>

ተጠይቃዊ እይታ. . .  ( አቻምየለህ ታምሩ)

ተጠይቃዊ እይታ. . .  

አቻምየለህ ታምሩ

 

*… ትናንት ወያኔን ወክለው “ተወዳድረው” መቶ በመቶ ተመረጡ ሲባሉ የነበሩ ሰዎች በኦሮሙማ ዘመንም እነዚሁ ተመሳሳይ ሰዎች ኦሮሙማን ወክለው “ተወዳድረው” መቶ በመቶ ተመረጡ ከተባለና  እነዚህ በወያኔ ዘመን መቶ በመቶ ይመረጡ የነበሩ ሰዎች መቶ በመቶ የተመረጡበት የኦሮሙማ ዘመን ምርጫ ተብዮ “ዲሞክራሲያዊ ነበር”፤ “አልተጭበረበረም” ከተባለ ፤ እነዚሁ ሰዎች ወያኔን ወክለው መቶ በመቶ ተመረጡ ሲባሉ የኖሩበትን በወያኔ ዘመናት ተካሄዱ የተባሉ ምርጫ ተብዮዎችን “ዲሞክራሲያዊ አልነበሩም፤ የተጭበረበሩ ናቸው” ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ገፊ ጭብጥ ከቶ ሊኖር አይችልም!
 
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሄደ የተባለው ምርጫ ተብዮ ነገር  የኢዜማ ሰዎች እንደሚሉት “ዲሞክራሲያዊ ነበር” ፤ “አልተጭበረበረም” ከተባለ በወያኔ ዘመን ተካሄዱ የተባሉትን ምርጫ ተብዮዎች ዲሞክራሲያዊ አልነበሩም፤ የተጭበረበሩ ናቸው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ገፊ ጭብጥ ይኖራል ብዬ አላስብም። “ዲሞክራሲያዊ ነበር” ፤ “አልተጭበረበረው” እየተባለ በኢዜማ ሰዎች እየተነገረለት ያለው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ተብዮ ነገር የተደረገው ወያኔ በዘረጋው ሥርዓት ላይ ምንም አይነት የሥርዓት ለውጥ ሳይኖርና የኦሮሙማው አገዛዝ በየምርጫ ቅስቀሳ ተብዮው የወያኔን ሕገ አራዊት ሳይበረዝና ሳይከለስ ለማስቀጠል ቃል በገባበት ሁናቴ ነው።
ልብ በሉ! ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተደረገ የተባለው ምርጫ ተብዮ የተካሄደው ወያኔ ለመቀዳጀት 27 ዓመታት የፈጀበትን የአፓርታይድ አገዛዝ ነውሮች በዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ በአስር ወራት ውስጥ ክብረ ወሰኑን በሰበረበትና እልቆ ቢስ የኦሮሙማ ነውሮችን በጨመረበት ማግስት ነው። በወያኔ የ27 የአገዛዝ ዘመናት ውስጥ ያልታዩ ኦሮሙማ መር የጅምላ ፍጅቶች፣ የጭካኔ ጥጎች፣ ከተሞች ሙሉ በሙሉ የወደሙበትና ድኆች በማንነታቸው ተለይተው በተኙበት በጅምላ የተፈጁበትና የዘር ፍጅት ሰለባ ሕጻናትና ሴቶች በግሬደ ተዝቀው እንደ ቆሻሻ የተጣሉት ባለፉት ሶስት የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ ዓመታት ውስጥ ነው።
ምን ይኼ ብቻ! በኢዜማ ሰዎች ስለ ዲሞክራሲያዊነቱ እየተመሰከረለት ያለው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተደረገ በተባለው ምርጫ ኦሮሙማን ወክለው [ብአዴን፣ ደሕዴን፣ ወዘተ የሚባሉትን ሁሉ ያጠቃልላል] ተወዳድረው መቶ በመቶ ተመረጡ የተባሉት ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ወያኔን ወክለው [ኦሕዴድ፣ ብአዴን፣ ደሕዴን፣ ወዘተ የሚባሉትን ሁሉ ያጠቃልላል] ተወዳድረው መቶ በመቶ ተመረጡ የተባሉ ሰዎች ናቸው።
በመሆኑም ወያኔ የዘረጋው ሥርዓት ሳይለወጥ፤ የቅሚያና የግድያ ደንብ የሆነው የወያኔ ሕገ አራዊት ሳይቀየር፤ ከወያኔ የጭካኔ አገዛዝ እጅጉን የከፋ አረመኔያዊ አገዛዝ በተተካበት፤  የራባቸውና ሁሉ ብርቁ የሆኑ፣ ሰማዩንም ምድሩንም የኛ ነው የሚሉ፣ ምንም አይነት የሞራል ስልጣኔ ብሎ ነገር ያልፈጠረባቸው ነውር ጌጡዎች በመንግሥትነት በተሰየሙበት፣ በወያኔ ዘመን አይተነውና ሰምተነው የማናውቀው ኦሮሙማ መር የጅምላ ፍጅትና የድኆች እልቂት በየሰርኩ በሚካሄድበት በዚህ ወቅት  ወያኔን ወክለው “ተወዳድረው” መቶ በመቶ ተመረጡ ሲባሉ የነበሩ ሰዎች በኦሮሙማ ዘመንም እነዚሁ ተመሳሳይ ሰዎች ኦሮሙማን ወክለው “ተወዳድረው” መቶ በመቶ ተመረጡ ከተባለና  እነዚህ በወያኔ ዘመን መቶ በመቶ ይመረጡ የነበሩ ሰዎች መቶ በመቶ የተመረጡበት የኦሮሙማ ዘመን ምርጫ ተብዮ “ዲሞክራሲያዊ ነበር”፤ “አልተጭበረበረም” ከተባለ ፤ እነዚሁ ሰዎች ወያኔን ወክለው መቶ በመቶ ተመረጡ ሲባሉ የኖሩበትን በወያኔ ዘመናት ተካሄዱ የተባሉ ምርጫ ተብዮዎችን “ዲሞክራሲያዊ አልነበሩም፤ የተጭበረበሩ ናቸው” ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ገፊ ጭብጥ ከቶ ሊኖር አይችልም!
Filed in: Amharic