>

የወልቃይት ስትራቴጅክ ጠቀሜታና የውጭ ኃይሎች የፖለቲካ ሴራ.. !!! (ንጉሱ አያሌው)

የወልቃይት ስትራቴጅክ ጠቀሜታና የውጭ ኃይሎች የፖለቲካ ሴራ.. !!!

ንጉሱ አያሌው

  በዚህ ትንታኔ ለአንባቢያን መሰረታዊ ግንዛቤ ያመች ዘንድ ‹ወልቃይት› እያልን የምንጠራው አካባቢ ሰቲት ሁመራን፤ ጠገዴንና ጠለምትን ያካትታል፡፡ በዚህ ቀጠና እንደ አማራ ቀዳሚ ፍላጎታችን የተነጠቀ ማንነታችንን ማስመለስ ሲሆን፤ አማራ በመሆናቸው ብቻ በትህነግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምባቸው የኖሩ ወገኖቻችን ከቀጥተኛ የህልውና አደጋ ተጋላጭነት ነጻ ማድረግ፣ እንዲጠፋ ሲሰራበት የኖረውን አማራዊ ማንነታቸው ዳግም አብቦ፣ የተጎዳ ሥነ-ልቦናቸው ተጠግኖ አማራዊ የአስተዳደር ነጻነታቸው እውን ሁኖ ማየትና ለሠላሳ ዓመታት ለተፈጸመው ግፍና በደል የፍትሕና የካሳ ጥያቄ ያለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሁኖ፣ በዚህ ጽሑፍ የአካባቢውን ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ እንመለከታለን፡፡
ጉዳዩ ከዚህም አልፎ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ጉዳይ ስለመሆኑ በማስረጃዎች እንፈትሻለን፡፡
ወልቃይት የቀጣናዊ ፖለቲካዊ መስፈንጠሪያ ማዕከል እና የብሔራዊ ደኅንነታችን አስኳል ስለመሆኗ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካን የመወሰን አቅምም አለው፡፡ ትልቁ ጉልበቱ ለጂኦ-ፖለቲክሱ ያለው ጠቀሜታ ነው፡፡ የተከዜ-አጥባራ ንዑስ ተፋሰስ ድንበሮች ይህን አካባቢ በሰፊው ያካልላሉ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱዳን በዚህ ተፋሰስ በርካታ ከተሞቻቸውን ያዳርሳሉ፡፡ ዋናው መነሻና ማዕከሉ ግን ወልቃይት ነው፡፡
በሰብል ምርት አቅሙ የአፍሪካን የግብርና ታሪክ የቀየረ አካባቢ ስለመሆኑ ምሁራን በጥናቶቻቸው መስክረዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ የኢትዮጵያን ግብርና ልማት ለማምጣት ሲካሄድ ከነበረው ጥረት አንዱ ‹Comprehensive Package Project (CPP)› ነበር፡፡ ይህ ፕሮጀክት በተመረጡ የኢትዮጵያ ለም አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የግብርና ልማት ሥራን በማከናወንና ትርፍ እህል በማምረት በምግብ እህል ራስን መቻል፣ ለውጭ ንግድ ማቅረብና ለሌላው መማርያ መሆን በሚል ዓላማ የተጀመረ ነበር፡፡
እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንዲካሄዱ ከተመረጠበት ቦታ አንዱ የበጌምድሩ ሁመራ (Humera Agricultural Development Unit)፤ በዛሬዋ ኤርትራ ጋሽ ባርካና ታህታይ አዲያቦ (GBADU, TARDU) ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከፍተኛ የሆነ የመንግሥትና የብድር ገንዘብ ወጭ ተደርጎበት ሲካሄድ የነበረው የግብርና ልማት ፕሮጀክት አንዱና ዋነኛው የወልቃይት ሁመራ ፕሮጀክት ነበር፡፡ በዚህ ፕሮጀክት የተነሳ ነበር የአፍሪካን የግብርና ታሪክ የቀየረ ሰፊ ምርት ማግኘት የተጀመረው፡፡ ይህ እንድምታ በነጻነት ራሷን ችላ በቆመች ሀገር፣ በመኪና (ትራክተር) በማረስ የሰፊ ግብርና ምርት ባለቤት የመሆን ተምሳሌት ለሆነችው ኢትዮጵያ ወልቃይት ትልቅ የግብርና አቅም ሊሆናት ችሏል፡፡
