>
5:26 pm - Thursday September 17, 7959

ታላቋ ሐረር እና በደደቢት በረኸኞች የተቀበሩ እውነቶቿ...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ታላቋ ሐረር እና በደደቢት በረኸኞች የተቀበሩ እውነቶቿ…!!!

አሰፋ ሀይሉ

ሐረር ከተማ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ያፈራች የሶስተኛው ክፍለጦር መናኸሪያ በመሆኗ ምክንያት ለወያኔ የበቀል በትር እስክትዘጋጅ ከ1983 እስከ 1987 ድረስ፣ ልክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ብሔር ቀለም ቋንቋ ሳይለዩ በጋራ በሠላም እየሰሩና እየነገዱ እንደሚኖባቸው እንደማናቸውም የኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች ሁሉ – በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተሞች ጋር አብራ በሶስተኛነት «ነፃ ክልል» ተብላ የተሰየመች የኢትዮጵያውያን ሁሉ መናገሻ የሆነች ክልል ነበረች፡፡
ወያኔ በእነዚያ ጥቂት ዓመታት የሰዉን ስነልቦና አጠና፣ የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ከሐረር ሕዝብ ላይ መፋቅ እንደማይችል አወቀ፣ እና ለጠባብ የብሔር-ብሔረሰብ ትርክቱና አደረጃጀቱ ሐረር ከፍ ብላ ከሥልጡን ከተሜ ሕዝቦቿ ጋር ተሳለቀችበት፡፡ በሐረር ከተማ በነጻነት ተዋዶና ተከባብሮ የማይኖር የሰው ዘር የለም ቢባል ይቀል ነበር፡፡
ሐረር ከተማ ቀዝቀዝና ለስለስ ባለ ለጤና ተስማሚ ወይናደጋ የአየር ንብረቷ በሐርጌሳና ጂቡቲ በኩል ለሚመላለሱ አረቦች ማረፊያ ታዛቸው ነበረች፡፡ ሐረር ከተማ በወታደራዊው ዘመን የጦር አማካሪዎች፣ ሐኪሞችና የጦር አካዳሚ መምህራን ሆነው ለመጡ በርካታ ኩባውያን እጅግ ተወዳጅ መኖሪያቸው ነበረች፡፡ በየሆስፒታሎቹና ካምፖቹ ለሚኖሩ ራሺያኖች ዘና የሚሉባት፣ ከሞቃታማዋ ዝቅ ያለ የድሬዳዋ ሙቀት ከፍ ብለው ነፋሻ አየርን የሚቀዝፉባት ሰገነታቸው ነበረች፡፡
በመምህርነት ሙያ ለመጡ በርከት ያሉ ህንዳውያን ሐረር ውብና ተወዳጅ ከተማቸው ነበረች፡፡ የአለማያ ዩኒቨርሲቲ ከየዓለሙ ማዕዘን የማይስበው ዓይነት ምሁር አልነበረም፡፡ በእኛ ዘመን ሠርግ ሠርጎ በዓለማያ ሀይቅ ላይ ሄዶ ፎቶ የማይነሳና ቪዲዮ የማይቀረጽ ተጋቢ፣ ከዓለማያ ሀይቅ የሚቆረጡ ውብና ረዣዥም ቄጤማዎችን በቤቱ ወለል ላይ ያልነሰነሰ፣ የዓለማያ ሀይቅን ዓሳዎች ያላወራረደ የሐረር ነዋሪ አይገኝም ነበር፡፡
ጥንታዊውን የጀጎል ግንብ፣ የፈረንሣዊውን ባለቅኔ የአርተር ራምቦድን መኖሪያ ቤት፣ የሐረር ከተማን አጠቃላይ መሳጭ መስህቦች ሁሉ ሊጎበኛት የማይመጣ የዓለም ዜጋ አልነበረም፡፡ ከአሜሪካው እስከ ቻይናው፣ ከህንድ እስከ እብድ ሐረር ውብ መዳረሻቸው ነበረች፡፡ በሐረር የማይኖር የኢትዮጵያ ብሔረሰብም አልነበረም፡፡ ብዙ የኤርትራ ተወላጆች በሐረር ነባር ነዋሪዎች ሆነው በሠላምና በፍቅር ይኖሩ ነበር፡፡
