>

የፈሪ በር (መስፍን አረጋ)

የፈሪ በር

 

መስፍን አረጋ


ይህ አጭር ጽሑፍ ‹‹የሰንሹ የጦርነት ጥበብ›› በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው ጨርሸ፣ ህትመቱን ከሚጠባበቀው መጽሐፌ ባጭሩ የተቀነጨበ ነው፡፡  

በቻይና ዘመነ መሳፍንት የሃን (Han) መስፍን የጦር አዛዥ የነበረው ኩንግ (Kung) በመስፍኑ ላይ ያመጹትን ወንበዴወች ተራራማ ምሽጋቸውን ዙርያውን ከቦ መፈናፈኛ በማሳጣት ቀን ከሌት እያጠቃ አንድ ወር ሙሉ ቢያስጨንቃቸውም፣ ምሽጋቸውን ግን መስበር አልቻለም ነበር፡፡  

መስፍኑም ኩንግን ጠርቶ ‹‹እነዚህን ወንበዴወች ዙርያቸውን ከበህ መፈናፈኛ በማሳጣት በሁሉም አቅጣጫ ስለምትደበድባቸው፣ ያላቸው አንድ ምርጫ እስከሞት ድረስ በቆራጥነት መዋጋት ነው፡፡  ፈሪወቹን አጀግነኻቸዋል፡፡  አንተው ራስህ የሰጠኻቸውን ጀግንነት አንተው ራስህ ልትቀማቸው ከፈለክ፣ የፈሪ በር ክፈትላቸውና የተከፈተው የፈሪ በር በየት በኩል እንደሆነ በተዛዋሪ አሳውቃቸው›› ብሎ መከረው፡፡  

ኩንግም የመስፍኑን ምክር ሲተገብረው፣ አንድ ወር ሙሉ ተዋግቶ፣ አያሌ ወታደሮቹን ሰውቶ፣ ሊሰብረው ያልቻለውን ምሽግ በግማሽ ቀን ውጊያና ባነስተኛ መስዋዕትነት በረጋገደው፡፡  

ያገራችንን የጦቢያን ዳር ድንበር ለማስከበር ባሕርጌ (Eritrea) ላይ በተደረገው ጦርነት (በተለይም ደግሞ በናቅፋው ግንባር) ከተፈጸሙት አያሌ ስሕተቶች ውስጥ አንዱና ዋናው የፈሪ በር አለመከፈት ይመስለኛል፡፡  የናቅፋን ቀበሮ አንበሳ ያደረግነው እኛው ራሳችን ነበርን፡፡

በተንቤን ተራራማ ሽኩቻወች ውስጥ የተሸኮተውን የወያኔን ሽፍታ ባጭሩ ትጥቅ በማስፍታት የወንድማችንን የትግራይን ሕዝብ መከራ ለማሳጠር ደግሞ፣ የፈሪ በር ጉዳይ በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic