>
5:18 pm - Saturday June 14, 5473

የኢዜማ ግምገማ...!!! አሳዬ ደርቤ

የኢዜማ ግምገማ…!!!

አሳዬ ደርቤ

*… ቅንጅት ነኝ ስትል- ካንተ ተቀናጀሁ
ግንቦት ሰባት ስትሆን- ኤርትራ ተገኘሁ
አምና ግን በልጽገህ- አራት ኪሎ ስትውል
ሰርክ ሞት ቢሆንም- የእኔ የጧት እድል
አዳራሹ አድባር እርቆታል፡፡ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው ባነር ካንድ ጎኑ በመልቀቁ የተነሳ እኩል የነበረውን ሚዛን ላይና ታች አድርጎታል፡፡ ከርቀት ‹‹አንቺም ዜሮ ዜሮ›› እያለ የሚጮህ ሙዚቃ ይሰማል፡፡
አቶ የሽዋስ ተከሳሽ የሆነ ይመስል ጸጉሩ የሱፍ ማሳ መስሏል፡፡ የአቶ ግርማ ፊት ግርማ ሞገሱን አጥቶ ኑግነቱን ብቻ ሲያስቀጥል፣ አቶ አንዱ አለም ፊት ላይ የሚታየው እርጋታና ቅዝቃዜ ደግሞ ‹‹እርጎ ጠጡ›› እያለ ይወሰውሳል፡፡
ከምርጫው በፊት በቀን አሥር ጊዜ ሲደውልላቸው የኖረው ንጉሥ ከምርጫው በኋላ ተደውሎለትም የማያነሳ መሆኑ ፕሮፌሰሩን ለከባድ ብስጭት ዳርጓቸዋል፡፡
ውይይቱ በተጀመረ ጊዜም….
መድረክ ላይ የተቀመጡት ፕሮፌሰር መልሱን መናገር ሲገባቸው ‹‹ለምን ተሸነፍን?›› በማለት ጠየቁ፡፡
ይሄም ጥያቄ ሲነሳ አቶ ግርማ አንገቱን መድፋት ፈልጎ ጭንቅላቱን አጠፍ ሲያደርገው ማጅራት ገትር የያዘው ይመስል ወገቡን ደፋ፡፡
በቅድሚያ የመናገር እድሉን ያገኘው አቶ አንዱ ዓለም አራጌ ‹‹በእኔ ግምት የተሸነፍነው ኢዜማን የሕዝብ በማድረግ ፈንታ የመንግሥት ፓርቲ ማድረጋችን እና ባልተገሩ ንግግሮቻችን የአማራን ሕዝብ ማስቀየማችን ይመስለኛል›› የሚል መልስ ሲሰጥ ፕሮፌሰሩ ‹‹አማራ የሚባል ሕዝብ አላውቅም›› ብለው በንዴት ጠረጴዛቸውን ሲወቅሩት በጠርዙ ቆሞ የነበረው የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ በጀርባው ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡
በማስከተል አቶ ግርማ ሰይፉ እጁን ካወጣ በኋላ ‹‹አልተሸነፍንም›› ብሎ መናገር ሲጀምር ‹‹ተደመሰስን እንጂ›› በማለት ፕሮፌሰሩ አሾፉበት፡፡
እሱ ግን በዚያው አቋሙ በመጽናት ‹‹ኢዜማ ተፎካካሪ ፓርቲ ሳይሆን አጋር ፓርቲ ሆኖ ለውጡንና ጠሚውን ሲደግፍ ሰንብቶ የብልጽግናን አሸናፊነት እውን አድርጓል፡፡ ስለሆነም ሕዝባችን ባይመርጠንም አጋር ድርጅታችን ስላሸነፈ ከጠሚው ጋር በመደራደር ሥልጣኑን ማጋራት እንችላለን›› በማለት ተናገረ፡፡
ይሄንንም ንግግሩንም በተግባር ለማረጋገጥ አስቦ ወደ ጠሚው ጋር በመደወል ሰላምታ ከሠጣቸው በኋላ ስለ ድርድር ሲያወራቸው ‹‹ባገኛችሁት ድምጽና ወንበር ልክ መደራደር እንችላለን›› ካሉት በኋላ ስልኩን ጆሮው ላይ ዘጉት፡፡ ያን ጊዜም ግርምሽ ከሕዝብ ድምጽ ባለፈም የእራሱም ድምጽ የጠፋው ይመስል ቃላት አልባ ሆኖ ቆዬ፡፡ ድንጋጤው ካለፈለት በኋላም  ‹‹ድርድሩን ከድምጽ ወደ አመጽ ማሸጋገር ይቻል ይሆን?›› የሚል ጥያቄ ይዞ ምናባዊ ጉዞ ሲያደርግ በኢዜማ ጥሪ ግርማ የተባለ ሕዝብ መስቀል አደባባይ ላይ ቁሞ ‹‹ዳውን ዳውን›› እያለ ቁጣውን ሲገልጽ ይታየው ጀመር፡፡
በመጨረሻም እጃቸውን ያወጡት አቶ ክቡር ገና ‹‹ኢዜማ የእራሱ የሆነ አገራዊ ዜማ ያለው ድርጅት ቢሆንም የብልጽግናን ግጥም ተቀብሎ ጠሚውን ሲያወድስና መራጩን ሲያንኳስስ ከከረመ በኋላ የምርጫው ቀን የእራሱን ግጥም ጽፎ ‹‹ተቀበል›› ማለቱ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ ድምጻዊው ሕዝብም የእኛን ግጥም በመቀበል ፈንታ በእራሱ ግጥም እንዲህ ብሎን ድምጹን ለብልጽግና የሰጠ ይመስለኛል፡፡
ቅንጅት ነኝ ስትል- ካንተ ተቀናጀሁ
ግንቦት ሰባት ስትሆን- ኤርትራ ተገኘሁ
አምና ግን በልጽገህ- አራት ኪሎ ስትውል
ሰርክ ሞት ቢሆንም- የእኔ የጧት እድል
በዘር ተለይቼ- ስገደል ስጠቃ
ያን ሁሉ እሪታዬን- ያንን ሁሉ ሲቃ
ዘር ተኮር አይደለም- ብለህ ስታበቃ
ለውጡ እንዳይናወጥ- አገሪቷ እንዳትፈርስ
ጠሚውን እንደግፍ-
ማለትክን ሰምቼ- ለውጡን እናወድስ
እኔ ያንተ አገልጋይ- እኔ ያንተ ሙሲባ
አንተ የጠላኸውን- አብሬ ጠልቼ- ኤርትራ የምገባ
አንተ የደገፍከውን- አብሬ ደግፌ- ከሞት የምስማማ
ቃልህን አምኜ- በልጽጌያለሁና- ክላልኝ ኢዜማ፡፡››
Filed in: Amharic