>

የት ነበራችሁ...??? (ኤርሚያስ ለገሰ)

የት ነበራችሁ…???

ኤርሚያስ ለገሰ

፩.  ከትላንት ወዲያ ወዲያ እስክንድር ነጋ “በጀዋር መሃመድና አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት የሚመራውና ራሱን ቄሮ ብሎ የሚጠራ ቡድን ጄኖሳይድ ለመፈፀም ተዘጋጅቷል” በማለት አሳሰበ። ተደግፈው የተደመሩት ኃይሎች ተረባርበው ” መንግስት አንድ እርምጃ ይውሰድ!” የሚል ምክረ-ሃሳብ አቀረቡ። ምክራቸው ወደ ተግባር ተቀየረ።
፪. ከትላንት በስቲያ የአብይ አገዛዝ ሚዲያዎችን ይቆጣጠር። ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ እርምጃ ይውሰድ። ኢንተርኔት ይዘጋ አሉ። አገዛዙ ምክረ-ሃሳቡን አዳመጠ። እናም ቁጭት ውስጥ የገቡ ጋዜጠኞች ” የአንዳርጋቸው ጽጌ ዓዋጅ” ብለው የሚጠሩት ድራኮኒያን የሚዲያ አዋጅ ወጣ። አሁን ደግሞ ማህበራዊ ድረ-ገፅን የሚቆጣጠር ደንብ ለመፅደቅ ጠረጴዛ ላይ ነው።
፫. ትላንት ሉዓላዊነት የሚባል ነገር የለም። የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት እርምጃ መውሰድ አለባቸው አሉ። ምክረ-ሃሳባቸው ተሰምቶ የኢሳያስ ሰራዊት ሉአላዊነት ጥሶ ገባ። በኢትዮጵያውያን በተለይም በትግራይ ተወላጆች ላይ ዘላለማዊ ጠላትነት ያነገበው የሻዕቢያ ሰራዊት የበቀል እርምጃ ወሰደ። የጦር ወንጀል ፈፀመ። ጄኖሳይድ ፈፀመ። አስገድዶ መድፈር ፈፀመ። የሻይ ማንቆርቆሪያ ሳይቀር ዘረፈ።
፬. እንደገና ትላንት በአማራ ተወላጆችና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና ምዕመኗ ላይ ተለይቶ የተፈፀመ ጄኖሳይድና የማጥራት ስራ የለም አሉ። እንደ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ያሉ ጄኖሳይዱን እንዲቆም የተንቀሳቁሱ ሰዎች ከጠላት ጋር በሚሰሩ ባንዳነት ተፈረጁ። አገዛዙም ይህን ምክረ-ሃሳብ መሰረት አድርጎ ፕሮፐጋንዳውን ቀረፀ። በአማራና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ላይ ጄኖሳይድ ተፈፅሟል የሚሉትን በማሳደድ እርምጃ ወሰደ። የተለዩ ባለስልጣናትን በጄኖሳይድ በመክሰስ ላይ ያሉትን ተቆርቋሪዎች በጠላትነት በመፈረጅ ማሳደድና የተቀነባበረ ስም ማጥፋት ከፈተ።
፭. ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ በግልፅ ሰይፋቸውን መዘዙ። ማህበረ ቅዱሳን አመራሩን የተቆጣጠረው ህውሃት ነው፣ መንግስት በተቋሙ ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት ብለው ምክረ-ሃሳብ ለአገዛዙ አቀረቡ። ነገ የዓብይ አህመድ አገዛዝ ምን እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን።
እናም እንዲህ በማለት አንዳንዶችን እንጠይቃለን፣
የተደጋፊ ተደማሪዎቹ አካሄድ እስከዛሬ <<ብራ መብረቁ>> የሆነባችሁ ለምንድነው? አካሄዳቸውን ሳታውቁ ቀርታችሁ ነው? ባለፉት ሶስት ዓመታት የዓብይ አህመድን ውታፍ ሲነቅሉ አንዳንዶቻችሁ ተባባሪ አልነበራችሁም? ዛሬ በእነሱ ላይ በአገም ጠቀም ተረማምዳችሁ የራሳችሁን ስም ለማደስ ለምን ፈለጋችሁ? ህሊናዊና መንፈሳዊ ሞራሉን ከየት አመጣችሁት? እናም ዋነኛው “የሴራ ፖለቲካ” ምልክት ናችሁና በቅድሚያ የራሳችሁን ዘነዘና የሚያክል ጉድፍ መንጭቃችሁ ጣሉ። መርህ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም የመርህ ሰው ሁኑ!!
( በተያያዘ ሁኔታ ለወንድሜ መምህር ዘመድኩን በቀለ ያለኝን አክብሮትና አድናቆት ሳልገልፅ ማለፍ አልፈልግም። አንድ ግለሰብ ሆነህ “አንደ ሺህ” ስታፍ ያለው ግዙፍ ድርጅት የምታንቀሳቀስ የሚመስል የአደባባይ ሰው ነህ። እውነት ለመናገር አስር ዘመድኩኖች ቢኖሩን ኖሮ የሚዲያው ምህዳር ግልብጥብጡ ይወጣ ነበር። በዚህ አጋጣሚ የአገዛዞቹ ቁንጮዎች ጭምር ” ዘመድኩን ዛሬ ምን አለ? ምን አቅጣጫ አስቀመጠ?” የሚል የየዕለቱ ሚዲያ ሞኒተሪንግ እንደሚቀበሉ አረጋግጫለሁ። በርታ! በርታ! ምስጋና ለመረጃ ቲቪ!!)
Filed in: Amharic