>
5:16 pm - Monday May 24, 6680

( ትዝታ ዘጎንደር) የሱዳን ህገወጥ ወረራና የጎንደር ፖሊስ  - ክፍል ሁለት 

የሱዳን ህገወጥ ወረራና የጎንደር ፖሊስ 

( ትዝታ ዘጎንደር) – ክፍል ሁለት 
ብርሀኑ ተክለያሬድ
አግባው አጠገቤ ሲደርስ በመገላገል ፈንታ ፖሊሱ ላይ አፍጥጦ “ትገለው ነው? አስኪ ተኩስማ!ግደለውማ! የት ልትገባ?” አለው የፖሊሱ  ደምስር ሲገታተር አየሁት በአግባው የጎንደሬ ወኔ ተያይዘን ስንሞት ታየኝ አንገቱን አልለቀቅኩም የሽዋስ አሰፋ ከየት መጣ ሳይባል በፖሊሱ ወገብ ላይ ተጠመጠመ…
 የሽዋስ ፖሊሱን አረጋግቶ ገለል አደረገው። ከግልግል በኋላ በዙሪያችን የቆሙ ፖሊሶች ሁላችንንም ወደ መኪና አስገቡንና በፖሊሶች መኪና ታጅበን ወደ 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንድንሄድ ተደረገ።መኪናው ሊንቀሳቀስ ሲል ዮኒ ማይክሮፎን አብርቶ እስከዛሬ ስንገናኝ እያነሳን በሳቅ የምንፈርስባትን አጭር ዲስኩር አደረገ። “የጎንደር ህዝብ ሆይ እንደምታዩት እኛ ልጆቻችሁ ከአዲስ አበባ ተነስተን መተናል አሁን ደሞ እንደምታዩት በፖሊስ ተይዘናል ወዴት እንደሚወስዱንም አናውቅም እናም የጎንደር ህዝብ ሆይ ተከታተለን” አለ። ጉዞ ስንጀምር መኪናው ወደ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚወስደውን መንገድ ትቶ ወደ ሁመራ መውጫ መስመር እንድንሄድ ታዘዝን ከዚያም ፖሊሶቹ “ያልበተናችሁት ወረቀት ካለ በትኑና ጨርሱ” አሉን እየተገረምን ወይኒና ጄሪ በመስኮት ወጥተው ወረቀቶቹን በትነው ጨረሱ መኪኖቹ ዞረው ወደ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ገባን።
በፍቅረ ማርያም የተነከሰው ፖሊስ እጁን አንከርፍፎ መጥቶ “አንት ውሻ ትነክሰኝ? አሳይሀለሁ ና ተነስ ሆስፒታል ሄደን ትመረመራለህ” አለ። ከፍቅረ ማርያም ጋር አንገታችንን ደፍተን በሳቅ ፈረስን።(አይ ጥሩ ዘመን) “ደሞ ትገለፍጣላችሁ?” ተባልን የዮኒን ንግግር ሰምቶም ሳይሰማም ተከትሎን የመጣው የጎንደር ነዋሪ ውጩን ሞልቶት ነበር። ከግማሽ ሰአት ቆይታ በኋላ ከበላይ ፍቷቸው የሚል ትእዛዝ መጣ። እናም ፖሊሶቹ “ካሜራችሁን እንመርምርና ከተናካሹ ውጪ ሁላችሁም ትወጣላችሁ አሉ” ሌላ ፖሊስ ውሳኔውን ተቃወመ “እኔም እከሳለሁ አግባው ወያኔ ብሎ ሰድቦኛል እንዴት ወያኔ እባላለሁ እኔም እንደሱ ጎንደሬ ነኝ” አለ ሌላ ረጅም ሳቅ ተጀመረ።
ከደቂቃዎች በኋላ ከከተማው ፖሊስ ኮሚሽን አንድ የተቆጣ የሚመስል ፖሊስ መጥቶ
“ለምን እስካሁን አልተፈቱም?” አለ።
“አይ ካሜራቸውን መፈተሽ ስላለብን ባለሙያ እየጠበቅን ነው”አለ ከኔ ጋር ግብግብ የፈጠረው ፖሊስ
አዲስ መጪው ፈገግ ብሎ “ካሜራቸው ከተመረመረ በኋላስ? ፎቶ ልታስጠፏቸው? ተመልከት እስኪ ይኽንን”ብሎ ስልኩ ላይ የሚታየውን ፌስቡክን ያጥለቀለቀውን ፎቶ አሳየው። መስቀል አደባባይ ከፖሊሶቹ ጋር የነበረውን ግብግብ  ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ፍቅረ ማርያም ፎቶዎቹን ካነሳ በኋላ ቨፖሊስ ሲያዝ ሚሞሪውን ለሰው አቀብሎ ነበር ያልተያዙ ጓዶች ደግሞ ፎቶውን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፈውታል።
