>

ወሎ እና የክልልነት ጥያቄ በእነማን ? ለምንስ አላማ...!!! (ምስጋናው ታደሰ)

ወሎ እና የክልልነት ጥያቄ በእነማን ? ለምንስ አላማ…!!!

ምስጋናው ታደሰ

*… በወሎ ሥም የሚቀነቀነው ክልላዊ ጩኸት!!

ሰሞኑን በዚሁ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ወሎ እና ክልልነትን አስመልከቶ የተለየያዩ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ ተመልክቻለሁ፡፡ የተመለከትኳቸዉ ሀሳቦች ከተለያዩ ወገኖች እና አቅጣጫዎች የተሰነዘሩ ናቸዉ፡፡ ማለትም ነገሩ ከገባቸዉም ካልገባቸዉም፣ ነገሩን በስሌት ከሚሰሩትም በነገሩ በስሜት ከሚነዱትም፣ ጉዳዩን በበጎ  መልኩ ከሚመለከቱትም እንዲሁም ጉዳዩን ለራሳቸዉ እኩይ ዓላማ መጠቀሚያ ለማድረግ ከሚፈልጉት ወገኖች የሚሰነዘሩ እንደሆኑ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ማለትም ከወሎ ክልልነት ጋር በተያያዘ የሚንሸራሸሩት ሀሳቦች የተለያዩ እጆች እና ፍላጎቶች ያሉበት ስለሆነ ነገሩ በአትኩሮት ሊጤን ይገባዋል፡፡

በዚች አጭር ጽሑፍ ሁለት አንኳር ነገሮችን ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ የመጀመሪያዉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸዉ የማህበረሰብ ክፍሎች ቢወያዩባቸዉና ቢያንሸራሽሯቸዉ ያልኳቸዉን ሀሳቦች በጥያቄ መልክ አስቀምጣለሁ፡፡ እናንተ ጓደኞቼም እንድትነጋገሩባቸዉ እጋብዛለሁ፡፡ በመቀጠልም የራሴን የግል ሀሳብ በአጭሩ አስቀምጣለሁ፡፡

ወደ ጥያቄዎቹ ልለፍ

1. በመጀመሪያ የወሎ የክልልነት ጥያቄ የማን ነዉ የመላዉ? ወሎየዎች ጥያቄ ነዉ ወይስ የጥቂት ቡድኖች እና ግለሰቦች ነዉ?

2. ይህን ጉዳይ በባለቤትነት የያዙት እነማን ናቸዉ ዓላማቸዉስ ምንድን ነዉ?

3. ጉዳዩን ከኋላ ሆነዉ የሚገፉት (የሚደግፉትስ) እነማን ናቸዉ?

4. የወሎ ክልል መሆን ከአማራነት እና ከአማራ ክልል ጋር የሚኖረዉ አንደምታ ምንድን ነዉ? ትርፉ እና ኪሳራዉስ ምን ሊሆን ይችላል?

የግል ምልከታ እና አስተያየት

ሀገሪቱ አሁን የምትተዳደርበት በዘር እና በቋንቋ ላይ የተመሰረተዉ ህወሓት የተከለዉ የፌዴራል አወቃቀር ፈርሶ በሌላ የአስተዳር መዋቅር ቢተካ ከሚመኙ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ ስክነት እና ዘላቂ ሰላም ሲባል መተግበር ያለበት ነዉ፡፡ እነዚህ ክልሎች በተለይም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ፈርሰዉ በሌላ (መልከዓምድራዊም ሆነ ሌላ) የሚተኩ ከሆነ ወሎ የራሱ ማንነት ያለዉ ህብረ ብሔራዊ ክፍለ ሀገር እንደመሆኑ መጠን ራሱን ችሎ ክልል ወይንም ክፍለ ሀገር መሆኑ አይቀሬ ነዉ፡፡

ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ወሎን ከአማራ ክልል መገንጠል አማራ ክልልን ቆራርሶ በማሳነስ ክልሉን ማዳከም እና ለባሰ መለያየት ማጋለጥ ነዉ፡፡ እንዲሁም አንድ የአማራ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገዉንም ሂደት ማኮላሸት ነዉ፡፡ እርግጥ ነዉ ወሎ ላይ በርካታ ችግሮች እና ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለችግሮቹ ዘርፈ ብዙ መፍትሄዎችን ማፈላግ እንጂ አማራ እና አማራነት መከራዉን እያየ ባለበት በዚህ ወቅት 90% አማራ የሆነዉን ወሎ ለመገንጠል የሚደረገዉ አካሄድ ወቅቱን ያልጠበቀ፤ ሀገሪቱም ሆነ ክልሉ ያሉበትን ሁኔታ ያላገናዘበ ነዉ፡፡ ነዉ፡፡

ጉዳዩን በባለቤትነት ይዘዉ የሚያራግቡት ግለሰቦች ቁጥራቸዉ እዚህ ግባ የማይባል የአንድ ማህበር አባላት እንደሆኑ በግልጽ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖች ባለፈዉ ሳምንት በሳፋሪ ሆቴል እነሱ የሚፈልጓቸዉን ሰዎች ብቻ ጠርተዉ የዉይይት መድረክ እንዳዘጋጁና  ለዚሁ ዓላማ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ የሚያሰባስቡ ሰዎችም እንደተመደቡ ተሰምቷል፡፡ ጉዳዩ የወሎ እና የወሎየዎች ከሆነ የሚመለከታቸዉ እና ማህበረሰቡን የሚወክሉ የየማህበረሰቡ ክፍሎች ተገኝተዉ ሀሳብ አስተያየታቸዉን እንዲሰጡ በተደረገ ነበር፡፡

በወሎ ሥም የሚቀነቀነው ክልላዊ ጩኸት!!

* ደቡብ ወሎ ላይ አዲስ ዞን በመመስረት ነባሩን ዞን በኦነግ ፖለቲካ የመሰልቀጥ ምኞት ያለው፤

* በተመሳሳይ የፌስ ቡክ ሥም የተደራጀ የኦነግና የብልጽግና የሳይበር ጦር የሚያራግበው፤

* ሕዝባዊ መሠረት የሌለው፤

* አማራን ወደ ማይኖሪቲ አውርዶ ኦሮ፤ሚያን ብቸኛ ማጆሪቲ የማድረግ ሕልም ያለው ፤

* የኃይማኖት ግጭት የመፍጠር ተልዕኮ የተሰጠው፤

* የቤተ አማራዎች እትብት መቀበሪያ ምድር ወሎ መሆኗ የተዘነጋው፤

* ትልቁን የአማራ ዞን አንዲት ወረዳ ከማታክል ልዩ ዞን ስር የማዋል እቅድ ያለው…

አሁንም መፍትሄዉ ጉዳዩን ለሚመለከተዉ ለአካባቢዉ ማህበረሰብ መተዉ ነዉ፡፡ ራሱ የሚበጀዉን ያደርጋል፡፡

Filed in: Amharic