>
5:13 pm - Friday April 19, 7907

መርታት፤ መረታት፤ መገገም!!! (በእውቀቱ ስዩም)

መርታት፤ መረታት፤ መገገም!!!
በእውቀቱ ስዩም
የሆነ ጊዜ ላይ  ረከቦት ጎዳና፤ ባንዱ ካፌ ውስጥ፤ ቡን ስጠጣ፤አንድ ጎረምሳ ወደ ተቀመጥኩበት መጣ፤ልጁ ግድንግድ ነው፤ጎልያድ ዳዊትን አዝሎ ያክላል፤  እኔ ደሞ እንደምታውቁኝ ነኝ፤ከፊቴ ሲቀመጥ የሚጥሚጣ ብልቃጥ አከልኩ፤ ግብዳው ብዙ ሳይቆይ የምነት ክርክር ጀመረ፤በተቻለኝ መጠን ወደ ክርክሩ ላለመግባት ተግደረደርኩ፤ ሰውየው ግን  አልከራከርም ብለው ንቀኸኝ ነው ብሎ  ሊደበድበኝ ይችላል፤ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ የነደደ ክርክር ውስጥ ራሴን አገኘሁት፤ሰውየው አረፋ እየደፈቀ ተተጋተገኝ፤
ጎረርህ በሉኝ ብትፈልጉ ! አስር ቀቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ልጁን መፈናፈኛ አሳጣሁት፤ መግብዳው  ክርክክራችንን ያሳረገው እንዲግ በሚል ቃል ነው፤
“‘ ልታሳምነኝ አትድከም ! እገግምብሃለሁ”
አሁን ሳስበው፤  አስተምረዋለሁ ያልሁት  ያ ግብዳ ሰውየ ትልቅ ቁምነገር አስተምሮኛል ፤ ባፍለኝነቴ ፤የሰው ልጆች ለሀቅ  እና ለምክንያታዊነት የሚኖሩና የሚሞቱ  ይመስለኝ ነበር፤ሰዎች በውይይት የሚያምኑ ይመስለኝ ነበር፤ አዋቂ ባላዋቂ ላይ የሚበረታ፤፤ እውነት የያዘ ሰው ሀሰተኛውን የሚረታ  ይመስለኝ ነበር፤ እየኖርኩ ስሄድ ይሄ እምነቴ ጥሎኝ ሲመንን ታዘብኩት፤ አብዛኛው ሰው ለውነት ደንታ የለውም፤ አብዛኛው ሰው፤ ስለ እውቀት ስለተጨባጭ መረጃ ግድ አይሰጠውም፤  በተፈጥሮ ይሁን በልማድ እንጃ፤ አብዛኛው ሰው ችኮ መንቻኮ ነው፤ ልብ አድርቅ ነው፤ የውይይት አላማ ከላይ ከላይ የእውቀት ልውውጥ ቢመስልም ውስጥ ውስጡን መሸናነፍ ነው ፤ሽንፈት መራራ ፍሬ በሚያስለቅምበት አገር ውስጥ ደሞ፤  ማንም መሸነፍ አይፈቅድም፤ ብታሸንፈው ተሸነፍኩ አይልህም፤ ተዘርሮም ይፎክርብሃል! ይገግምብሃል!
ቀኛማች በላይነህ የተባሉ ባላባት በዳግማይ ምኒልክ ጊዜ  ነበሩ፤በዘመናቸው፤  ከስራቸው ጋራ የማይመጣጠን አንጀባ ስለሚያበዙ ” ቁንን  በላይነህ”  የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቱዋቸው ነበር፤የሆነ ጊዜ ላይ ከሸገር ወደ ጎንደር ይሄዱና ባንድ ደብር ውስጥ  ይስተናገዳሉ፤ቁንን በላይነህ ፊደል ያልቆጠሩ ጨዋ ቢሆኑም  በሊቃውንቱ ፊት የተማሩ ለምምሰል ተጋጋጡ፤  ዳዊት እየደገምኩ ነው ለማለት ዳዊት ገለጡ፤ ግን የማያውቁትን ዳዊት  ገልብጠውት ነበር የያዙት፤
ይህንን የሾፈ  አንድ ደብተራ ሳቁን በጋቢው ለመጨቆን እየሞከረ፤
“ጌቶች ዳዊቱን ዘቅዝቀው  ነው የያዙት” ቢላቸው፤
))“ጠላቴን እንዲዘቀዝቅልኝ  ብየ ነው! ጠፍቶኝ እንዳይመስልህ ” አሉት ይባላል፤
ቁንን በላይነህ አላዋቂ ናቸው፤ግን አላዋቂነታቸውን አምነው ማረም አይፈልጉም፤ ማንን ደሰ ይበለው ብለው!?ተሸንፈው፤አሸናፊ መስለው ቆመዋል! ገግመዋል!
ታዋቂው የታሪክ ፀሀፊ ተክለፃድቅ መኩርያ በግለታሪካቸው ላይ አንዲት ገጠመኝ ጠቅሰዋል፤ ገጠመኚቱን በኔ አማርኛ ሸክሽኬ ሳቀርባት ይቺን ትመስላለች፤ የሃይለስላሴ ባለስልጣኖች በደርግ ወጣት መኮንኖች እየተለቀሙ በሚታጎሩበት ቀውጢ ወቅት ፤ ሁለት ወጣት ታጣቂዎች ተክለፃድቅ ቤት ድረስ ይመጡና በቁጥጥር ስር ያውሉዋቸዋል፤ በገዛ መኪናቸው፤ይዘዋቸው በሚሄዱበት ጊዜ አንዱ ታጣቂ ለጉዋደኛው_-_
“ከተማ ይፍሩ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት  አስር ሚሊዮን ብር በኪሱ ተገኘ” ይላል፤(ከተማ ይፍሩ የዘመኑ ባለስልጣን ነው)
“ይሄን የሚያክል ገንዘብ በኪስ ሊያዝ አይችልም” አሉ ተማራኪው ተክለፃድቅ፤
“ባይኔ በብረቱ ያየሁትን” አለ ወታደሩ፤
“ይህን ጊዜ” ይላሉ ተክለፃድቅ መኩርያ “ ይህን ጊዜ ዝም አልኩ፤”
ዝም ባይሉ ኖሮስ?
ታጣቂው ይገግማል!
 ጠመንጃውም ያስገመግማል፤
አስከሬን ይለቀማል
እና  ይሄ ማን ይጠቀማል?
 አንዳንዴ በፌስቡክ ማለቂያ አልባ ክርክር ውስጥ ዘልየ ለመግባት ሲቃጣኝ እኒህን ነገሮች አስታውሳለሁ፤አንዳንዴ ዝም አልክ ማለት እውነቱን ከመናገር ተቆጠብክ ማለት አይደለም፤ሃይልህን ቆጠብክ፤ሰላምህን ቆጠብክ፤ ህይወትህን ቆጠብክ ማለት ነው፤
Filed in: Amharic