>
12:56 am - Thursday December 1, 2022

ኸርማን ኮኸን፣ የፕሮቻዝካ ደቀመዝሙር (መስፍን አረጋ)

ኸርማን ኮኸን፣ የፕሮቻዝካ ደቀመዝሙር

ኸርማን ኮኸንና ሌሎች ፀራማራ
አደነቁኝ ብለህ ኦሮሞ አትኩራራ፡፡
የነጭ ዘረኞች የአሕዛብ ጎራ
የሚጸየፉትን እያሉ አሞራ
ሊበሉት ሲያስቡ ይሉታል ዥግራ፡፡

 

መስፍን አረጋ

 

ኸርማን ኮኸን

የዚህ ጦማር ዋና ትኩረት ስለሆነው ስለ ሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) ከማውሳቴ በፊት አሜሪቃዊ ይሁዳዊው ኸርማን ኮኸን (Herman Cohen) የባሕርዳሩን ክስተት በተመለከተ ስለ ሰጠው አስተያየት ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ፡፡
”Faild coup in #Ethiopia’s Amhara state was an attempt by ethnic nationalists to restore Amhara hegemony over all of Ethiopia that existed for several centuries prior to 1991. That dream is now permanently dead.”

‹‹ባማራ ክልል ውስጥ የተካሄደው ያልተሳካው የመንግሥት ግልበጣ (ወያኔ ጦቢያን እስከተቆጠረበት) እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ለምዕተ ዓመታት ሰፍኖ የነበረውን ያማራ የበላይነት ለማስመለስ ያማራ ብሔርተኞች ያደረጉት ሙከራ ነው፡፡ ይህ ህልማቸው ለዘለዓለም አሸለበ፡፡››

አለቅጥ መረን ተለቆ እልፍ አእላፋትን የጨፈጨፈውና ያፈናቀለው የኦነግ ብሔርተኝነት ቅንጣት ሳያሳስበው ያማራ ብሔርተኝነት ያሰጋኛል ያለው ዐብይ አሕመድ ባሕርዳር ላይ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ባካሄደው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ተጎናጽፏል፡፡ በብርሃኑ ጁላ የሚመራው የኦነግ ጦር በመላው አማራ ላይ ተሰራጭቶ ያማራን ቁልፍ ተቋሞች የሚያፈራርሰውና ዓይነተኛ ልጆቿን የሚጨፈጭፍው ይህ ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ባቀዳጀው ወታደራዊ የበላይነት ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ይህን ወታደራዊ የበላይነት በመጠቀም የወያኔ ተለጣፊ የነበረውን ብአዴንን የኦነግ ሙጫ እንዳደረገው ድርጅቱ ሰኔ 22፣ 2019 በሰጠው እጅግ አሳፋሪ መግለጫ ግልጽ ሁኗል፡፡

ዐብይ አህመድ ባሕርዳር ላይ የተቀዳጀው ወታደራዊ ድል ባሸብራቂነቱ ግራኝ አህመድ ሽምብራቁሬ (ማለትም የሽንብራ ቁሬ ወይም ያሁኒቷ ዱከም) ላይ ከተቀዳጀው ድል ቢልቅ እንጅ አያንስም፡፡ ሁለቱም ወታደራዊ ድሎች ለኦሮሞ ተስፋፊ ሰፊ በር የከፈቱ ታላላቅ ድሎች ናቸው፡፡ ወሳኙ ነጥብ ግን ዐብይ አህመድ የተቀዳጀው ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ሳይሆን፣ ወታደራዊ ድሉ ያደረሰበትና እያደረሰበት ያለው ከፍተኛ ፖለቲካዊ ኪሳራ ነው፡፡

