 

ህገ-መንግስቱ አይነካ” ወይም “ህገ-መንግስቱ ጥቅሜን አይወክልም” የሚሉ ሃይሎች ዋልታ ረገጥ ናቸው!!!”-
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ 
(ኢ.ፕ.ድ)
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህገመንግስቱን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ጥያቄ የኢፌዴሪ ህገመንግስትን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት በአንድ በኩል ህገመንግስቱ ከተነካ ሀገር ትፈርሳለች የሚሉ በሌላ በኩል ደግሞ ህገመንግስቱ አካታች አይደለም ሊሻሻል ይገባል የሚሉ አሉ፤ በዚህ ዙሪያ የመንግስት አቋም ምንድን ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድም በምላሻቸው ህገመንግስቱን በተመለከተ “አይነካ ወይም ህገመንግስት ጥቅሜን አይወክልም” የሚሉ ሃይሎች ዋልታ ረገጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ህገመንግስት በህዝብና በመንግስት መካከል የሚደረግ ኪዳን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሚደረጉ ለውጦች ካሉ እነሱን ተቋማዊ የሚያደርግ ሰነድ እንደሆነም ነው ያነሱት።
ህገመንግስቱ በሂደት የሚታዩ ለውጦችን ለማስተናገድ እንደሚሻሻል በራሱ አንቀጽ ያካተተ ሆኖ ሳለ ሊነካ አይገባም ማለት እና በህገመንግስቱ የተካተቱ መብቶችን ሙሉ ለሙሉ በመካድ አይወክለኝም የሚሉ አቋሞች ተገቢ እንዳልሆኑ ነው ያነሱት።
ህገመንግስቱ ያጎናፀፋቸውን መብቶች ተቀብለን ይህኛው ቢሻሻል የሚል ሀሳብ ማንሳት ችግር እንደሌለው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉንም በሚዛናዊነት ማየት ይገባል ብለዋል።
ህገመንግስቱ “ይሻሻል እና አይሻሻልም” የሚሉ አካላት ችግራቸው ዋልታ ረገጥ አቋም ይዘው መነሳታቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
“እንዲሻሻል የሚፈልግ አካል ለአንድ ቀበሌ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ህዝብ ሊሆን የሚችል የማሻሻያ ሀሳብን ማቅረብ ይገባል።” ነው ያሉት
“በቡራ ከረዮ ህገመንግስት አይነካም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳማኝ የሆኑ ሀሳቦችን በማንሳት ድንጋጌዎች እንዲሻሻሉ መጠየቅ እንደሚቻል ነው ያነሱት።
በሌላ በኩል ግን የህገመንግስት ማሻሻያ ሀሳብ ሲነሳ የሚደነግጡ አካላትም አካሄዳቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በዓለም ላይ የተጻፈና ያልተጻፈ ህገመንግስቶች እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደ እስራኤል ያሉ ሀገራትም ባለ አንድ ገፅ ህግመንግስት አላቸው ብለዋል።
ህገመንግስት በማሻሻል ረገድም እነ አሜሪካ፣ ህንድ፣ እነ ኮሪያ ብዘ ጊዜ ጥሩ ልምድ እንዳላቸው ያነሱ ሲሆን የኢፌዴሪ ህገመንግስት ለመሻሻል በሩ ክፍት እነደሆነ ነው ያነሱት።
ነገር ግን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ የሚያግባባ ህገመንግስት ማዘጋጀት እንደማይቻል አንስተው የተለያዩ ፍላጎቶችን እና ሀሳቦችን አካታች ማድረግም ዴሞክራሲያዊነት መሆኑን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
Filed in: Amharic