ፖሊሱ የብሽቀት ሳቅ እየሳቀ “ሁላችሁም መታወቂያ ዋስ አምጡ”አለን በር ላይ መጨረሻችንን ለማየት ይጠብቅ የነበረው የጎንደር ነዋሪ እየተሽቀዳደመ ዋስትና ፈረመልን።ከዚያ ተነካሹን ማባበል ጀመርን “በቃ ሲታነቅ አማራጭ አጥቶ ነው የነከሰህ ደሞኮ አልተጎዳህም በቃ ይቅርታ አርግለት” ወዘተ ሁላችንም ተንጫጫንበት ፖሊሶችም አብረውን አማላጅ ሆኑ በመጨረሻ ተስማማ። ሁላችንም  “ካሁን በኋላ ብትቀሰቅሱ ………. ” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶን ተያይዘን ወጣን ሆቴላችን ስንደርስም የአበባ ሆቴል ባለቤት የጎንደር ከተማ አመራሮችና ፖሊሶች መጥተው “እዚህ አልጋ የያዙትን የፓርቲ አባላት በሙሉ አስወጣ” እንዳሉትና እርሱም “ሆቴል የከፈትኩት ልሰራ ነው። እኔን መርጠው የመጡ እንግዶቼንም አላስወጣም” ብሎ እንደመለሳቸው ሰማን።
በሁላችንም ልብ ውስጥ “ሰልፉ መደረግ አለበት” የሚል ቁርጠኝነት አለ። እናም ተሰብስበን እቅድ አወጣን ቅስቀሳ ካደረግን መታሰራችን አይቀርም በሁለት ቡድን እንከፈልና ግማሾቹ ከሆቴል እንዳይወጡ ሌሎቻችን ከታሰርን እነሱ ሰልፉን  እንዲቀጥሉ ተስማማን። ዮኒ፣የሽዋስ፣ጌታነህ፣ጄሪ ፣አቤል፣ሀብታሙ ደመቀ፣ወይኒና እኔ ሆነን ለቅስቀሳ ተመደብን። ሰልፉ 2ቀን ቀርቶታል እናም በጠዋት ተነስተን እንደምንወጣ ተነጋግረን በጊዜ ወደ መኝታ ክፍላችን!
እኩለ ሌሊት አካባቢ የሆቴሉ አካባቢ ጩኸት በጩኸት ሆነ ሁሉም ከየክፍሉ ወጥቶ ኮሪደር ላይ ቆሞ የጩኸቱን ምንጭ ማጣራት ጀመረ፤ጩኸቱ እየጨመረ መጣ መብራት ጠፋ፤ድንገት የተኩስ እሩምታ ተሰማ። ትርምስምሳችን ወጣ ፍቅረ በቅፅበት ጋንታ መሪ ሆነ”መሬት ያዝ” አለ፤አንዱ ጓድ በደረቱ እየተሳበ ወደክፍሉ ገባ፤የሽዋስና ሀብታሙ እየተገፋፉ ወደክፍላቸው …….. ብቻ ተተራመስን። በሮች ተቆለፉ። ልሮጥ ስል በረንዳ ላይ ዮኒ በሳቅ እየፈረሰ ቆሟል ወደታች እየተመለከተ” ኧረ ጎረቤት እሳት ተነስቶ ነው ተኩሱም የእርዳታ ጥየቃ ነው ተረጋጉ”አለ መሮጤን ትቼ ከዮኒ ጋር ወደታች ማየት ጀመርኩ፤እውነትም ማህበረሰቡ እሳት እያጠፋ ነበር። ሁሉም ከየክፍሉ ወጣ ኮሪደሩ በተረብ ተደበላለቀ። “መሬት ያዝ” መሳቂያችን ሆነች። በደረቱ የተሳበው ጓድ “ዘንዶዬ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ስንስቅ አመሸን።
በጠዋት ለቅስቀሳ የተመደብነው ወደ ቅስቀሳ ለመውጣት ተዘጋጀን። ፖሊሶች ድጋሚ እንዳንቀሰቅስ ነግረውና እናም እስር ሊገጥመን ይችላል። የፖሊሶቹ ምክንያት ከፖለቲካው ባሻገር ‘የድምፅ ብክለት’ የምትል ምክንያት ነበረቻቸው። ይሁን እንጂ ጃኖ ባንድ ቅዳሜ ለሚያዘጋጀው ኮንሰርት በነፃነት ቅስቀሳ እያደረገ ነበር። ያም ሆኖ ቁርስ ተበልቶ ጉዞ ወደ ቅስቀሳ ሆነ ከተማዋን በቅስቀሳ አደመቅናት ቅስቀሳውን ቀጥለን አዘዞ ስንደርስ በፖሊስ ተያዝን ያሁኑ እስር ማባበል አልነበረውም በቁጣና በጉልበት ነው ከነመኪናችን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገባን ስልካችንን ተቀማን ሴቶቹ ለብቻቸው እንዲቀመጡ ተደረገ “መሬት ቁጭ በሉ መነጋገር አይቻልም” ተባለ።
Filed in: Amharic