ዐብይ አህመድ የኦነግን ዓላማ ለማሳካት የሚያደርገው ጉዞ እኩይ በመሆኑ ምክኒያት ያቀበት ጉዞ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ እስከ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ድረስ ዐብይ አህመድ እኩይ ያቀበት ጉዞውን የሚጓዘው በጥድፈት (acceleration) (ማለትም እየጨመረ በሚሄድ ፍጥነት) ነበር፡፡ ጉዞውን በጥድፈት እንዲጓዝ ያስቻሉት ደግሞ በቅቤ አፉ የደለላቸው ጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ አማሮች) ነበሩ፡፡

ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ግን ዐብይ አህመድ ክንብንቡን ራሱ በራሱ አውልቆ ፀራማራ መሆኑን በግልጽ ስላሳየ፣ አማሮች ፊታቸውን መቸም ላይመልሱ አዞሩበት፡፡ ከዚች ዕለት በኋላ ዐብይ አህመድ በመረጠው እኩይ የአቀበት መንገድ የተጓዘውና የሚጓዘው በዝግመት (deceleration) (ማለትም እየቀነሰ በሚሄድ ፍጥነት) ሆነ፡፡ ባለበት ያልቆመውም አማሮች በለገሱት ከፍተኛ ድጋፍ አማካኝነት የገነባው ከፍተኛ ሴቹማ (momentm) ማለትም እንድርድረት ወደፊት ስለሚገፋው ብቻ ነበር፡፡ ይህን ዓይነት ያቀበት ጉዞ ደግሞ እንድርድረቱ ሊገፋው እስከሚችለው መልዕል ነጥብ (maximum point) ያሻቅብና ፣ ቀኝ ኋላ ዙሮ ዝቅዝቅ በመምዘግዘግ ድባቅ ይገባል፡፡

ስለዚህም የሰኔ 15 ትርጉም ኸርማን ኮኸን የሚመኘውን ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ ዕለት ያማራ ብሔርተኝነት ለኻቹ የሞተበት ዕለት ሳይሆን፣ የፀራማራው ዐብይ ውድቀት የባተበት ዕለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ሰኔ 15 ለዐብይ አህመድ የመጨረሻው መጀመርያ ዕለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ አማራን የሚያስጨፈጭፈው ዐብይ አህመድ ይሁዳወችን (የኸርማን ኮኸን ዘመዶችን) ካስጨፈጨፈፈው ኤዶልፍ ሂትለር ጋር ይመሳሰላል፡፡

ፈረንሳይን፣ ቸኮስላቫኪያንና ፖላንድን በቀላሉ ስለተቆጣጠረ በወታደራዊ ድሉ የተኩራራው ሂትለር፣ ውድቀቱ ሀ ብሎ የጀመረው ወታደራዊ ድሉን ምሉዕ (complete) ለማድረግ በማሰብ ራሺያን በወረረበት ዕለት ነበር፡፡ ከዚያች ዕለት በኋላ እስቀድሞ ባካበተው እንድርድረት ብቻ እየተገፋ በመገስገስ የራሽያን ተቋሟት እያፈራረሰና ሕዝቦቿን እየጨፈጨፈ ከራሽያ ዋና ከተማ ዳርቻ ቢደርስም፣ ወዲያውኑ ቀኝ ኋላ በመሸምጠጥ እገዛ ራሱ ዋና ከተማ በርሊን ላይ ተከሰከሰ፡፡

ሱማሌንና ደቡብ ክልልን ስለተቆጣጠረ በወታደራዊ ድሉ የታበየው ዐብይ አህመድም፣ ወደ ሞቱ ማዘገሙን የጀመረው የኦነግን የበላይነት ምሉዕ ለማድረግ ያማራን ክልል በወረረበት ዕለት ነው፡፡ እንደ አጀማመሩ ቢቀጥል የጦቢያ ዕድሜ ልክ መሪ ለመሆን ሰፊ እድል የነበረው ዐብይ አህመድ፣ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሞን አጼጌ (oromo empire) መሥርቸ የመጀመርያው አጼ እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ እጅግ በጣም ተሳስቷል፡፡ እሱ ጦቢያውያንን በጀርባቸው እንደወጋ፣ ለማ መገርሳም እሱን በማጅራቱ ያርደዋል፡፡ ዐብይ አህመድ ግማሽ አማራ ስለሆነ፣ የተፈለገው አማሮችን እያታለለ የኦሮሞን አጼጌ ምሥረታ ሊቀለበስ ከማይችልበት ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንዲያደርስ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ሊታመን የማይችል ግማሽ አማራ በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ቲም ለማ ባፋጣኝ ያቀዘቅዘዋል፡፡ ይህ ደግሞ የዐብይ አህመድ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የግማሽ ኦሮሞ ጽንፈኞች አይቀሬ ፈኒማ (inevitable fate) ነው፡፡ ፀጋየ አራርሳ፣ ሰማኸኝ?