ብዙ የትግሬ ተወላጆች፣ ብዙ ቤተ ጉራጌዎች፣ ብዙ ስልጤዎች፣ ብዙ ሃዲያዎች፣ ብዙ ጋምቤላዎች (በተለይ በፖሊስና ወታደራዊ ክፍሉ ውስጥ)፣ በርካታ ኦሮሞዎች፣ አደሬዎች፣ የአማራ ተወላጆች፣ በርካታ ሶማሌዎች (የኢትዮጵያም የሞቃዲሾም ሶማሌዎች)፣ እና በተለይ በጂቡቲም በሶማሌም በኩል የሚመጡ የንግድ ሸቀጦች የሚራገፉባት የንግድ ማዕከልም ስለነበረች – ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ (ብሄርና ብሔረሰብም ካልነው) የማይኖርባት የለም ነበር በነጻይቱ የሐረር ከተማ፡፡
ለኦጋዴን፣ ቀብሪደሃር፣ ደገሃቡር፣ ፊቅ፣ ነጌሌ፣ ወዘተ ወቴዎች የደረቀ የጫት ቅጠል እየተወቀጠ እንደ ጌሾ ዱቄት የሚላከው ከሐረር ነበር፡፡ ከሐረር አወዳይ የሚቀጠፈውን የቆንጆ ሴት ጭን የሚመስለውን የሐረር ጫት በየዕለቱ የሚጠባበቁ ሶማሊዎች ለሐረር ለብቻዋ በየዕለቱ ዱዓቸውን ያደርሱላት ነበር፡፡ በሐረር ከተማ የመስጊዶቿ ብዛት፣ የቤተክርስትያኖቿ ማማርና ብዛት፣ የሰዉ ተፋቅሮ ተከባብሮ ተዋዶና ተዋህዶ መኖር ለጉድ ነበር! ስለ ሐረር ሲወራ ፍራፍሬዎቿና ቆንጆዎቿ፣ ዛሬ አውቆህ ዛሬውኑ ቤተሰቡ የሚያደርግህ እንግዳ-ተቀባይና ሰው-ወዳድ ነዋሪዎቿ፣ ሌላ ቀርቶ ሰው-የለመዱ ጅቦቿና መዓት ዓይነት የቤት እርግቦቿ ነበሩ ቀድመው የሚታሰቡት፡፡ ሐረር የሰብዓዊ እሴቶች ሁሉ ምድረ ገነት ነበረች፡፡
ወያኔ መጣችና – ይህን ሁሉ አስተዋለች፡፡ እና ላሰበችው ኢትዮጵያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጎሳ፣ በቋንቋ ሸንሽኖ ለመግዛት ህልሟ ሐረር ከነ ፍቅር አድባሯ ትልቅ እንቅፋት እንደምትሆንባት አወቀች፡፡ በዚህም ላይ ወያኔን በቁሟ የሚያቃዣትን ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ያፈራው ታላቁ የኢትዮጵያ ኩራት የነበረው የኦጋዴን አንበሣ ክፍለጦር መዲናም ነበረች ሐረር፡፡
ወያኔ ይህን ቂሟን ያብስብሽ ሲላት፣ ወያኔ አዲስ አበባን በግንቦት 20 ተቆጣጥራ ሀገሪቱን በቁጥጥሯ ሥር ስታውል – ጀግናው የሐረር ሕዝብ «እምቢኝ ለሀገሬ!» ብሎ እጅ አልሰጥም በማለት ተዋግቷታል፡፡ እና ያ ጥልቅ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የወለደው የሐረር ሕዝብ እምቢ-ባይነት በወያኔ ዘንድ ከፍ ያለ ቂም-በቀል እንዲደገስላት ተጨማሪ ምክንያት ሆነ!
ብዙው ሰው ከቶውኑም አልጠረጠረም ነበር፡፡ ሐረር ከተማ – ከድሬዳዋና ከአዲስ አበባ ተነጥላ ከነጻ ክልልነት ትሰረዛለች ብሎ፡፡ ወያኔ ግን የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ተሰርዞ ህገመንግስቱን ስታጸድቅ – አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ብቻ የፌዴራሉ ከተሞች መሆናቸውን አወጀችና – በቻርተሩ ከአዲሳባና ድሬዳዋ ጋር አብራ ነጻ ክልል የነበረችውን ሐረር ከተማን – «ሐረሪ» የሚል በከተማው ነዋሪ ብዙም ያልተለመደ አደሪኛ ቃልን አስረግጣ ሐረር ከተማን በሙሉ «ሐረሪ ክልል» በማለት ለአደሬዎች ሰጠች!
በወቅቱ 80 በመቶ የሚሆነው የሐረር ነዋሪ ይህን ነገር እንደ ቀልድም አድርጎ ነበር የወሰደው፡፡ በአደሬዎቹ በኩልም ብዙ እንቅስቃሴ አልነበረም መጀመሪያ ላይ፡፡ እየቆየ ግን ቀልድ መሆኑ ቀርቶ፣ ዓይኑን ያፈጠጠ እውነት ሆኖ መጣ፡፡ አደሬዎች ራሳቸው በወቅቱ የከተማው ነዋሪ በሙሉ በእነርሱ አገዛዝ ሥር ተላልፎ እንደተሰጣቸውና፣ ያንንስ ለማድረግ አቅሙና ድፍረቱ ይኖረናል ወይ ብለው ተጠራጥረው ነበር፡፡
ከጥቂቶቻቸው በስተቀር – ለማይሆን ነገር ከከተማው ሕዝብ ጋር ጠላትነት አናተርፍም ብለው አርፈው ጥጋቸውን ይዘው የሩቅ ድጋፍ እየሰጡ የተቀመጡት አደሬዎች ይበዙ ነበር፡፡ ነገር ግን በሐረር ከተማ ምሥራቅ እዝ ላይ የሀገሪቱን 1/4ኛ ሠራዊት ያሰፈረችው ወያኔ – በመትረየስ ፓትሮሎች እንደተወረረ የጠላት ከተማ እያንዣበበች – አይዟችሁ፣ በእኔ ይሁንባችሁ፣ ከእናንተ አቅም በላይ የሆነውን ለእኔ ላኩት፣ ዋጋውን እሰጠዋለሁ፣ የደርግ ርዝራዥ ካለ እጠርገዋለሁ! ብላ የልብ ልብ ሰጠቻቸው፡፡
እና የማውቃቸው አደሬዎች ራሱ – በአንድ ዓይናቸው በይሉኝታ እያፈሩ – በሌላ ዓይናቸው ግን ያው የተሰጣቸው ‹‹ልዩ ጥቅም›› ነውና ዓይናቸውን እያሹ ገቡበት ከተማዋ የእኛ ነች፣ ሕዝቡም የእኛ ነው፣ የምንመርጠውም፣ የምንመረጠውም እኛ ነን – ብለው የመንግሥት አስተዳደር መሥሪያቤቶችን ሁሉ ቀስ በቀስ ተቆጣጠሩ፡፡ ኦነግ ከሐረርጌ ሲመነጠር ከወያኔ ጋር የተባበሩ የኦፒዲኦ የኦሮሞ ብሔርተኞችም ከአደሬዎች ጋር በየከተማው ተቋማት አብረው ተሰገሰጉ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ከዓይናውጣዎቹ ፖለቲከኞች የተለየው አብዛኛው አደሬ እና አብዛኛው ኦሮሞ – እና የተቀረው የሐረር ሕዝብ – ጉዳዩ በሕገመንግሥት ደረጃ የጸደቀ መሆኑን ከቁብ ሳያስገባ በተለመደው ሐረራዊ ያልጣሙትን ነገሮች በማጣጣልና ንቆ-በመተው ዘዬ – ጉዳዬም ሳይላቸው የራሱን ኑሮ በሠላም መኖሩን ቀጥሎ ነበር፡፡
የከተማውን ነዋሪ ሁሉ እንደ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም የግል ቤተሰብ አድርጋ ከቆጠረችው፣ እና ታንኩም መትረየሱም በእጇ ከገባው ከወያኔ  ጋር የሚደረግ ትግል አይታሰብም ነበር፡፡ የሻዕቢያም የተወሰኑ ጦሮች ከወያኔ ጦሮች ጋር ተዳብለው በሐረር ነበሩ፡፡ በወቅቱ የተሸነፈችውና እጅ የሰጠችው ሐረር ከተማ ብቻ አልነበረችም፡፡ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በጠባቧ የደደቢት ጎሰኛ በወያኔ የተሸነፈችው አጠቃላይ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ እና የሐረር ከተማ ሰው ለባለጊዜዋ ለወያኔ (እና የወያኔ ደንገጡሮች ሆነው በሐረር ከተማ ለነገሱት አደሬዎች) ሁሉን ነገሩን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ የዕለት ጉርሱን ለማቅናት ደፋ ቀና ማለቱን ቀጠለ፡፡
የሚገርመው ነገር ወያኔ ሐረር ከተማን ለአደሬዎች ስትሰጥ – በሐረር ከተማ 19 (አስራ ዘጠኝ) ቀበሌዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ አደሬዎች የሚኖሩባቸው የጀጎል ቀበሌዎች 7 ቀበሌዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ያውም  እኮ እነዚህ 7ቱ ቀበሌዎች የአደሬ ተወላጆች በብዛት የሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ነበሩ ማለታችን ነው እንጂ፣ አደሬዎች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮችም የሚኖሩባቸው ቀበሌዎች ነበሩ፡፡ እንግዲህ ወያኔ – 7 ቀበሌ የማይሞሉ አደሬዎችን አንስታ ነው በተቀሩት እና እጅግ ሰፋፊ በሆኑት የሐረር ከተማ 12 ቀበሌዎች ላይ ገዢ ብሔር አድርጋ የሾመቻቸው፡፡
