>

ቁጣን ምን አመጣው? (ዶ/ር ሰማህኝ ጋሹ)

ቁጣን ምን አመጣው?
ዶ/ር ሰማህኝ ጋሹ
ጠ/ሚኒስትር አብይ ዛሬ በተናገሩት አንድ ነገር እስማማለሁ። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ የማይታሰብ ነዉ። ወያኔ ከመጣ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ ብሄር ጋር ስለሚያያዝ ባላፈዉ ወታደሮች ቤተ መንግስት በመጡበት ወቅት ጠ/ሚኒስትር አብይ እንደገለፁት ‘ መንግስቴ ተገለበጠ ብለዉ ሰዎች ከሰበታና ቡራዩ ሊመጡ ነበር’ ። ስለዚህ ስልጣን በዘር በሚከፋፈልበት አገር መፈንቅለ መንግስት የሚሳካበት እድል ዝቅተኛ ነዉ። ይህ ያስማማናል። ነገር ግን በአለፈዉ አንድ አመት ያጋጠመዎትን ተቃውሞ ሁሉ እንደ መፈንቅለ መንግስት አድርገው ማቅረብዎ የሚከሰቱ ነገሮችን እንዴት እንደሚመለከቱ ጥሩ ፍንጭ የሚሰጥ ነዉ። በተለይ የመምህራን የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ እንዴት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሊሆን እንደሚችል እግዜር ይወቅ።
እርስዎ  ሊሸጡልን የፈለጉትን ‘የመፈንቅለ መንግስት’ ትርክት ባላመግዛታችን ለምን እንደሚቆጡን አልገባኝም። በነፃ ገበያ የመግዛትም ያአመግዛትም ነገር የመብት ጉዳይ በመሆኑ ምንም የሚያስቆጣ ነገር የለዉም። በደረቅ ሌሊት ብቅ ብለዉ መፈንቅለ መንግስት ተደረገብኝ ያሉት ነገር ከመፈንቅለ መንግስት ይልቅ የባለ ስልጣን ግድያ መሆኑ ግልፅ ሆንዋል። የባህር ዳሩና አዲስ አበባዉ ግድያ እንደሚገናኝ በነገሩን አንደበትዎ በነጋታዉ ሁለቱ ጉዳዮች ስለመገኛኘታቸዉ እርግጠኛ አይደለንም ሲል መንግስትዎ ነግሮናል። ጄኔራል ሰአረን የገደለዉ ግለሰብ ሞትና ትንሳኤ ጉዳይ በራሱ ብዙ ጥያቅ ያስነሳ መሆኑ ይጠፋዎታል  ተብሎ አይታሰብም። ከዚህም በተጨማሪ ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ሰዎች እየታሰሩ እንደሆነ ይታወቃል።
እነዚህን ጉዳዮች በዝርዝር ሳያነሱ በደፈናው እንዴት አልታመንም የሚል ቁጣ የተቀላቀለበት ንግግር አድርገዋል። በእርስዎ ቁጣ የሚደናገጥና የሚፈራ  ሰዉ ያለ አይመስለኝም።
ለመንግስቱ ሃይለማርያምንና መለስ ዜናዊን ቁጣ ያልተበገረ ህዝብ የእርስዎ ቁጣ ያስበረግገዋል ብለው አስበዉ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነዉ። ይልቁንም ቅንነቱ ቢኖርዎት ኖሮ ጥርጣሬዉ ተገቢ መሆኑን ገልፀዉ  አጠራጣሪ ያደረጉትን  ጉዳዮች አንስተዉ መልስ ይሰጡ ነበር። ነገር ግን በደፈናዉ መንግስትዎ እንደሚያጣራው ነግረዉን ጉዳዩን አልፈዉታል ። የእርስዎ መንግስት አጣርቶ የሚያቀርበዉ የምርመራ ዉጤት ግን ገዥ አጥቶ ጥንቡል እንገሚጥል ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም። እዉነት እንደተናገሩት እዉነት ከእርስዎ ጋር ካለችና የእዉነት አምላክ እንዲፈርድ ከፈለጉ እጅዎን ከዚህ ምርመራ ላይ አንስተዉ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ያድርጉ።
Filed in: Amharic