ለኔ እንደሚመስለኝ ጥድፊያ መለያ ባሕሪው የሆነው ስግብግቡ የኦነግ ጅብ ቸኩሎ ቀንድ ነክሷል፡፡ ለማ መገርሳ አማራን አስተኛለሁ ብሎ በነ ዶ/ር አምባቸው ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ሐበሻን ቀስቅሷል፡፡ ስለዚህም ዐብይ አህመድ፣ ፀጋየ አራርሳና መሰሎቻቸው የቲም ለማ ምሳ ከመሆናቸው በፊት የሣልሳዊ ምኒሊክ ቁርስ የመሆናቸው እድል የሰፋ ነው፡፡

ኦነግ ወታደራዊ ድል ቢጎናጸፍም፣ ፖለቲካዊ ሽንፈት ተጎንጭቷል፡፡ ወታደራዊ ሽንፈት የሥጋ ሽንፈት ስለሆነ ሁኔታወች ሲመቻቹለት በቀላሉ ያገግማል፡፡ ፖለቲካዊ ሽንፈት ግን የመንፈስ ሽንፈት በመሆኑ ሳይገል አይለቅም፡፡ ኸሐሀሃናፖሊዮን ቦናፓርት (Napoleaon Bonapart) በግልጽ እንዳስቀመጠው ‹‹ባለም ላይ ያለት ኃይሎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ሰይፍና መንፈስ ናቸው፡፡ የመጨረሻው ድል ደግሞ ሁልጊዜም የመንፈስ ነው፡፡›› (There are only two forces in the world, the sword and the spirit. In the long run the sword will always be conquered by the spirit).

ሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም ሀ ብሎ የጀመረውን የዐብይ አህመድን ውድቀት ለማፋጠን ሙሉ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን በዐብይ እኩይ መንገድ ላይ የምናስቀምጣቸውን መሰናክሎች በማብዛትና በማጠናከር ላይ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በማያከራክሩ ጉዳዮች ላይ በመከራከር ጊዜያችንን ማጥፋት የሚጠቅመው ለኦነጋውያን ብቻ ነው፡፡ ርስበርሱ የሚጣረሰው የቲም ለማ የመረጃ ግንብ ራሱ በራሱ ይፈራርሳል፡፡ የተለያዩ ሐሳዊ ምስክሮችን ማቅረብና በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ የተለያዩ ንግግሮችን አሰባስቦ መቀጣጠል፣ ትርፉ አወዳደቅን ማክፋትና ማፋጠን ብቻ ነው፡፡

 

ሮማን ፕሮቻዝካ

ሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) ጥቁሩ አደጋ (die Schwarze Gefahr) የተሰኘውን መጽሐፍ ከዘጠና አመታት በፊት (1929 ዓ. ም) በጀርመንኛ የጻፈ፣ በታላቁ የጥቁሮች ድል አንጀቱ የቆሰለ ነምሳዊ (Austro-Hungarian Empire) የናዚ ባላባት (baron) ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ በጣልያንኛ አደገኛዋ ጥቁሯ ጦቢያ (Abissinia pericolo nero) በሚል ርዕስ የተተረጎመ ሲሆን፣ Abissinia: The Powder Barrel የሚለውን የእንግሊዘኛ ትርጉም ደግሞ ደበበ እሸቱ ጦቢያ፣ የባሩድ በርሜል በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ መልሶታል፡፡ የመጽሐፉ ፍሬ ሐሳብ ደግሞ በጥቁርነታቸው የሚኮሩት የጥቁሮች አገር ጦቢያ፣ ለነጭ ዘር መቅሰፍት ስለሆነች፣ ባገር በቀል ጎጠኞች ተጎጥጉጣ መገነጣጠል አለባት የሚለው ነው፡፡

The numerous tribes who inhabit the Ethiopian state are being forcibly kept from European colonialism by Abyssinian rulers whose aim is to act as champions of all black people so as to attack and destroy Western culture
የጦቢያ አያሌ ብሔረሰቦች የነጭ ባርያ የመሆን ምርጫቸውን የነፈጓቸው መሠረታዊ ዓላማቸው በነጭ ተጽእኖ መቃብር ላይ የጥቁርን ልዕልና መገንባት የሆነው የሐበሻ መሪወች ናቸው፡፡
Roman Prochazka (Abyssinia: The Powder Barrel, Vienna, 1935)

ምዕራባውያን ዘረኞች በተለይም ደግሞ ለጥቁር ሕዝብ የጋቱትን እንቆቆ ወር ተራቸው ደርሶ እንዳይጋቱ እጅጉን የሚሰጉት አሜሪቃኖችና እንግሊዞች ጦቢያን በተመለከተ ማናቸውንም ፖሊሲ (policy) የሚቀርጹት የፕሮቻዝካን መሠረታዊ ሐሳብ በመንተራስ ነው፡፡ በሌላ አባባል እነዚህ ዘረኞች ጦቢያን በተመለከተ ማናቸውንም ድርጊት የሚያደርጉት ድርጊቱ ከፕሮቻዝካ ሐሳብ ጋር የሚጣጣም እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ምዕራባውያን ለጦቢያ የሚያደርጓቸው ድጋፍ፣ እርዳታ፣ ብድር ወዘተ. መታየት ያለባቸው በዚህና በዚህ መነጽር ብቻ ነው፡፡

በምዕራባውያን ባህል ነጻ ምሳ (free lunch) የለም፣ በተለይም ደግሞ ለጥቁሮች፡፡ ለጦቢያውያን ለሚያቀርቡት የተበላሸ ወይም ሊበላሽ የተቃረበ መናኛ ምሳ የሚጠይቁት ክፍያ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን፣ እሱም የጦቢያውያንን ማንነትና እንድነት ነው፡፡ የራሳቸውን ሕዝብ ራስህን ለማንነትህና ላንድነትህ ሰዋ እያሉ፣ የጦቢያን ሕዝብ ግን ማንነትህንና አንድነትህን ለራስ ሰዋ ይሉታል፡፡

የመላው ዓለም ጥቁሮች ነጭን ድል ባደረገችው በጦቢያ ከመኩራት ይልቅ እንዲያፍሩባትና የነጭን የበላይነት በጸጋ እንዲቀበሉ፣ ጦቢያን አሳፋሪ ለማድረግ ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ በጥቁርነታቸው እየኮሩ የጦቢያን ጥቅም የሚያስቀድሙ አገር ወዳድ ጦቢያውያን ስልጣን እንዳይዙ፣ ከያዙም እንዳይቆዩ፣ ከቆዩም ሰላም አግኝተው ዓላማቸውን እንዳያሳኩ \መጋረጥ\ የሚችሉትን ጋሬጣ ሁሉ ይጋርጣሉ፡፡ መለስ ዜናዊን የመሰለ የነጭ ቡችላ ሲያገኙ ደግሞ ቡችላውን ባስፈላጊው ዘዴ የይስሙላ ስልጣን አስጨብጠው፣ ቡችላነቱን እስከቀጠለ ወይም ደግሞ ከሱ የተሻለ ቡችላ እስከተገኘ ድረስ ስልጣኑ እንዲቀጥል የቻሉትን ሁሉ ይፈጽማሉ፡፡ የኦነጉ መለስ ዜናዊ ደግሞ ከወያኔው መለስ ዜናዊ ጋር በስልት ባዕድ ቢሆንም ባላማ አንድ የሆነው ዐብይ አህመድ ነው፡፡