ወያኔዎች በ1987 ህገመንግሥታቸውን አጽድቀው ሐረር ከተማን ከነጻ ክልልነት (የፌዴራል ከተማነት) ሰርዘው፣ ለአደሬዎች «ሐረሪ ክልል» ብለው በሰጡበት ወቅት፣ በሐረር ከተማ በነበሩ ቀበሌዎች አደሬዎች ይኖሩባቸው የነበሩት የትኞቹ እንደነበሩና ሌሎች (ከአደሬ ውጭ ያሉ ብሔረሰቦች) ይኖሩባቸው የነበሩት ቀበሌዎች የትኞቹ እንደነበሩ እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ፡-
© ቀበሌ 01 – መድረሳ (ሠንጋበር) – አደሬዎች + ኦሮሞዎች በብዛት ይኖሩበታል፤
© ቀበሌ 02 – ጀጎል ውስጥ – አደሬዎች በብዛት የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 03 – ጀጎል ውስጥ – አደሬዎች + ሌሎችም በብዛት የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 04 – ጀጎል (እና 1ኛ መንገድ) – አደሬዎችና ሌሎችም በብዛት የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 05 – ጀጎልና ሸዋበር – አደሬዎች + ኦሮሞዎች + እና ሌሎችም የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 06 – ጀጎልና ከጀጎል ዙሪያ – አደሬዎች + እና ሌሎችም የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 07 – ጀጎልና ከጀጎል ዙሪያ – አደሬዎች + ኦሮሞዎች + እና ሌሎችም የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 08 – ከጀጎል ውጭ፣ ከፈላና ወዲህ ከርቸሌ ሰፈር – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 09 – ከጀጎል ውጭ፣ ሸንኮር – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 10 – ከጀጎል ውጭ፣ ሥላሴ፣ ራስመኮንን፣ ቤተመንግሥት፣ ወዘተ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 11 – ከጀጎል ውጭ፣ አቦከርና ቲቲአይ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 12 – ከጀጎል ውጭ፣ ቀላዳምባ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 13 – ከጀጎል ውጭ፣ አርበኞች፣ ኦጋዴን አንበሣ፣ ጥምቀተባህር፣ ወዘተ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 14 – ከጀጎል ውጭ፣ ቦቴና አካባቢው – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 15 – መንፈሳዊ፣ ሚካኤል፣ እስከ እንደራሴ (ኩባ ካምፕ) – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 16 – ጠቅል፣ ችግኝ ጣቢያ፣ ሐኪምጋራ፣ ሳንፊል፣ ሐረርቢራ፣ ወዘተ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 17 – ጁንየር ት/ቤት፣ አዲሱ ስቴዲየም፣ አራተኛ፣ ወዘተ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 18 – ሳንፊል፣ አዲስ ሰፈር፣ አዳዲስ ቀበሌዎች፣ ወዘተ – ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፤
© ቀበሌ 19 – ሐማሬሳ – በብዛት ኦሮሞዎች + እና ከአደሬ ውጭ ሌሎች ብሔሮች የሚኖሩበት፡፡*
