>

መላው ዓለም በምርጫ ቀን ይጋጫሉ ሲለን እኛ ደግሞ እናስተምራቸዋለን...!!!”  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

መላው ዓለም በምርጫ ቀን ይጋጫሉ ሲለን እኛ ደግሞ እናስተምራቸዋለን…!!!” 
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ረቡዕ ለጅማ ከተማ ነዋሪዎች ባሰሙት ንግግር
  ኢትዮጵያ ኢንሳይደር:-

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በምርጫው ዕለት መራጮች ድምጽ ከመስጠት ጎን ለጎን ዛፍ በመትከል ለዓለም ትምህርት የሚሆን ተግባር እንዲያከናውኑ ባሳሰቡበት መልዕክታቸው ነው።
“በሚቀጥለው ሰኞ በምናደርገው ምርጫ ‘ዲሞክራሲን እንተክላለን፤ ዛፍም እንተክላለን’ ያልንበት ዋናው ምክንያት መላው ኢትዮጵያ  እንደዚህ እንደ ጅማ አረንጓዴ ለብሶ ለአይን የማይጠገብ ውብ እንዲሆን ካለን ፍላጎት ነው” ያሉት አብይ፤ የጅማ ነዋሪዎችም ሆኑ ኢትዮጵያን በዕለቱ ችግኝ እንደሚተክሉ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስቴድየም ለተሰበሰቡ በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻችው ባሰሙት ንግግር፤ ራሳቸው በሚመሩት ብልጽግና ፓርቲም ሆነ በሌሎች ፓርቲዎች ውስጥ የማያስፈልጉ ያሏቸውን ግለሰቦች ግብር ዘርዝረዋል። “ከብልጽግናም ሆነ ከሌላ ከህዝባችን የሚሰርቅ ሌባ   አያስፈልግንም። ከብልጽግናም ሆነ ሌላ  ጠዋታ ማታ ሰርቶ የኢትዮጵያን ብልጽግና እና ልማት የማያረጋግጥ አያስፈልግንም” ብለዋል አብይ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔ 14ቱ ምርጫ ከሚፎካከሩ ኃይሎች መካከል “ኢትዮጵያን የሚወዱ፣ ኢትዮጵያን ማገልገል የሚፈልጉ፣ የኢትዮጵያ አንድነትን እና ነጻነትን የሚያከብሩ”  ላሏቸው ተወዳዳሪዎች መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።  ከየትኛውም ፓርቲ ቢሆን፤ “የኢትዮጵያን ህዝቦች እኩልነት፣ የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት እንዲሁም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህዝብ ፈርጥ መሆኗን አምኖ” ለሚሰራ ተወዳዳሪም የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላፈዋል።
የምርጫ ቅስቀሳ ለመጨረሻ ቀን በሚካሄድበት በዛሬው ዕለት በጅማ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በንግግራቸው እምብዛም የምርጫን ጉዳይ አላነሱም። ከሰሞኑ በተለያዩ ቦታዎች በሚካሄዱ መርሃ ግብሮች ላይ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የተደመጡትን  “የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን”  ጉዳይም አልጠቀሱም። እርሳቸው በንግግራቸው ጉዳዩን ባያነኩትም የጅማውን የስቴድየም መርሃ ግብር ይመሩ የነበሩ መድረክ መሪዎች እና ዘፋኞች ግን አሜሪካንን ጭምር በስም በመጥቀስ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መፈክር ቀመስ መልዕክቶች ሲያስተላልፉ ተደምጠዋል።
በዛሬ የጅማ መርሃ ግብር ማጠቃለያ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አብረዋቸው በክንውኑ ላይ ለተሳተፉ ባለስልጣናት የፈረስ እና የጋቢ ሽልማት ተበርክቷል። በስቴድየም በተሰበሰበው ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ የተደመሙ የመሰሉት አብይ፤ የስቴድየሙን ግማሽ በሩጫ በመዞር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ምርጫ የተናገሩትን ለማድመጥ እና የሩጫ ትዕይንታቸውን ለመመልከት ከታች ከተያያዘው ቪዲዮ ተጭነው ይመልከቱ።
Filed in: Amharic