ባፍ መፍቻ ቋንቋው ባማረኛ መናገር እስከሚያሸማቅቀው ድረስ የዝቅተኝነት ስሜት ክፉኛ የተጫወተበት ዋለልኝ መኮንን ‹‹በእንተ ብሔራተሰብ ጦቢያ›› (On the question of ethopian nationalities) የተሰኘውን ጦማር በ 1962 ዓ.ም የጦመረው የፕሮቻዝካን ሐሳብ በመኮረጅ ነበር እስከሚያስብል ድረስ በማንጸባረቅ ነበር፡፡ ወያኔ የገበረተው (apply)፣ ኦነግም ሊገበርተው የተነሳው ይህንኑ የፕሮቻዝካን ሐሳብ ነው፡፡ በሌላ አባባል፣ ዋለልኝ፣ ወያኔ፣ ኦነግ፣ ሻቢያና ሌሎቹም የጎጠኞች፣ የፕሮቻዝካን ህልም እውን ለማድረግ የተፈጠሩ የፕሮቻዝካ የሐሳብ ልጆች ማለትም ፕሮቸዝከኞች ናቸው፡፡

ፕሮቸዝከኛውን ዋለልኝን የሚያደንቀው ችሮቸዝከኛው ሌንጮ ለታ በሰፊው ያማራ ሕዝብ ላይ ያሾፈ መስሎት ‹‹በቅርቡ ብሔርተኛ የሆኑት አማሮቸ ብሔርተኝነት ጥሟቸዋል›› ሲል፣ የራሱን አላዋቂነት ራሱ መመስከሩ እንደሆነ አልገባውም፡፡ አማራ ማለት በኦሮሞ፣ በትግሬና በሌሎች ታፔላወች ራሱን በራሱ ሳይወስን በጦቢያዊነቱ ብቻ የሚያምን አማረኛ ተናጋሪ ማለት ነው፡፡ የዚህ ሕዘብ ብሔርተኝነት ደግሞ እንደ ወያኔና እንደ ኦነግ ብሔርተኝነት ትናንት የተፈጠረ የፕሮቻዝካ ዓላማ ውጤት ሳይሆን፣ ዘመናትን የተሻገረ፣ ከብረት የጠነከረ ብሔርተኝነት ነው፡፡

በሌላ አባባል በብሔርተኝነት ደረጃ ያማራን ሕዝብ የሚበልጥ ማንም – እደግመዋለሁ – ማንም የለም፡፡ ያማራ ብሔርተኝነት ግን እንደ ወያኔና ኦነግ የቀበሌ ብሔርተኝነት ሳይሆን፣ መላውን ጥቁር ሕዝብ የሚያጠቃልል የጥቁር አንበሶች ጥቁር ብሔርተኝነት (black nationalism of black lions) ነው፡፡ ይህን ሐቅ ደግሞ የሻቢያ፣ የወያኔና የኦነግ የሐሳብ አባት የሆነው ራሱ ፕሮቻዝካ በግልጽ ገልጾታል፡፡ ያማራ ልጆች ሬሳ ከወደቀበት ሳይነሳ፣ ኸርማን ኮኸን ለትዊተር ዘለፋ መቻኮሉ የሚያመለክተው ደግሞ የነጭ ብሔርተኞች ለጥቁር አንበሶች ጥቁር ብሔርተኞች ያላቸውን ከፍተኛ ፍራቻ ነው፡፡