እንግዲህ ወያኔ የሐረር ከተማንና ለዘመናት ከመላው ኢትዮጵያ መጥተው ዋናዋን የሐረር ከተማ እየተባለች የምትጠራዋን ሐረር (ጀጎል ውስጣ ያሉ ተቋማትንና የተከማ መሠረተ ልማቶችን ጨምሮ) የቆረቁሩትን – በህዝብ ቁጥርም፣ በአሰፋፈርም፣ በማንኛውም የከተማ ይዞታና ኑሮ መለኪያ ከሐረር ከተማ ከ80% በላይ የሚሆኑትን ነዋሪዎቿን – በቁጥርም በአሰፋፈርም 20% ለማይሞሉት ለጀጎል አደሬዎች አሳልፋ የሰጠችው ይህን ዓይነቱ ያፈጠጠ እና ማንም የሐረር ሰው ሊመሰክረው የሚችለው እውነታ ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የጠባቧየደደቢት ውላጅ የወያኔ የመንግሥቱ ኃይለማርያም የቂም በቀል በትር ያረፈባት የሐረር ከተማ፣ አብዛኛውን ሕዝብ የያዙት ነዋሪዎች ለአናሳዎቹ አደሬዎች «የሐረሪ ክልል» ተብላ በ1987ቱ የወያኔ ህገመንግሥት መሰጠቷን በየብሔረሰቡ ስታቲስቲካዊ መረጃ አስደግፈው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም «አፓርታይድ በኢትዮጵያ» ሲሉ በትክክለኛ ስሙ የጠሩት፡፡
«አፓርታይድ» ማለት ጥቂቶች በዘርና በቋንቋ ተለይተው፣ የብዙሃኑን መብት ጨፍልቀው እንዲገዙ የሚፈቅድ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ በሐረር ከተማ ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት፣ እና የሚያስደነብራትን የመንግሥቱ ኃይለማርያምን መንፈስ ለመቅበር የሠራቸው ታሪክ ይቅር የማይለው ደባና ሸፍጥ ይህ ነበር! ይህ ወያኔያዊ ሸፍጥ በሐረር ከተማና በነዋሪዎቿ ላይ ከተፈጸመ ስንት ዓመት ሆነው? ከ1987 ዓ.ም. እስከ አሁን 2021 ዓ.ም. – 24 (ሃያ አራት) ዓመታት ብቻ! ይህ የአንድ ጎረምሳ ዕድሜ ማለት ነው! በዚህ በአንድ ጎረምሳ ልጅ ዕድሜ ነው ወያኔ ይህን ሁሉ አፓርታይዳዊ ሸፍጥ በምስራቅ ኢትዮጵያዋ መዲና በሐረር ከተማና ነዋሪዎቿ ላይ የፈጸመችው፡፡
ዛሬ በወያኔ መትረየስ በአብዛኛው የሐረር ሕዝብ ላይ በገዢነት የሥልጣን መንበር የወጡት አደሬዎች ምን ያህሉን የሐረር ሕዝብ አማርረው አፈናቅለዋል? ዛሬ አደሬዎች በ24 ዓመት ያገጠጠ የተስፋፊነት ዘመናቸው ምን ያህሉን የከተማውን ክፍልና ሕዝብ በራሳቸው እጅ አስገብተዋል? ምን ያህሎቹ ኢንቬስትመንቶች በአደሬዎች እጅ ናቸው? ምን ያክሉ ስልጣን በአደሬዎችና በኦፒዲኦዎች እጅ ወድቋል? (ስማቸውን ሺህ ጊዜ ቢቀያይሩትምና አሁን ኦሮሞ ብልጽግና ቢባሉም ያው ኦፒዲኦ መሆናቸውን አይቀይረውም ብዬ ነው በዚያው በነባሩ ስማቸው የምጠራቸው!)፡፡
ይህን የታሪክ ሸፍጥ እንዳልነበረ፣ ፍጹም እንዳልተፈጠረ፣ በጭራሽ እንዳልተከሰተ ቆጥሮ – ህገመንግሥት፣ ህገመንግሥት እያሉ በመለፍለፍ ይህን ከሥሩ የተበላሸ ዘረኛና ጎሰኛ ሥርዓት ተሸክሞ መጓዝ ይቻላል ወይ? እስከመቼ? ለመሆኑ የህዝብን የማስታወስ ብቃት እስከመጨረሻው በ‹‹ፖለቲካል ብሬይንዎሺንግ›› አጥቦና ፍቆ እስከምን ድረስ መጓዝ ይቻላል? የተዛባውን ግፍ የተፈጸመበትን ታሪክ የሚያስተካክለው ማነው?
ዛሬ የግፍ አቀባዮችና ደጋፊዎች ሆነው የቆሙት እነዚሁ በወያኔ ሸፍጥና ግፍ የተመሠረቱ ጎሰኛ «ክልሎች» አይደሉም ወይ? ይህን የቆሸሸ የደደቢት በረሃ የወለደው አፓርታይዳዊ ሥርዓት በሚገባ ተረድቶ፣ ነቅቶ፣ ተደራጅቶ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለማውረድ የሚነሳ ትውልድስ መቼ ነው የሚነሳው? ወይስ እንደተባለው «ሾርት ሜሞሪ» ብቻ ያለን አጭር ተመልካች፣ አጭር አስታዋሽ፣ ባለ አጭር መነጽር፣ ባለ አጭር አንጎል፣ አጭሬ ህዝቦች ነን ወይ ኢትዮጵያውያን?
