>
5:21 pm - Tuesday July 19, 6281

በአዲስ አበባ ስለሚፈፀመው የጅምላ እስር - የባልደራስ አስቸኳይ ወቅታዊ መግለጫ   

የባልደራስ አስቸኳይ ወቅታዊ መግለጫ 

 
ዋና ጉዳዮች:-
 
1.በአዲስ አበባ ስለሚፈፀመው የጅምላ እስር
 
2. ህጋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት ልንገደድ የምንችል ስለመሆኑ 
 
የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ክብር በዓለም ላይ ከፍ ያደረገና የናኘ ዘላለማዊ አንፀባራቂ የጥቁር ህዝቦች ድል ነው። በመሆኑም ይህን ታሪካዊ በዓል በየዓመቱ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን በመላው ዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ዘንድም ይዘከራል። የዘንድሮው 126ኛ ክብረ-በዓል በመደበኛነት ከሚከበርበት ከአፄ ምኒልክ አደባባይ ወደ አድዋ ድልድይ በገዥው ፓርቲ ውሳኔ ተዘዋውሯል፡፡ ይህ ድርጊት ታሪክን ለማዛባትና የድሉ መሃንዲስ የነበሩትን አፄ ምኒልክን ከአድዋ ታሪክ ለመነጠል የተጎነጎነ፣ ከዘመናችን የተረኛ ቡድናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና ስሜት የመነጨ ነው፡፡
ሆኖም ታሪኩን አሳልፎ የማይሰጠው የአዲስ አበባ ሕዝብ፣ የገዥው ፓርቲ ተረኛና ጽንፈኛ የዘውግ እንቅስቃሴ ወደ ጎን በመተው፣ ህፃን፣ ወጣት፣ አዋቂ፣ አረጋዊ ሳይል በነቂስ ወጥቶ፣ መሃል አራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የአጼ ምኒልክ አደባባይ በዓሉን አክብሮታል። በዕለቱ የባልደራስ አመራሮች በዓሉን ለማክበር ወደ አጼ ምኒልክ አደባባይ ሲደርሱ የአዲስ አበባ ህዝብ ያደረገላቸው ደማቅ አቀባበል፣ በአገራችን ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠ ነው፡፡
በተለይ የአዲስ አበባ ወጣት ፍጹም ሰላማዊ በሆነና በሰለጠነ መንገድ ታሪኩን በማድመቅ አወድሷል፤ ባህሉን አንፀባርቋል፤ ታሪካዊ እሴቶቹን  በኩራት ዘክሯል። በዚህ ዘመን እንደዚህ ታሪኩን የሚወድ ወጣት በዓለም ዙሪያ ቢፈለግ ብዙም አይገኝም። ኢትዮጵያ የምትኮራባቸው ወጣቶች ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶችም ሆኑ ቀሪው የአዲስ አበባ ማኅበረሰብ በዘንድሮው የአድዋ ክብረ-በዓል ላይ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ቅሬታ አሰምተዋል። ተቃውሞው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተገለፀ መሆኑን መላው ዓለም የታዘበው እውነታ ነው፡፡ ከቅሬታዎቹ መካከል የኢትዮጵያ አንድነት እና የሰንደቅ ዓላማው ጥያቄዎች፣ የኑሮ ውድነት፣ የአዲስ አበባ ሕዝብን የማይወክለው የምርጫ 2013 ውጤትና ሌሎች ይጠቀሳሉ፡፡
መንግሥት ለጥያቄዎቹ አግባብነት ያለው መልስ በመስጠት ፈንታ፣ ወጣቶችን እያዋከበና እያሰረ ይገኛል። እስካሁንም ድረስ 34 የባልደራስ አባላት እና በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶች ታስረዋል፡፡ እስሩ በዛሬው ዕለትም እየተከናወነ ይገኛል፡፡
 ይቀጥላልም ተብሎ ይታሰባል፡፡
ይህ ጉልበትን እንጂ ህግን መሠረት ያላደረገ፣ አንድን የፖለቲካ ፓርቲ እና የአዲስ አበባን ልጆች የማሳደድ መንግሥታዊ እርምጃ በአገራችን ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ብሄራዊ ንግግርም ሆነ ለከተማዋ መረጋጋት ፈጽሞ የሚበጅ ባለመሆኑ፣ የሚከተሉት የማስተካከያ እርምጃዎች በመንግሥት በኩል በአፋጣኝ እንዲወሰዱ ባልደራስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡
 እነዚህም፡- 
 
1ኛ. ይፋዊው የአድዋ ድል ማክበሪያ ቦታ እንደ ቀድሞው የአጼ ምኒልክ የመታሰቢያ ሀውልት ዙሪያ እንዲሆን፣ 
2ኛ. በ126ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ ክብረ-በዓል ላይ፣ እንዲሁም፣ በካራማራ ድላችን በዓል ላይ በመገኘት ለአገራቸው፣ ለታሪካቸውና ሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸውን ወደር የለሽ ፍቅር በመግለፃቸው የታሰሩ 34 የባልደራስ ፓርቲ አባሎች፤ እንዲሁም ከየቤታቸው ተለቅመው የታሰሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ 
 
3ኛ. መንግሥት የፍትህ ሥርዓቱን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ መጠቀሙን እንዲያቆም፣  
4ኛ. የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ ህዝብ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች እንዲመለሱ፣   
 
5ኛ. በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው ህዝብን ሆን ብሎ የመተንኮስና የማበሳጨት ሥራ እንዲቆም፣ 
ለእነዚህ ጥያቄዎች መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ በአፋጣኝ የማይሰጥ ከሆነ፣ ባልደራስ ህዝብን አስተባብሮ ህጋዊ ሠላማዊ ሠልፍ ለመጥራት የሚገደድ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
ባልደራስ ለአውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ 
የካቲት 29/06/2014 ዓ.ም
Filed in: Amharic