ወያኔና ኦነግ ያሜሪቃ የጌቶወች (ghettos) ጋንጎች ጦቢያዊ አምሳሎች ናቸው፡፡ የጦቢያወቹ ወያኔና ኦነግ የጦቢያ ሕዝብ ልእልና ፀሮች ሲሆኑ፣ ያሜሪቃወቹ ጋንጎች ደግሞ ያሜሪቃዊ ጥቁር ልዕልና ፀሮች ናቸው፡፡ ያሜሪቃወቹን ጋንጎች የፈጠራቸው ወይም እንዲፈጠሩ ሁኔታወችን ያመቻቸላቸው፣ የሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ የሚባለውን ያሜሪቃን መንግሥት እንዳሻው ወዳሻው የሚዘውረው ቀላይ መንግሥት (deep state) በመባል የሚታወቀው የነጭ ዘረኞች ሕቡዕ ድርጅት ሲሆን፣ የጦቢያወቹን ጎጠኞች የፈጠሯቸው ወይም እንዲፈጠሩ ሁኔታወችን ያመቻቹላቸው ደግሞ የፕሮቻዝካን ሐሳብ አቀንቃኝ የሆኑት የምዕራባውያን (በተለይም ደግሞ ያሜሪቃና የእንግሊዝ) ቀላይ መንግሥታት ናቸው፡፡

ያሜሪቃወቹን ጋንጎችና የጦቢያወቹን ጎጠኞች የፈጠሯቸው ደግሞ ያሜሪቃንና የጦቢያን ጥቁር አንበሶች፣ በነዚህ በተመረዙ ውሾች አስነክሰው፣ አንበሶቹ ሲሞቱ፣ ውሾቹን ገድለው ሁለቱንም /ለመገላገል/ ነው፡፡ ይህን የነጭ ዘረኞች እኩይ ዘዴ ምን እንበለው? እሾህን በሾህ እንዳንለው፣ ለነጭ ዘረኞች እሾህ የሆኑባቸው አንበሶቹ እንጅ ውሾቹ አይደሉም፡፡

ያሜሪቃ ጋንጎች ትልቁን ስዕል እንዳያዩ ተደርገው በትንሹ ስዕል ላይ እየተወዛገቡ፣ ያሜሪቃ ቀላይ መንግሥት በሕቡዕ በሚነዛላቸው እጽ ደንዝዘው፣ በሚስጥር በሚያስታጥቃቸው መሣርያ ርስበራሳቸው እየተጨፋጨፉ ጥቁርን በጥቁር ይጨፈጭፋሉ፡፡ አልፈው ተርፈው ደግሞ ለጥቁር ልዕልና ሲሉ የጥቁር ፀር ከሆነው ካሜሪቃ ቀላይ መንግሥት ጋር ግብግብ የገጠሙትን ማልኮልም ኤክስን የመሠሉትን ድንቅ ታጋዮቻቸውን ከቀላዩ መንግሥት በተሰጣቸው ቀጭን ትእዛዝ መሠረት በጠራራ ፀሐይ እየረሸኑ፣ ቀኝ እጃቸውን በግራ እጃቸው ቆርጠው ምንም መተከር የማይችሉ ዱሾች ይሆናሉ፡፡

የነጭ ቅጥቅጦቹ የጦቢያ ጎጠኞች ደግሞ፣ የጦቢያ ችግር ሊፈታ የሚችለው በፕሮቻዝካ የሽንሸና ዘዴ ብቻና ብቻ ነው በማለት፣ ራሳቸውን አሳንሰው ጦቢያን በማሳነስ ራሳቸውንም ጦቢያንም ለምዕራባውያን ፕሮቻዝካዊ አውሬወች የፋሲካ ቅርጫ ለማድረግ ይናውዛሉ፡፡ ራሱ ፕሮቻዝካ በግልጽ እንደመሰከረው፣ የቅኝ ገዥወች መቅሰፍት የነበሩትን አባ ዳኘውን በተስፋፊነት እያወገዙ፣ የታላቂቱን ተስፋፊ የንግሥት ቪክቶርያን ልደት በያመቱ ያከብራሉ (በተለይም ደግሞ በካናዳና በአውስትራሊያ)፡፡ አባ ታጠቅን እየኮነኑ የጀርመኑን ቢስማርክ (Otto von Bismarck)፣ እና የጣልየኑን ጋሪቫልዲ (Guiseppe Garibaldi) ያሞግሳሉ፡፡

