>
5:14 pm - Friday April 30, 9238

እንዴት ከርመን ነበር? ት/ቤትና ሥነ ሥርዓት፣ለአሁኑ ትውልድ እምቦቀቅላ ተማሪዎች ትምህርት ቢሆን (ደረጀ መላኩ)

እንዴት ከርመን ነበር?

ት/ቤትና ሥነ ሥርዓት፣ለአሁኑ ትውልድ እምቦቀቅላ ተማሪዎች ትምህርት ቢሆን

ደረጀ መላኩ (የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

በውጭ ሀገር  በስደት የሚኖሩ ሰዎች ተጋነነ ወሬ ሲያወሩ ስደት ለወሬ ያመቻል እየተባለ ሲነገር በልጅነቴ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ እኔ ግን የልጅነት ትዝታዬን ላወጋችሁ ፈልጌ ከማስታወሻ ደብተሬ ያገኙሁትን ትዝታ ላወጋችሁ ፈለኩ፡፡ እስቲ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቴ ውስጥ ያለፍንበትን ከስክሱ ። 

የተረፋችሁን ግን በኪስ አኑሩት ።

አዲሱ አስተማሪ ከጃፖን የመጣ

ማስመሪያውን ትቶ በቦክስ የሚማታ ።

( ጃፖኖች ቀላል ሚዛን ቦክሰኛ ናቸውን ? )

ወላጆች ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን አስተባብረው ፣ መንግሥት ደግሞ ተቋም ነውና ሕግና ደንብ ማስከበር ባሻገር ማኀበራዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋትና ለማፋጠን ኑሮን ለማሻሻል ሰው ሰውነቱ እንዲለማና ዕውቀት እንዲሰፋ በየቀበሌው ት / ቤት ያቋቁማሉ መሞህርም ይመድባሉ ። 

ለመማር ዝግጁና ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ አዕምሮውን በትምህርት አበልፅጎ ቀሪውን ዘመኑን በሚፈልገው ሙያ ያገለግላል ። 

በሥራም ክህሎትን ያዳብራል ። 

ሰው ሁልጊዜ ተማሪም ፣አምራችም፣ አገልግሎት ሰጪም ተቀባይም ነው ።

እኔ መደበኛ ትምህርት የጀመርኩበት ት/ ቤት ውሰጥ መምህርም ዳይሬክተርም የነበሩ አሰፋ ማብረጃ የሚባሉ ነበሩ ። ወጣት ነበሩ ። 

ቁመታቸው ቢያጥርምና ሰውነታቸው መጠጥ ያለ ቢሆንም ራሳቸው ገለጥ ገለጥ ቢልም አሰፋ ሁሌ ዜንጠኛ ነበሩ ። 

ሸኪቦ ሸሚዝ ጥቁርና ነጭ ሱፍ ኮት ከሌዚማን ቺፖሊኒ ጫማ ጋር ለባሽ ነበሩና ሁሌም ንፁህና የደመቀች ጨረቃ ይመስሉ ነበሩ ።

አሴ እንግሊዝኛ አስተማሩኝ ። ስለ ጊዜያቶች በቋንቋ አጠቃቀም የጀመሩኝ እርሳቸው ናቸው ። 

Tenses ብለው በሠሌዳው ፃፉ ። እኛ አስሮች ብለን አልነው ። ሣቅ !

የሣይንሱን ” አቶም ” አትረሱትም አይደል ። ተማሪው ቸኩሎ የአክብሮት ቃል ነው ያለውን ።

መጀመሪያ በቅጡ ያልገባኝ ግን አሴ ሁልጊዜ የምታበራ ከዘራ ይይዛሉ ። አብራቸው አለች ። 

ሲያሽከረክሯት የሐረሩ አካዳሚ የሰልፍ ኩሳ መቺውን ዓይነት ችሎታ አላቸው ።

ድጋፍ ነች እንዳልል አሳቸው ገና ጥንቸል ነበሩ ። 

መራመድም መቆምም አልተሳናቸው ።

ብቻ ” ፋሽን ” ሆና ነበር ከዘራ መያዝ እንዳልል እርሳቸው ብቻ ናቸው የሚይዙት ቀሪዎቹ አልማዝ መሳይ መምህሮቼ አይሸከሟትም ።

አሴ ከባንድራ መስቀል በኋላ ክፍል ከመግባታችን አስቀድሞ በተማሪዎች ፖሊስ የቀረበ የሥነ ሥርዓት መጉደል ሪፖርት ካላቸው ተማሪው / ዎች ስማቸው ይጠራና ሰልፈኛው ፊት ይቆማሉ ። 

ቀልድ አያውቁም ።

ጎንበስ ተብሎ እጅ በጉልበት ሥር ሾልኮ ጆሮን ከያዘ በኋላ መቀመጫን ለአየር ስትሰጥ ብልት ፈልገው በጂኦሜትሪ መስመር ዲግሪ ጠብቀው ሃባህን አንዴ በከዘራው አገዳ ሲለጥጡህ ሙቀት ይለቅብሃል ። 

መቀመጫህ ተቆርጦ የወደቀ ይመስል እርሱን ይዘህ ትንሽ ዳንኪራ ትዘላለህ ውይ ጋሼ ….. እኔኮ አይደለሁም ልመናና መማፀን ትጀምራለህ ። 

ሙቀቱ እስከሚበርድ ይጠብቁሃል ። 

ከዛ ታጎነብሳለህ ትደገማለህ ። ትጨፍራለህ ። 

ተሜ እንደተሰለፈች ትስቃለች ። 

አይነጋ መስሏትና ነግ በኔ መሆኑን ረስታ ።

አሴ ጋ በከዘራ መቀመጫ መጠለዙ መጠኑ ሦስቴ ነው ። 

ይሄ የባለጌ ልክ ማስገቢያ ” ዶዝ ” ነው 

ጥሩ ሐኪም ናቸው ። 

መርፌያቸው ሦስት ብቻ ። 

ግን አልጫ እንደ ዘመኑ ሐኪም አያዙም ። 

መቀመጫ ሰንበር ቢጤም ከሰራም ያው ደረቅ ወንበር ላይ ሲቀመጡ ቀስ ብሎ ይሆናል ።

እኔም ቀምሻለሁ ። 

የአሴ ከዘራ ለካ ወጠጤ ማብረጃ ነች ። 

እቤት ውስጥ ግርግዳ ላይ እንዳለቺው ማንጠግቦሽ አለንጋ ። አሽትት ትባለህ የለ ጣዕሟ ትዝ እንዲልህ ?

አጥፊ የትም ሞልቷል ። 

ጥፋቴንም ስላወቅሁ ከዛ በኋላ ልጅቷን ቀናም ብዬ አላየኋት ። ግን እኮ በዓይኔ እወዳት ነበር ። 

አጠገቧ ስቆምና ሳወራት ደስም ትለኝ ነበር ። 

የሆነ ነገር ተቀላቀለብኝና አሻቅቤ ከሌሎች አብሬ የፈሪ ዓይነት ረብሻ ገባሁና ለካስ በሩቁ የተማሪ ፖሊስ መለያ የለበሰ አይቶኝ ኖሮ ዋጋዬን አሰጠኝ ።

የዘልዓለም ሥነ ሥርዓት ለብሰህ ቁጭ ። 

ጓደኛ ፣ የተማሪ ፖሊስ ፣ ዘበኛ ፣ መምህር …..ወዘተ አክብረህ መማር ።

ት/ ቤት ሥነ ሥርዓት መማሪያም ጭምር አይደል ።

መድገም የለም ።

ዛሬ ግን ተራጋጭ ሆንን ። 

ኧረ በአስተማሪም ቂም ቋጥረው ጠብቀው የሚያጎመጠምጡም ሞልተዋል አሉ ። 

ይዘገንናል !

ወላጅ አባትህን ስለመድፈርም ይቆጠራል ። 

እንዴትስ በዕድሜም በዕውቀትም ካንተ የሚሻለውን አሻቅበህ ጋጠ ወጥስ ትሆናለህ ? 

አሥርቱ ትዕዛዛት ኩነኔ ነው ብሎ ያስተማረህ አለን ?

Rude !

Vulgar !

Filed in: Amharic