ከዚህ የምርት አቅሙ በተጨማሪ ወደጎረቤት ሀገር ሱዳን ለመሻገር ወሳኝ አካባቢ በመሆኑ ከዘውዳዊው ሥርዓት ማክተም በኋላ በአካባቢው መንቀሳቀስ የጀመሩ ኃይሎች ዐይናቸውን ሲጥሉበት ታይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት (EDU) በተቀናጀ ሁኔታ ትግል ሲጀምር ወልቃይትን የትኩረት ማዕከሉ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ አንድም አካባቢው ሰፋፊ የእርሻ ልማት ያለበት በመሆኑ ከመንግሥታዊ ኃይሎች የዕለት ተዕለት ቁጥጥር አንጻራዊ ነጻነት ለማግኘት፤ በሌላ በኩል ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ድጋፍ ለማግኘት ወሳኝ ስትራቴጅካዊ ቦታ በመሆኑ ወልቃይትን መርጧል፡፡ በዚህም ከወቅቱ የሱዳን (ኒሜሪ) መንግሥት የሎጀስቲክስ ድጋፍ ለማግኘት አግዟቸዋል፡፡ በወቅቱ ሱዳን ውስጥ የሬዲዮ ጣቢያና የካድሬ ትምህርት ቤት ከፍተው ማስተማር የቻሉት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት አመራሮች፣ ወልቃይት ዋና መንቀሳቀሻው እንደነበረ የዘመኑ ወታደራዊና አብዮታዊ ታሪክ ጥናቶች (John Young 1997, Christopher Clapham 1998) ያመለክታሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኀብረት በተለምዶ ‹ኢዲዩ› መዳከም በኋላ ደግሞ የግዛት ተስፋፊው አሸባሪው ትህነግ አካባቢውን ለመቆጣጠር ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ በተለይም ከሱዳን ድጋፍ ለማግኘት ተከዜን መሻገርና አካባቢውን መቆጣጠር የግድ አስፈላጊ ሁኖ ስላገኘው ትግሉን የሞት ሽረት ለማድረግ ተገድዷል፡፡
ከ1972 እስከ 1976 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ አሸባሪው ትህነግ ከደርግ ጋር ሲያካሂድ በነበረው ጦርነት ምክንያት አካባቢውን በቁጥጥር ስር ቢያደርገውም፣ የወልቃይት አማራ ሕዝብ ግን አልተቀበለውም ነበር፡፡ በወቅቱ ሕዝብ ከማስተዳደር ይልቅ ወደሱዳን መመላለሻ ኮሪደሩን ለወታደራዊ ዓላማ መጠቀም የመረጠው ትህነግ የደርግን ወታደራዊ ውድቀት ወደዕድል ለመቀየር አካባቢውን ተጠቅሞበታል፡፡
በመጨረሻም ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኃላ በ1984 ዓ.ም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ፣ ያለሕዝብ ይሁንታ ወልቃይትን የትግራይ አካል አደረገው፡፡ ይሄም ማለት አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ከመጽደቁና ሥራ ላይ ከመዋሉ ከሦስት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡
እዚህ ላይ ዛሬም እንደገና መነሳት ያለበትና በደንብ ሊታይ የሚገባው አንድ መሰረታዊ ነገር አለ፡፡ ይሄውም ‹ትህነግ በታሪክ የትግራይ አካል ሁኖ የማያውቀውን ‹ወልቃይት› ከ (በጌምድር) አማራ ሕዝብ በጉልበት ነጥቆ ለምን የትግራይ አካል አድርጎ መቀጠል ፈለገ?› የሚለው ነው፡፡  ጉዳዩ በዋናነት ከጂኦ-ፖለቲካው ጋር ይገናኛል፡፡
ስለሆነም ትህነግ የወልቃይትን ጉዳይ የሞት ሽረት ትግል ያደረገባቸው አራት ዋነኛ ምክንያቶች አሉ፡፡
• የመጀመሪያው ወልቃይትን የትግራይ አካል ማድረግ፤ ኢትዮጵያን በተለይም አማራን የማዳከም አንዱና ዋነኛው የትህነግ ስትራቴጅ ሁኖ መገኘቱ ቀዳሚው ምክንያት ነው፡፡
መላው የአማራ ሕዝብ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍ ሲል ደግሞ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚያውቀው፤ ትህነግ የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው፡፡ ትህነግ ኢትዮጵያን በመበተን ‹ታላቋ ትግራይ›ን ለመመስረት አቅዶ የተነሳና ዛሬም ድረስ በዚሁ መርህ እየተመራ ያለ ጸረ-ኢትዮጵያ ቡድን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ አማራን በቀዳሚ ጠላትነት ፈርጆ የተነሳና የታገለ፤ በተግባርም ዓላማውን ለመፈጸም ብዙ ርቀት የተጓዘ፣ ዛሬም ግማሽ አካሉ መቃብር በወረደበት በዚህ ዘመን ከቀደሙት ጥፋቶቹ ሳይታረም በአውዳሚ መስመሩ ላይ የቆመ ቡድን ነው፡፡
