>

ዛሬ 81 ዓመት የተሸነፈ መንፈስ....!!! (አዲሱ ኢትዮፕ)

ዛሬ 81 ዓመት የተሸነፈ መንፈስ….!!!

አዲሱ ኢትዮፕ

የአፄዎቹ ሥርዓት እና መሪዎች ከጠላት ጋር ተዋድ ያቆዩትን አገርና የአንድነት ታሪክ ለመሸርሸር የሚሞክር የመከነ ትውልድ።
፦ጣሊያን ከ81 ዓመት በፊት ተሸንፎ ሲወጣ ጥሎት የወጣው በሃይማኖትና በብሔር መከፋፈል አጀንዳ ዛሬ ያንን የተሸነፈ አጀንዳ የግብር ልጆቹ ይዘውት ይታያል።
፦ጥቁር ጣሊያኖች ከጣሊያን በከፋ አባቶቻቸው አንድ ያደረጓትን አገር ለማፍረስ እንቅልፍ አተዋል።
፦ከ81ዓመት በፊት የተሸነፈን መንፈስ በጀግኖች አባት እናቶቻችን  የቆመን አንድነት ለመናድ ዛሬ ተላላኪዎቹ እየተረባረቡ ይገኛል።
፦በአፄዎቹ ወደ ኢትዮጲያ የገባ ሃይማኖት መሆኑን የረሱ ድኩማን የአፄዎቹን ሥርዓት ሲረግሙ ሲታይ የትውልዱን ዕውቀትና ማስተዋል እንደጎደለው ትረዳለህ
ጣሊያን በዓደዋ ላይ የተከናነበውን ውርደት ቁጭት ፈጥሮበት ለአርባ ዓመት ሲዘጋጅ ቆይቶ ዳግም በ1928ዓም ወረራ ስትደርግ ጀግኖች አባቶቻችን ለአምስት ዓመት በዱር በገደሉ ተጋድለው በ1933 ዓም ድል አድርገው በማሸነፋቸው ወራሪው ጠላት ውርደቱን ተከናንቦ ወደመጣበት ሄዷል።
ኢትዮጲያን እናት አባቶቻችን ኢስላም ክርስቲያን ሳይሉ ለአንዲት አገራቸው ከጫፍ ጫፍ በአርበኝነት ሲዋጉ የከፈሉት መስዋዕት ወደር የሌለው ነበር።
ኦሮሞ፣አማራ፣አፋር፣ሱማሌ፣ሃዲያ፣ጉራጌ፣ወለይታ፣ጋሞ፣ሃረር፣ጋምቤላ፣ቤኒሻንጉል፣ትግሬ፣ዶርዜ መላው ኢትዮጲያዊ እንደ ንብ ተምሞ ያለሃይማኖትና ብሔር ልዩነት ያደረገው ድንቅ ተጋድሎ የታሪክና የአንድነት ጠላት የሆነውን ፋሺስት በመርታት በዛሬዋ ዕለት ቀዳማዊ አፄ ሃይለሥላሴ ከጀግኖች አርበኞች ጋር የድል ሰንደቅ አውለብልበዋል።
ጣሊያን በወረራው ወቅት ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ በማጋጨት በሺህ የሚቆጠሩ አብያተክርስቲያናትን በማቃጠልና ክርስቲያኖችን በመግደል ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደቆመ ለማሳየት በርካታ መስጊዶች እንደሰሩ አድርጓል።
አስቡት ፋሺስት ጣሊያን አባት ሃይማኖቱ ካቶሊክ ሆኖ መስጊድ መስራቱና ለሙስሊሙ የወገነ የመሰለው በቀልና ኢትዮጲያን እስከ መጨረሻው ለመበታተን ካለው የተጠና ዕቅድና ስትራቴጂ መሆኑ አይካድም።የሚገርመው በርካታ የሙስሊም አርበኞች በጀግንነት ተንኮሉን በመረዳት ተዋግተውታል።
በተመሳሳይ በብሔረሰቦች መሃል የዘራው እንክርዳድ እንዲሁ የከፋ ነበር አማራ በዳይ ሌላው ብሔር በተለይ ኦሮሞና መሰል ብሔረሰቦች በአማራ ጨቋኝ መደብ ግፍ እንደተፈፀመባቸውና እንደተሰቃዩ በማሳየት የዘራው መርዝ ኢትዮጲያዊያን በዓደዋ የፈፀሙበትን ውርደትና ንዴት በራሳቸው ዜጎች አገሪቱን ለማፍረስና ቁጭቱን ለመወጣት በብርቱ ሠርቷል።
በዓደዋ ድል ጣሊያን ምን ያህል የከፋ ንዴትና ብስጭት እንዳደረበት ከፈፀመው ጥቃት መረዳት ይቻላል።ይህንንም ታሪክ ይነግረናል።
ምዕራባውያን ያቀዱት የቅኝ ግዛት ቅዠት እንዲሆን ኢትዮጲያዊያን ያደረጉት ተጋድሎ የእግር እሳት ስለሆነባቸው የበቀል ቀስታቸው በሂደት በውጊያ ያልቻሏትን አገር በራሷ ልጆች ላይ መርዝ በመዝራትና እንድትዳከምን እንድትፈርስ አንዱን በአንዱ በማነሳሳት እና በማለያየት የፈፀሙት የማድረግ ዕቅድ ፍሬ አፍርቶ ዛሬ የተሳካላቸው ይመስላል።
ያ በአባቶቻችን የተሸነፈው ነጩ ሰይጣን ጣሊያንና ቅኝ ገዢ ሃይሎች የክፋት ጠፍራቸውን በራሳችን ልጆች ላይ ተክለው ለአንድነቷና ለህልውናዋ ዋጋ የከፈሉትንና መስዋዕትነት የፈፀሙትን በመስደብ በማዋረድ ጥንታዊት አትዮጲያ በአንድ ሃይማኖትና በአንድ ብሔር ፍቃድ ብቻ እንደቆመች ሌላው ብሔርና ሃይማኖት የተጨቆነ በማድረግ ጣሊያን ያልቻለውን አገር የማፍረስ ዕኩይ ተግባር ተላላኪዎቹ ሊፈፅሙት እየሞከሩ ይገኛል።
ክብር ለአፄዎቹ ክብር ለጀግኖቻችን ሞት ለኢትዮጲያ ጠላቶች።
Filed in: Amharic