>

የእውቀት ጾመኛው የተክለብርሃን ወልደ አረጋይ  ነገር. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

የእውቀት ጾመኛው የተክለብርሃን ወልደ አረጋይ  ነገር. . . 

አቻምየለህ ታምሩ
* ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን የኢትዮጵያ  ብቸኛ ሃይማኖት አድርገው ያወጁት በተክለብርሃን ወልደ አረጋይ  መመዘኛ ፌዴራሊዝም ተደርገው የቀረቡት ዐፄ ዮሐንስ እንጂ አሐዳዊ አድርጎ ያቀረባቸው ዐፄ ምኒልክ አይደሉም!
 
* ዐፄ ዮሐንስ  አማርኛን ብሔራዊ ቋንቋ ማድረጋቸውን፤ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን  ብሔራዊ ሃይማኖት አድረው ማወጃቸውን ዜና መዋዕላቸው ሊቀ መራዌ መዝግበውታል!
—-
የዐቢይ አሕመድና የተመስገን ጥሩነህ  አሳዳጊና ጌታ የነበረው ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ የሚባለው የፋሽስት ወያኔ የገበሬ ሽፍታ[ወታደር ላለማለት ነው] የትግላችን አላማ ኢትዮጵያ አልነበረችም ሲል  ከሰሞኑ የተናገረው ብዙ ሰዎችን ማነጋገሩ ሳያስገርመኝ አልቀረም።
 ድርጅቱ ብራና ፍቆ፣ ቀለም በጥብጦ፣ ጉባኤ አስፋፍቶ ካዘጋጀው ፕሮግራም፤ የነፍስ አባታቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ከሰጠው ምስክርነት፤ እንደ አረጋዊ በርሀ፣ ግደይ ዘርዓ ጽዮንና ተስፋዬ አጽበሃ  [ተሰፋዬ ቼንቶ] አይነት የድርጅቱ ቀደምት ሽፍቶች ከጻፏቸው መጽሐፍት ለማወቅ እንደቻልነው የፋሽስት ወያኔ  ተቀዳሚ አላማ ከትግራይ አልፎ ተከዜን በመሻገር በሱዳንና በጎንደር-ወለጋ መካከል እየተዋሰነ ቤንሻንጉል የሚባለውን ክልል ጠቅልሎ ጋምቤላን በማቀፍ ከመረብ እስከ ባሮ የተዘረጋች የታላቋ ትግራይ ሪፑብሊክ መመስረት ነበር።
ስለዚህ ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ ስለ ሕወሓት ተቀዳሚ አላማ የተናገረው መቀሌ የመሸጉት እነ ስብሐት ነጋና ስዩም መስፍን በተናገሩ ቁጥር ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ የትጥቅ ትግል የጀመሩት በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓት ለመመስረት ነው እያሉ ለሚያደነቁሯቸው  ብሔርተኞች እንጂ ፈጽሞ የማይታወቅ አዲስ ነገር አይደለም።
ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ  ራሱን የተማረ ቴክኖክራት እያለ ሲናገር ስሰማ ድፍረቱን አደነቅሁ። ራሱን እንደ ቴክኖክራት የሚቆጥረው  ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ  ለመማር ወይም ለማወቅ ያጠፋው ጊዜ እንደሚቆጨው የሚናገረው ጉድ ነው።
 ዐፄ ዮሐንስ የጀመሩት ፌዴራሊዝም  በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አንድ ቋንቋ [አማርኛን ማለቱ ነው] ፣ አንድ ባሕልና አንድ ሃይማኖት ፖሊሲ ተጨናገፈ ሲል ያስተጋባውም ቅርሻትም የተለመደው የፋሽስት ወያኔዎች ድንቁርና ነው። ታሪኩ  ሲወጣ ግን የሚያሳየን እውነታ በተቃራኒው ነው።
አማርኛን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ያደረጉት ዐፄ ዮሐንስ ናቸው። ዳግማዊ ምኒልክ በዘመናቸው ያስቀጠሉት ዐፄ ዮሐንስ ሕጋዊ ያደረጉትን ነው።  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን የኢትዮጵያ  ብቸኛ ሃይማኖት አድርገው ያወጁት በተክለብርሃን ወልደ አረጋይ  መመዘኛ ፌዴራሊዝ ተደርገው የቀረቡት ዐፄ ዮሐንስ እንጂ አሐዳዊ አድርጎ ያቀረባቸው ዐፄ ምኒልክ አይደሉም።  ዐፄ ዮሐንስ  አማርኛን ብሔራዊ ቋንቋ ማድረጋቸውን፤ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን  ብሔራዊ ሃይማኖት አድረው ማወጃቸውን ዜና መዋዕላቸው ሊቀ መራዌ መዝግበውታል።