ስለሆነም ሁሌም ቢሆን የተዳከመች ኢትዮጵያንና አማራን ማየት የትህነጋዊያን ያደረና ዛሬም ያለ ህልም ነው፡፡ የትሕነግ ስሌት እጅግ በተዳከመችና በተከፋፈለች ኢትዮጵያ ‹የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ አጀንዳችንን እውን እናደርጋለን› የሚል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ማዳከም፤ አማራውን መበተን የግቡ ማሳለጫ መንገድ አድርጎ ቆጥሮታል፡፡
የወልቃይት ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ ለሚኖራት የበላይነት እጅግ ወሳኝ ስትራቴጅካዊ አካባቢ ሲሆን፤ ለአማራ ሕዝብ ደግሞ ሁለመናው ናት፡፡ ትህነግ ይህን በሚገባ ከተገነዘበ ውሎ አድሯል፡፡ ‹ወልቃይት ለአማራ ሕዝብ ሁለመናው ናት› ስንል እንዲሁ ሳይሆን፤ እጅግ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ ያላት ከመሆኑም በላይ ለአማራ ሕዝብ የማንነቱ መገለጫውና ኩራቱም በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
ስለሆነም ወልቃይትን ከአማራ መንጠቅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ ሕዝብ ጉዳቱ ከፍተኛ ሲሆን፤ ለትህነጋዊያን ደግሞ የደደቢት ቅዠታቸው የሆነውን ‹ታላቋ ትግራይ›ን እንዲመሠርቱ ትልቁን በር ይከፍትላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ትህነጋዊያን ወልቃይትን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገው የሚመለከቱት፡፡
• ሁለተኛው ትህነግ ወልቃይትና አካባቢውን ዳግም በመቆጣጠር ኢትዮጵያንና አማራን ለማዳከም ሌላ እድል ያገኝበታል፡፡
ትህነግ ወልቃይትን በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፤ ያልተገደበና በራሱ የሚመራ የውጭ ግንኙነት በመፍጠር፤ ሀገር የመሆን ህልሙን እውን ለማድረግ ይጠቀምበታል፡፡ ከሱዳን ወታደራዊ ኃይል ጋር በመሻረክ ከሁመራ እስከ ቤንሻንጉል ያለውን የኢትዮጵያ መሬት የመቀራመት ፍላጎት እንዳለው በሀገር ክህደት ተግባራቱ አሳይቶናል፡፡
በተጨማሪም ግብጽን የመሰሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን እየመራ ለማምጣት፣ በእነርሱ የመሳሪያ ድጋፍ ማዕከላዊ መንግሥቱንና የአማራ ክልልን በመውጋት ኢትዮጵያን ወደፍርስራሽነት በመቀየር ግብጽ በዓባይ ፖለቲካ የነበራትን የበላይነት በቋሚነት ለማስቀጠል የባንዳነት ተልዕኮውን ለመወጣት፣ በወኪሎቹ በኩል የካይሮን ደጅ ደጋግሞ ረግጧል፡፡
የትህነግ ጭፍራዎች ከግብጽ ሚዲያዎች እኩል ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ፕሮፖጋንዳዎችን ሲነዙ የሚውሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጋራ ውል ያላቸው በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ትህነጎች ቢሳካላቸው እስከ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ያለውንና በምናብ ካርታቸው ላይ ያሳዩንን መሬት አካተው የ‹‹ታላቋ ትራግይ››ን ምስረታ እውን ሲያደርጉ፤ የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ደግሞ ባልተጨበጠ የታሪክ ዳራ እና የሕግ ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ ‹‹አለን›› የሚለውን መሬት በቀላሉ ይረከባል፡፡ ምኞታቸው ይህ ነው፡፡ በዚህ የተቀናጀና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ባሳተፈ የወረራ ተግባር የተዳከመች ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የተበታተነች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር አልመው ይሰራሉ፤ እንደሕዝብ ጨርሶ የሚጠፋ አማራ እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡
በጠቅላላ ሂደቱም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከመኖር ወደአለመኖር በመቀየር የኢትዮጵያ ጠላቶችን ማስደሰት የትህነጎች ፍላጎት ስለመሆኑ ገሃድ ወጥቷል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ወልቃይትንና አካባቢውን ዳግም መልሶ መቆጣጠርን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገውታል፡፡
• ሌላኛው ደግሞ ኢትዮጵያ በአማራ በኩል ከኤርትራ ጋር እንዳትገናኝ የማድረግ ሴራ ነው፡፡
ትህነጎች ኢትዮጵያ በተለይም አማራ ከኤርትራ ጋር በድንበር እንዳይገናኝ በማድረግ የኢትዮ – ኤርትራን ግንኙነት ለመገደብ ከመፈለጋቸውም በላይ አማራ ከኤርትራ ወንድም ሕዝብ ጋር በማኅበረ-ኢኮኖሚውም ሆነ በጋራ የጸጥታ ጉዳዮች መልካም መስተጋብር እንዳይኖረው ይፈልጋሉ፡፡ እንደሚታወቀው ኤርትራዊያን ከትግራይ ልሂቃን ይልቅ ከአማራ ጋር ቀረቤታና ፍቅር አላቸው፡፡ ይሄን እውነታ የሚያውቀው ትህነግ አማራና ኤርትራዊያን ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርጎ ቆይቷል፡፡ ይሄ የቆየ የፖለቲካ መሰናክል አሁንም እንዲቀጥል ፍላጎት አለው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ወልቃይት በትህጎች እጅ በጉልበት መልሶ ሲገባ ብቻ ነው፡፡ በመኾኑም ወልቃይትን ላለማጣት ትህነጎች የሞትሽረት ትግል ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
• አራተኛው ወልቃይት ለትህነጋዊያን ትልቅ የሀብት ምንጭ፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአንድ በኩል የሀገርን ኢኮኖሚ በሚያቆረቁዝ ደረጃ የኮንትሮ ባንድ ንግዱን በመጠቀም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የወልቃይት አማራ ተወላጆችን በማፈናቀልና ለም መሬታቸውን በመንጠቅ በሰፋፊ የእርሻ ልማት በመሰማራት በርካታ የትህነግ ባለሥልጣናትና ባለሟሎቻቸው የለየላቸው ከበርቴዎች ሁነዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ተወላጁ ወልቃይቴ አማራ የበይ ተመልካች ሁኖ ሦስት አስርታትን አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዘመናት ሲከፋም ዘሩ እንዲጠፋ በጅምላ ተገድሏል፤ ታስሯል፣ ሀገር ለቆ እንዲሰደድ፣ ወደ መሀል ጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች በግፍና በገፍ እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡
ትህነጋዊያን የእነሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ያስችለናል ያሉትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጋዮቻቸውን በማስታጠቅ እንዲሁም የሰብል ምርት እጥረት ካለበት ድንጋያማ የትግራይ አካባቢዎች ያልታጠቁ ሲቪሊያንን በአንድ ላይ በማዋሃድ ከመሀል ትግራይ አምጥተው ወልቃይት ላይ አስፍረዋል፡፡ ይህ የሆነው ግን ተወላጁን አማራ ከኖረበት ቀየው በማፈናቀል ነው፡፡
በዚህ ሂደትም በርካታ የወልቃይት አማራዎች ዘራቸው ሲጠፋ፤ በአንጻሩ በርካታ የትህነግ ባለስልጣናትና የነሱ ጥቅም አስጠባቂዎች በልጽገዋል፡፡ ራሳቸውንም ወደገዥ መደብነት ለመቀየር ወልቃይት የሀብት ኮረቻ፣ የብልጽግና ማማ ሁናቸዋለች፡፡ በዚህም ምክንያት ትህነጋዊያንና ጥቅመኛ ማኅበራዊ መሰረቱ ወልቃይትን ማጣት የሞት ያክል ከብዷቸዋል፡፡
በቀጣይ የዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ጩኸት የወልቃይት ጉዳይ፣ የውጭ ኃይሎች ሴራና አሁናዊ ጂኦ-ፖለቲካውን  እንመለከታለን፡፡
Filed in: Amharic