>
5:14 pm - Wednesday April 30, 7400

የጥበብን ምስጢር ሳይታክት የፈተሸ ደራሲ- ሀብቴ ባሴ ( ጌታ በለጠ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎጃም)

የጥበብን ምስጢር ሳይታክት የፈተሸ ደራሲ- ሀብቴ ባሴ

( ጌታ በለጠ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎጃም)


ዛሬ ጉዟችን ወደ ጎጃም፣ ቢቸና፣ጓቸሟም ቀበሌ ነው። የጉዟችን ዓላማ በሸጋ ብዕሩ የሥነ ጽሑፍን ጥበብ በብርቱ የመረመረ ታላቅ የኪነ ጥበብ ሰው ለማውሳት ነው። ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህር እና የሰርቬይንግ ባለሙያ ባሴ ሀብቴ ውቤ የብዕራችንን ትኩረት ስቧል። ባሴ ሀብቴ ውቤ እጅግ አጥብቆ የሚወዳት እናት አሉት።ሥማቸውም ወይዘሮ (በኋላ እማሆይ) ዛብሽ ወርቅነህ ይባላል።

ባሴ ሀብቴ (ባሳዝነው) ትውልዱ ጎጃም፣እነማይ ወረዳ፣ ጓቸሟም ከምትባለው ቀበሌ ነው፡፡ ጓቸሟም ከቢቸና ከተማ ከ 10-12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ቀበሌ ናት፡፡ የባሴን የትውልድ ዘመን አስመልክቶ ሁለት ዘመናት ይጠቀሳሉ፡፡ አብዱራህማን ናስር የተባለ የባሴ ሀብቴ ጓደኛ የባሴን የትውልድ ዘመን 1946 ዓ/ም እንደሆነ ዳንኤል ስቴል The promise ስትል በጻፈችው እና ባሴ ሀብቴ “ቃል” ሲል በተረጎመው መጽሐፍ ሁለተኛ ዕትም ላይ አስፍሯል፡፡ በሌላ በኩል “ጭጋግና ጠል” በሚል ርዕስ ደራሲያን በጋራ ባሳተሙት መጽሐፍ ባሴ ሀብቴ በ1942 ዓ/ም የተወለደ መሆኑ ሰፍሯል፡፡ የሆነ ሆነና እንኳን ተወለደ። በመወለዱ አትርፈናል። 

ባሴ ሀብቴ ገና በጠዋቱ እዚያው ጎጃም ከእነ የንታ ዘንድ የቤተክህነት ትምህርት ተማረ፡፡ ዘግይቶም በወቅቱ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ቴዎፍሎስ ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ወስደው ዘመናዊ ትምህርት ቤት አስመዘገቡት፡፡በዘመናዊ ትምህርት ገፍቶበት በሰርቬይንግ( ቀያሽነት) ሙያ ተመርቋል፡፡በቀያሽነት ሙያው በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውሮ ሰርቷል፡፡ የቀያሽነት ሥራው በየክፍለ ሀገሩ የሚያዞረው በመሆኑ እንደልቡ መጽሐፍትን የማግኘት ዕድል የነፈገው በመሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ በመምህርነት ሙያ ተወዳድሮ ሥራውን ጀመረ፡፡ በ1960ዎቹ አዲስ አበባ፣ ጎፋ ሰፈር “ነጻነት ጮራ ትምህርት ቤት” አስተማሪ በነበረበት ወቅት ከደራሲ አውግቸው ተረፈ ጋር አንድ ክፍል ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር፡፡

የአንባቢነት እና የደራሲነት ሥራው የጀመረ ከዚህ በኋላ ነበር፡፡ባሴ ሀብቴ አንባቢ፣ ትሁት እና ብርቱ ደራሲ እንደሆነ የዘመን ጓደኞቹ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ደራሲ ደምሴ ጽጌ ባሴ ሀብቴ አንብቦ የማይታክተው፣ ከመጻፍ ይልቅ ማንበብ የሚወድ፣ የዓለም ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አድኖ (ድ ጠብቆ ይነበብ) ያነበበ መሆኑን “ቃል” በተሰኘው የሀብቴ ባሴ የትርጉም ሥራ ላይ ምስክርነቱን አስቀምጧል፡፡ስንዱ አበበ በበኩሏ የጥበብን ምስጢር ሳይታክት የፈተሸ ስትል ታሞካሸዋለች፡፡ ደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር “ ባሴ ሲጽፍም ሲኖርም ፈረንሳዮች እርግማን ያለበት ባለ ቅኔ እንደሚሉት ነው።…ባሴ አንድ ሰው ሆኖ ውስጡ ሦስት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉልላት የሆኑ የሥነ ቃል ሊቃውንት ተባብረው ይፈጥራሉ። እነሱም፦ ደራሲው፣ ባለቅኔውና ተርጓሚው የምንላቸው ናቸው።” ሲል ወንድም ጌታ በተሰኘው መጽሐፍ መግቢያ ላይ ይገልጸዋል። 

ባሴ ሀብቴ በ1980 ዓ/ም ከደራሲ እና ጋዜጠኛ ስንዱ አበበ ጋር ተዋወቀ፡፡ ትውውቃቸው በወቅቱ እነ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ያሉበት የንባብ ከበብ ውስጥ ነበር፡፡ ደራሲ ስንዱ አበበ እንዳየችው በፍቅሩ ክንፍ አለችለት፡፡ እሱም አርፍዶም ቢሆን ወደዳት፡፡ ፍቅራቸው ለሦስት ዓመታት ዘለቀ፡፡ ስንዱ አበበ “ባሴ የፍቅር ጠቢብ ነው” ትላለች፡፡ “የኔ ማስታወሻ” ስትል ባሳተመችው መጽሐፍ ባሴ ሀብቴ “ሰላም ለኪ” በሚል ርዕስ ጽፎላት የነበረው የፍቅር ደብዳቤ ሰውዬው እውነትም የፍቅር ጥበበኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ 

ከባሴ ሀብቴ ሥራዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

ጠብታ ማር ( ትርጉም፣ ከደራሲ ደምሴ ጽጌ ጋር)

  1. ቃል (ትርጉም)
  2. ጭጋግና ጠል (ትርጉም፣ ከሌሎች ደራሲያን ጋር)
  3. ወንድምጌታ (ልብወለድ)
  4. ሮሜዮና ዡልየት (ትያትር፣ ትርጉም)
  5. ሲያኖም ደቨርዠራክ (ትያትር፣ ትርጉም)
  6. ደራጎን (አጭር ልብ ወለድ)
  7. ድንገት (አጭር ልብ ወለድ)
  8. ሀበሻ (አጭር ልብ ወለድ)
  9. ውሽንፍር ( ትርጉም)

በመጨረሻም ለሐገራችን የሥነ ጽሑፍ ዕድገት አያሌ አበርክቶዎችን ያደረገው ምትሃተኛ ደራሲ እና ተርጓሚ ባሴ ሀብቴ ግንቦት 7 ቀን 1988 ዓ/ም 50 ዓመት እንኳን በምድር ሳይቆይ በፈጣሪው ተጠራ፡፡

Filed in: Amharic