ውስጣዊ ችግር የሌለው አገር የለም፡፡ ዲሞክራሲ ከኔ ወዲያ ላሳር የምትለውን አሜሪቃን ብንወስድ ባያሌ ውስጣዊ ችግሮች የተሰነገች፣ በኃይል የተሳሰረች፣ አስተሳሳሪው ኃይል ቢወገድ ባጭር ጊዜ ውስጥ የምትበታተን ስንጥቅጥቅ አገር ናት፡፡ ያሜሪቃን ስንጥቅጥቅነት በደንብ የሚያውቁት፣ ሌሎች አገሮችን ለመሰነጣጠቅ የማይተኙት ያሜሪቃ መሪወች ደግሞ ያገራቸው ስንጥቅጥቆች በጊዜ ሂደት ሸለቆወች እንዳይሆኑ በመስጋት ‹ባብሔር አንድ የሆነች የማትከፋፈል አገር›› (One nation under god, indivisible) የሚል የታማኝነት ቃልግባት (pledge of allegiance) አዘጋጅተው፣ ታማኝነት ቀርቶ ቃል መግባት ምን እንደሆነ የማያውቁ እንቃቅላወችን በየቀኑ ያስነበንባሉ፡፡ የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል፡፡

ከመምሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ የኛወቹ ወያኔና ኦነግ ደግሞ ካሜሪቃ በላይ ዲሞክራት ነን አሉና ባረቀቁት የጫካ ሰነድ ላይ አንቀጽ ሠላሳ ዘጠኝን አሰፈሩ፡፡ ይህን ያደረጉት ግን በዲሞክራሲ የሚያምኑ ዲሞክራቶች በመሆናቸው ሳይሆን የጦቢያን ውስጣዊ ችግሮች በፕሮቻዝካ ዘዴ በመፍታት የራሳቸውንም የምዕራባውያንንም ዓላማ በማሳካት ባንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ሲሉ ብቻና ብቻ ነው፡፡ የጦቢያ ውስጣዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ግን በጦቢያ ጥላ ሥር በጦቢያዊ ዘዴ ብቻ ነው፡፡

ጎጠኛ ማይም ነው ደንቆሮ የማያቅ
ከክፍሎቹ ድምር ሙሉው እንደሚልቅ፡፡
ጠላቱን እንዳይጥል አንድ ሁኖ በጋራ
ተናጥሎ ይወድቃል በተራ በተራ፡፡

ለማጠቃለል ያህል የኸርማን ኮኸን የእስካሁን ተግባሮችና የቅርብ ትውተራው በግልጽ የሚያመለክተው ግለሰቡ የናዚው የሮማን ፕሮቻዝካ አፈቀላጤ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ግለሰብ ወገኖቹ በናዚ የተጨፈጨፉ አይሁዳዊ መሆኑ ነው፡፡ የኸርማን ኮኸን ትውተራ የሚያስፈነጫቸው ኦሮሞወች ደግሞ፣ ግለሰቡ ለኦሮሞ ዴንታ እንደሌለውና የሚመኘው የጥቁር አንበሶችን ጥቁር ብሔርተኝነት ሞት እንደሆነ ያልተገነዘቡ እንጭጮች ናቸው፡፡ ዐብይ አህመድ ‹በሬ ሆይ …› በሚባለው ዘዴ ጦቢያን እያታለለ ወደ ኦሮሞ አጼጌ (oromo empire) እወስዳለሁ ሲል፣ ፕሮቸዝከኞች ደግሞ በዚሁ ዘዴ ወደ ነጭ ባርነት እየወሰዱት እንደሆነ አልገባውም፡፡ ጎጠኛ የዕይታ አድማሱ ካፍንጫው ሥር የማያልፍ ድንጉዝ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic