ኢትዮጵያ መቼ ይሆን ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚኖራት?
ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ፍትህ እንዲሰፍን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ አድሎአዊነትና ዘረኝነት እንዲወገድ፣ሕዝብ ከመፈናቀልና ከድህነት እንዲላቀቀቅ፣ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር እንድትሆን እና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሰፍኑ የሚያስችል ሥርዓት ለማምጣት ጠንክሮ ሠርቷል፤እየሰራም ነው፡፡የሃገሪቱ መሪ ‹‹ከባልደራስ ጋር ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን›› እያሉ በተናገሩበት ወቅት እንኳን ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከመታገል ቁርጠኛ አቋሙ ወደ ኋላ አላለም፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በ6ኛው አገር አቀፍ ቅድመ ምርጫ ሂደት (Pre-election process) ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂዶ ዝቅተኛውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት የማያሟላ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የምርጫ ሂደቱ የተበላሸ ከሆነ ውጤቱም በተመሳሳይ መንገድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ባልደራስ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል በምርጫው የተሳተፈ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ፓርቲያችን ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ባካሄዳቸው ከፍተኛ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ወቅት ሕዝብ ከጎኑ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አረጋግጧል፡፡አዲስ አበቤ ለድርጅታችን በአሳየው ደጀንነትም ፓርቲያችን እጅጉን ኮርቷል፡፡ ያነሳነውን አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ ጉዞ ሕዝባችን ከጎናችን በመሆን ስለሰጠን ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን፡፡ ለሰጣችሁንም ድምፅ ምሽጋናችን ከፍ ነው፡፡ ይህንኑ ወደ ፊትም አጠናክረን እንደምንሄድ በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን ።
ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ገንዘባችሁንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጭምር የለገሳችሁ የፓርቲው አመራሮች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች እጩዎች፣የምርጫው የቅስቀሳና የሎጂስቲክስ አካላት፣የባልደራስን የዴሞክራሲ ማዕዘን በመሆን የምርጫውን ሂደት ከሁለት ቀንና ሌሊት በላይ የተከታተላችሁ ወኪሎቻችን እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና የምናቀርብላችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በሌሎችም ዓለማት የምትኖሩ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ እና የአማካሪ ቦርድ አባላት ላደረጋችሁት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፣ ምክር እና አስተዋፆኦ ምስጋናችን እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡
‹‹አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው›› በሚል ዓላማ የጀመርነውን ጉዞ ገዥው ፓርቲ መሪዎቻችንን በማሥር ለማሰናከል ጥረት አድርጓል፡፡ነገር ግን ትግሉ የተነሳበትን ዓላማ ይበልጥ ከፍ አድርጎ በመቀጠሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገዙት ሃሳብ ሆኗል፡፡በሀገር ውስጥ ያላችሁ አባላት እና በውጭ ሃገር የምትኖሩ ድጋፍ ሰጭዎች የተሸረበውን ሴራ በጣጥሳችሁ በመውጣት፣ በሰላማዊ ትግሉ ፋና ወጊ የሆኑ መሪዎችን ቀንዲል ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረጋችሁ ናችሁና በድጋሚ የባልደራስ አመራር በእናንተ ደስታና ኩራት እንደሚሰማው ይገልጻል ።
በባልደራስ ፓርቲ ቅድመ ምርጫ ሂደት ጥናት እንደተረጋገጠው በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ የታጀበው ዝቅተኛውን የምርጫ መመዘኛ ደረጃዎች ያላሟላው የሰኔ 14/2013 ዓ.ም. ምርጫ የመጣውን ውጤት ማሳየት ችሏል። እንደሌሎቹ ጊዜዎች ሁሉ የዘንድሮውንም ምርጫ ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ምንም ቁርጠኝነት አለመኖሩን ፓርቲያችን ተገንዝቧል።
ከምርጫው ቀን ዋዜማ ጀምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የፓሊስ እና የመከላከያ አባላት የጦር መሣሪያቸውን ወድረው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የስነ ልቦና ጫና ሲፈጥሩ ሰንብተዋል፡፡ ይህም ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ›› እንደሚባለው በምርጫው ሰሞን ከነበሩ ኢዲሞክራሲያዊ ትዕይንቶች አንዱ ነበር።
ምርጫውን ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ጠቀሜታው በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት እና ተወዳድረው ለማሸነፍ ለሚፎካከሩት ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለሚወክሉት ሕዝብ ጭምር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ሲቀር የሕዝብ ነፃነት ይገፈፋል፡፡ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡በዜጐች መካከል የደረጃ ልዩነት እና መሠል ችግሮች ተፈጥረው ህዝብ በፍርሃት አረንቋ ውስጥ ይወድቃል።እነዚህን ችግሮችን ለማስወገድ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ሓላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የተከሰቱ ችግሮችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጥልቀት እየመረመረው ይገኛል። እስካሁን በደረሰበት ሁኔታ ምርጫው ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራት መኖራቸውን ፓርቲያችን ያምናል፡፡ ለአብነትም፡-
1. ድምፅ አሰጣጥንበ ተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት የተሰየሙት የምርጫ አስፈፃሚዎች የገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ የሚረዳ ገለጻ ሲያካሂዱ የፓርቲዎች ወኪሎች እርምት እንዲያደርጉ ቢያስገነዝቡም አስፈፃሚዎች ብልሹ አሠራራቸውን አለማስተካከላቸው በችግርነት የታየ ጉዳይ ነው፡፡
2. በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያልነበሩ አዳዲስ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ ማንነታቸው የማይታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ሲሰጡባቸው መቆየታቸው፣
3. አቅመ ደካሞችን፣ በእድሜ የገፉትን እና የአካል ጉዳተኞችን የመንግሥት ካድሬዎች ከምርጫ ህጉ ውጭ በማገዝ ስም በሚስጥር ድምፅ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ይዘዋቸው በመግባት ጫና እየፈጠሩ የሚፈልጉትን ማስመረጣቸው፣
4. በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የባልደራስን የምርጫ ውጤት ቁጥሮች እየቀነሱ እንዲጻፉ መደረጋቸው፣
5. ባልደራስ የተመረጠባቸውን ወረቀቶች በስልት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ወይም የባከኑ ውጤቶች እንዲሆኑ መደረጋቸው፣
6. በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ያለው የመራጩ ቁጥር ቀድሞ የሚታወቅ ሆኖ እያለ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከመራጮች ቁጥር እንዲያንስ መደረጉና ወረቀቱ እስኪመጣ መራጮች በፀሀይ፣ በዝናብና በብርድ በርካታ ሠዓታት እንዲቆዩ መሆናቸው የተወሰኑት ሳይመርጡ ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል፡፡
7. ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች በርካታ በመሆናቸውና በምርጫ ወረቀቱ ላይ በምርጫ አስፈፃሚዎች በቂ እና ግልጽ ማብራሪያ ባለመሰጠቱ የምርጫ ወረቀቱ በውስጡ ምን ያህል እጩዎች እንደያዘ አለመታወቁ ለመራጮች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር ሆኗል፡፡ይህም መራጩ በግልጽ ድምፅ የመስጠት ነፃነት እንዳይኖረው አድርጓል፡፡በዚህም የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲባክኑ ወይም መራጩ ላልፈለገው ድምፅ እንዲሰጥ ሆኗል፡፡ከላይ የተጠቀሱት በምሳሌነት ከሚነሱት ችግሮች እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለችግረኛ ሰዎች የተለያዩ መደለያዎች በመስጠት የሕዝብን ገንዘብ ለሥልጣን መሸመቻ ማድረጉ በምድር ቀርቶ በፈጣሪ ዘንድ ይቅር የማያሰኝ ተግባር ነው። በሌሎች ጊዜዎች የድሆችን ችግር ለማስወገድ ትኩረት የማይሰጠው ገዥው ፓርቲ በምርጫ ሠዓት ብቻ ማባበያ ይዞ መቅረቡ ነዋሪውን ለመደገፍ ሳይሆን ሥልጣኑን ለማቆየት የተጠቀመበት ዘዴ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ከምርጫ 97 ወዲህ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲበዙ የተደረገባቸው ምክንያቶች ኗሪዎች በረጃጅም ሰልፎች ላይ በመቆየት እንዳይንገላቱ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ምርጫ ጣቢያዎች እንደአሸን እንዲፈሉ በተደረገበት ወቅት መራጮችን ለማሰላቸትና ለማስመረር ይሁን ተብሎ የተከናወኑት ማጓተቶች ድምፅ ሰጭዎች እንዲንገላቱ ማድረጉ የሚያስተዛዝብ ሁኔታን ፈጥሯል። ቀን በፀሀይና በዝናብ፣ በምሽት እና በሌሊት ደግሞ በብርድ እንዲንገላታ የተደረገበትን ደባ ተቋቁሞ የተሰለፈው አዲስ አበቤ ድምፁን ለማን እንደሰጠ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንቅቆ ያውቃል ።
በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ለማሰላቸት ሆን ተብሎ በተፈጠረው ተስፋ የማስቆረጥ ሂደት ሳትመርጡ ለቀራችሁ፣ ሆን ተብሎ በተሠራ ደባ ካርድ እንዳታወጡ የተደረጋችሁ እና መምረጥ ያልቻላችሁ፣ ጊዜ በማጣት ካርድ ላልወሰዳችሁ፣እንዲሁም በአገራችን ሁኔታ ተስፋ በመቁረጥ የዜግነት ግዴታ መወጣት ያልቻላችሁ የናንተ ድምፅ ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግሮች መውጫ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሆኖ ሳለ በመቅረቱ በእጅጉ ያስቆጫል።
የአሁኑ የኦህዴድ/ብልጽግና አባት የሆነው ህውሃት/ኢህአዴግ በምርጫ 2007 የ100% የአሸነፍኩ ጉዞ ከ2ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት እንዳልቻለ የ3 ዓመት ትውስታችን ነው።በህዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ራሱን ይሸነግል ይሆናል እንጂ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝ ከዚሁ ከሀገራችን ታሪክ መረዳት ይቻላል። ለነፃ፣ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዳኝነት የሚሰጠው ሕዝብ ነውና።
6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ‹‹ነፃ፣ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አደርጋለሁ›› ይል የነበረው ኦህዴድ/ብልጽግና በምርጫው ዙሪያ እየተፈጸሙ ያሉት ድርጊቶች የማያልቅ ሀሰቱ ማሳያዎች ሆነዋል። ዜጎች እየተገደሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ እየተራቡ እና እየተደፈሩ፣የውጭ ወራሪ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ሀገራችን ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ እየሆኑ ‹‹ኢትዮጵያ አሸንፋለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል፡፡ … ›› የተሰኙት አባባሎች ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ከማለት ያለፈ ትርጉም የላቸውም።
የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰጠን ታላቅ ድጋፍና ፍቅር፣ ክብርና ሞገስ አሁንም ደግመን እናመሰግነዋለን። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እና አባላት በሕዝብ ፊት በተግባር ጭምር እየተፈተንን የሰላማዊ ትግል አርበኞች መሆናችንን አስመስክረናል፡፡
የዴሞክራሲ ኃይሎች ትንንሽ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለማይቀረው የሰላማዊ ትግል ተደጋግፈን ሕዝብን በማስተባበር እንድንታገል ዛሬም እንደቀድሞው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።
ብሔራዊ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም. የተካሄደወን የምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ባልደራስ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን በአክብሮት ይገልጻል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ!!!
ሰኔ 18/2013ዓ.ም.