ሌላኛው የዘመኑ ታሪክ መዝጋቢ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ደግሞ በዐፄ ዮሐንስ ዘመን  ስለነበረው አስተዳደርና ዳግማዊ ምኒልክ ስላደረጉት ለውጥ በስፋት አቅርበዋል።  በ1931 ዓ.ም.  በእንግሊዝ ባዝ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ «የኢትዮጵያ ታሪክ  ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል» በሚለው መጽሐፋቸው [ከገጽ 209-210]  በዐፄ ዮሐንስ  ዘመን  ሕዝብ የተመረረባቸውን ጉዳዮችና  ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ  ለውጠው ሕዝብን ያስደሰቱባቸውን እርምጃዎች እንዲህ ዘርዝረዋል፤
1ኛ. ዐፄ ዮሐንስ የተጠሉበት ዋናው ነገር ባልተማሩ መነኮሳት ምክር እየተመሩ እስላሙን፣ ኢ-አማኒውንና ፈላሻውን ሳይማር እንዲያው በግድ ተጠመቅና ክርስቲያን ሁሉ እያሉ በአዋጅ በመንገራቸውና አንጠመቅም! ክርስቲያን አንሆንም ያሉትን በሞትም በስደትም በእስራትም በልዩ ልዩ መከራና ስቃይም በመቅጣታቸው ነበር። ዐፄ ምኒልክ ግን ተምሮ በፍቃዱ ተጠምቆ ክርስቲያን ካልሆነ በቀር እንደ አባቱ ሃይማኖት እንዲኖር እንጂ በግድ እንዳይጠመቅ አደረጉለት፤
2ኛ. ዐፄ ዮሐንስ የተጠሉበት ሌላው ዋና ነገር መንም ሰው በመሬቱ ላይ ትንባሆ እንዳይዘራና እንዳይጠጣ አዋጅ  በመናገራቸውና በመሬቱ የዘራ መሬቱ ይነጠቃል፤ ባፉም የጎረሰው ከንፈሩ ይቆረጥ፣ ሱረትም በአፍንጫው የጠጣ አፍንጫውን ይፎነን በማለታቸው ነበር።  ዐፄ ምኒልክ ግን ትምባሆ መጠጣት እንደጠላ፣ እንደ ጠጅ፣ እንደ ቡና ልማድ ነው እንጂ በመጽሐፍ የተከለከለ በነፍስም የሚያስኮንን አለመሆኑን አውቀው በትንባሆ ነገር ሰው ሁሉ እንደልማዱ እንዲኖር አደረጉለት፤
3ኛ፡ ዐፄ ዮሐንስ የተጠሉበት አንዱና ዋናው ነገር ካንዱ  አውራጃ ወደ ሌላው አውራጃ  ሲዘዋወሩ ለወታደራቸው ሁሉ  ነጻነት እየሰጡ በየባላገሩ ቤት ተሠሪ እየሆነ እየገባ የባላገሩን እንጀራውን፣ ወጡን፣ ጠላውን፣ ሥጋውን ይህንን ሁሉ የመሳሰለውን ሁሉ በግድ እንዲወሰድበት ስላደረጉ ነበር። አንዳንዱማ የባላገሩን ሚስት በግድ እየያዘ በባሏ ፊት ያስነውራት ነበር። ዐፄ ምኒልክ ግን  [ለሕዝባቸው] «ለኋላው ሁሉንም አስቀርልሃለሁ። አሁን ለጊዜው ግን ባላገር የሆንህ እንደ አቅምህ እህል እያወጣህ ለወታደር ቀለብ ስጥ እንዲ ወታደር በቤትህ አይግባብህ» የሚል አዋጅ ነገሩለት። [ዐፄ ምኒልክ] ይህንንም የመሰለውን የከበደ ነገር ሸክም ከባላገሩ ጫንቃ ላይ ስላወረዱለት ደስ አለው።
እንግዲህ! ይህንን  በታሪክ  ተመዝግቦ የምናገኘው እውነት  ይዘን ተክለብርሃን ወልደ አረጋይ ስለ ዐፄ ምኒልክ አሐዳዊነትና ስለ ዐፄ ዮሐንስ ፌዴራላዊነት የተናገረውን በርሱ መመዘኛ ስንመረምር  ከሁለቱ ነገሥታት  ማን አሐዳዊና ማን ፌዴራላዊ እንደነበር መናገር አይከብድም።
ስለዚህ ሳትመረምር ሀሳብ የሌለበትን የፋሽስት ወያኔ የፈጠራ ወሬ ይዘህ ዐፄ ዮሐንስ የጀመሩት ፌዴራሊዝም  በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አንድ ቋንቋ ፣ አንድ ባሕልና አንድ ሃይማኖት ፖሊሲ ተጨናገፈ  እያልህ አለማወቅህን በአደባባይ ስታስታውቅ የምትውል  የእውቀት ጾመኛ  ሁሉ  «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር ልንለግስህ እንደወዳለን!
Filed in: Amharic