ለእነዚህ ያልተመለሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያለበት ትውልዱ ነው! ስለመጪዋ ኢትዮጵያ መጠየቅ የሚገባው ኢትዮጵያዊው ትውልድ! በወያኔ የተተበተበለትን የደደቢት አፓርታይዳዊ አገዛዝ ጀርባው እስኪጎብጥ ተሸክሞ፣ ወያኔ-ገዳይ እያሉ መፎከር – ለባለ «ሾርት ሜሞሪ» ሕዝብ የተሰጠ የውርደት ካባ ነው፡፡ ያለፈው ትውልድ የራሱን የክብር ታሪክ ሠርቶም፣ ጽፎም አልፏል፡፡ እውነቱን የምንናገረው የራሱን ታሪክ ለመሥራትና ለመጻፍ የሚነሳ ትውልድ ወደፊት ከተገኘ በማለት ነው፡፡
ይህ በደደቢታዊው የውርደት አፓርታይዳዊ ሥርዓት ውስጥ ያለፍን የባከንን ትውልዶች የእውነት ድምጽ ነው፡፡ ይህ ወያኔ ከደደቢት ጎጠኝነትና ጎሰኝነቷ ጋር የፍቅር ከተማዋን ሐረርን ሣትረግጥ በፊት የነበረችው፣ እና በህገመንግሥት-ስም ከኢትዮጵያውያን ዓይን ለመሰወር የተሞከረው እውነተኛው የሐረር ከተማ የግፍ ታሪክ ነው፡፡ ግፉ ቀጥሏል፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡
ከትናንቱም የወያኔ ደደቢቶች ግፍና ሸፍጥም አልፎ ዛሬ – አደሬዎችን ጀጎል መንደሮች ውስጥ ዘልቆ እየገባ በቀለሞቹ አሸብርቆ በሳላቸው፣ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቴምብሮች ላይ በማውጣት ከማንም ቀድሞ ባሳወቃቸው በታላቁ የኢትዮጵያ እጅግ የተከበረ የጥበብ ሎሬት ሜይትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የታነጸውና ሐረር ከተማን ከጥንታዊት ጠባብ የፈራረሰች የጀጎል ከተማነት አውጥተው፣ ታላቅ ሰፊ የኮራችና የደራች ሥልጡን ዘመናዊ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከተማ ያደረጓት ባለውለታዋ፣ የአድዋው ጀግና የልዑል ራስ መኮንን መታሰቢያ ሐውልት – ከነታሪካቸው፣ በህዝቡ ላይ ፈራርሷል! የያኔዎቹን የወያኔዎች መትረየስ አሁን በተረኞቹ እጅ ተደግኖ ነው ሐረር ከተማና ታሪካዊ እውነታዋ እየፈራረሱ ያሉት፡፡
ከታሪክ የማይማሩ ያንኑ የቀደመውን ታሪክ ይደግሙታል፡፡ ማለት ይኸው ነው፡፡ ያን አስቀያሚ የደደቢቶች ታሪክ እየደገምነው ነው፡፡ አዕምሯችን አጭር ተብሎ እስኪዘበትበት ድረስ ታሪካችንን ረስተናል፡፡ አዋርደናል፡፡ ለሸፍጠኞችና ለዘረኞች አሳልፈን ሰጥተናል፡፡
ሕዝባችን ከታሪክ እንዲማር፣ የተጫነበትን የደደቢቶች የሸፍጥና የጎሰኝነት ድሪንቶ ከላዩ ገፍፎ የራሱን አዲስ የሠለጠነ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ እንዲጽፍ፣ መቼውኑም በጠባብ ዘረኞች የጥላቻ በትር ቅስሙ ተሰብሮ ከታላቅ ታሪኩና ሀቁ ጋር ወድቆ እንዳይቀር፣ በመንፈስና በእውነት በርትቶ እንዲነሳ፣ ይህ የተጫነበት የግፍና የሸፍጥ ታሪክ እስከወዲያኛው እንዲያበቃ – የበዛ ምኞቴ ነው፡፡
የፍቅር አምላክ በግፍ እውነቶቿ የተቀበሩባትን የፍቅር ከተማውን ሐረርን ያስብ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡
«ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም፡፡» 
መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic