ሕዝብን ሥልጣን የሚቀሙ – ችግርና ድህነት፣ አድሎና በደል፣ ወከባና ሁከት አምጭዎች ይራቁልን!
ሠርጸ ሚካኤል–
ባሁኑ ሠዓት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በሁለት ጥምዝ እና ችሎታ/ክህሎት–አልባ ፖለቲካ መሃል እየተጨመቁ ይገኛሉ (squeezed between two twisted and folly politics)። ጥምዙ ማስተዳደር ያቃተው በሥልጣን ላይ ያለው ኦሕዴድ–ኦዴፓ–ብልጽግና መንግሥት ሲሆን ችሎታ/ክህሎት–አልባው ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለመጣል በዘፈቀድ የሚራወጠው የባዕድ አገሩ ስብስብ/ቡድን ነው። ስብስቡ ችሎታ/ክህሎት ይታደል ዘንድ – በሳል የሆኑ ለኢትዮጵያ በሙሉ ልባቸው የሚቆረቆሩትን ብቻ እንጂ – ችኩሎችን፣ ሥልጣን አፍቃሪዎችን፣ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” ባዮችን፣ አስመሳዮችን፣ የወንጀል ተጠያቂዎችን፣ ዘረኞችን፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የወገኑን፣ የስደት ኑሮ የመረራቸውን፣ የዲስኩር ሱሰኞችን፣ ወዘተ፣ ግለሰቦችን ከወዲሁ ማራቅ እንደሚገባው አስተያየት መስጠት ነው የዚህ ጽሁፍ ዓላማ።
“የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ሠሪዎች“ ተፈጥሯዊ ሁኔታን መቋቋም የሚችል ቤት መስራት እንደማይችሉ ሁሉ ችሎታ/ክህሎት–አልባ ችኩል ፖለቲከኞችም ሻል ያለ ነገን ሊያመጣ የሚችል ስልትና ስትራቴጂ ሊነድፉ አይችሉም። ሁለንተናዊ ንቃት የሌለው ስብስብ የመንግሥት ከርባቾች “የባንከረባብት” ብይ ተጫዋቾች ከመሆን በዘለለ ለውጥ አያመጣም። ትግል አይናቅም፣ ቢሆንም ግን እውነትና እውነታ (truth and reality) ሊታሰብባቸውና ሊከበሩ የሚገባቸው መርሆች ናቸው። የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ መርምሮ እውነትና እውነታን መሬት ላይ ለማውረድ ስሜት (emotion) ሳይሆን ጥበብ (wisdom) ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ የአስተዳደር፣ የመሬት፣ የዲሞክራሲ፣ የሕዝባዊ መንግሥትና የብሄር/ብሄረሰብ፣ የባህር በር፣ ጥያቄዎች፣ ሁነኛ መልስ ያላገኙባት ይባስ ብሎም የትምህርት ማስረጃ የገዙ፣ የሙሰኞች፣ የዘረኞችና የእበላባዮች መቀለጃ አገር ከሆነች ሠንብታለች። ይህ ቀልድና ድራማ ሊወገድ ይገባል።
መንደርደርያ
“ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም” እንዲሉ በአስገንጣይና ተገንጣይ ቡድኖች (ግብጽ፣ ጀብሃ፣ ሻዕቢያ) ሲወላገድ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሰለሞናዊው ሥርወ–መንግሥት እንዲገረሰስ፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ እንዲደፈርና አንድነቷ እንዲናጋና ጽንፍ ድረስ ሄዷል። የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተከታታይ እርግማን ይዞ መጣ። ኢሕአፓ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለኤርትራ መገንጠል ጮኋል። ትንታጎቹ ወጣቶች ሶማልያ ኢትዮጵያን እንድትወርና ይሳያስ አፈወርቂ እሥልጣን ማማ እንዲወጡ ተሰውተዋል። ሕወሃት አሰብ ወደብን ሙሉ በሙሉ ለኤርትራ በማስረከብ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ትልቅ ደባ ሠርታለች። የተማሪው እንቅስቃሴ አማራውን በጨቋኝነት በማስፈረጁ ሳብያ ነገደ አምሃራ በወያኔና በብልጽግና መጠነ ሠፊ የዘር እልቂት ተካሂዶበታል። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ በዘረኞች የተመራችው ፖለቲካ – ያልተማሩ ባለሥልጣናትን – ንጉሡ ባዋቀሯቸው የአስተዳደር ቢሮዎች አስቀምታ ኢትዮጵያን በድንቁርና አለንጋ ለበለበች። ከጥበብ (wisdom) ወደ ከንቱነት (vanity) ሽግግር ማለት ይህ ነው።
በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ሶስት መንግሥታት ተገርስሰዋል፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት፣ የወታደራዊው ደርግ/ኢሠፓ መንግሥት፣ የህወሃት/ኢሕአዴግ መንግሥት። ኋለኛው ከፊተኛው ለመሻሉ ብዙም አይወራም። ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ የሆነበት፣ የህወሃት/ኢሕአዴጉ የክፋት ውጤት የሆነው ኦሆዴድ–ኦዴፓ ብልጽግና መንግሥት ሊወድቅ እጫፍ ደርሷል። መጪው ከዚህኛው ያልተሻለ ከሆነ ኢትዮጵያ ዳግም አንገቷን ቀና ከምታደርግበት ኃይሏ ይዝላል። የወቅቱ ሕዝባዊ ትግል እጅግ ወሳኝ፣ የሞት የሽረት ትግል ነውና የቀረችን ጥቂት ጊዜዓት እንዳትባክን መጠንቀቅ አለብን። አለበለዝያ አውላላ ሜዳ ፣ ሓሩር ምድረ በዳ፣ ጥልቅ ውቅያኖስ ላይ እንደዘበት ወድቆ እንደቀረው ባይተዋር ሃገርም ባክና ትቀራለች።
ችግር
ኦሆዴድ–ኦዴፓ–ብልጽግና – ሚኒልክ እና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ለችግር ጊዜ እንዲሆን ያስቀመጡትን የመጨረሻውን የአስተዳደር እርሾ አሟጦ ተጠቅሟል። የጠ/ሚኒስትሩ የሥራ መግለጫ (job description) ስሙኝ ላሞኛችሁ ስብሰባ፣ ካርታ ብወዛ፣ ቤት ማፍረስ፣ ሸርና ሴራ ብቻ ሆኗል። መላ ኢትዮጵያ የጦር አውድማ ሆናለች። በአማራ ጠቅላይ ግዛቶች ትምህርት ቆሟል፣ ሃኪም ቤቶች ተዘግተዋል፣ እርሻ ባክኗል። በወለጋ ኦነግ–ሸኔ መንግሥትን እያሽመደመደ ነው። በቤንሻንጉልና ጉሙዝ ሁከት እንጂ ፀጥታ የለም። በመላ ኢትዮጵያ በባህልዊ መልክ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ሕዝብ እንጂ ህግ አስከባሪ ተቋም ፈርሷል፣ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሷል። ካዝናው በመሟጠጡ ምክኛት ግብር በንጥቂያ ሆኗል። አያድርገውና የውጭ ኃይል ኢትዮጵያን ቢወር የመዋጋት አቅም ያለው መከላከያም ሆነ አመራር ሠጪ ብቃት ያላቸው አዋጊ መኮንኖች የሉም።
ማስተዋልና ብስለት የሚያስፈልገው አሁን ነው። ዲሞክራሲ እንግዳ በሆነበትና የፖለቲካ ባህል ባልዳበረበት አገር መንግሥት ለመለወጥ መሞከር ቀላል አይደለምና ለውጥ ለማድረግ ሲሞከር ብዙ ነገሮች አብሮ ማጤን ያስፈልጋል። “መንግሥት ይለወጥ” የሚለው ስብስብ አገሪቱ የተወተፈችበትን ውስብስብ ችግሮች ቀርፎ ሕዝቡ በልቶ እንዲያድር፣ በሰላም ወቶ እንዲገባ የሚያስችለውን እውቀት ለብሷል? ስብስቡ የጎሳ ልዩነቱን ያበርደዋል? ስብስቡ በህግ ማጉደል፣ በዘር ፍጅት፣ በዘረፋና የአገርን ሃብት በማሸሽ ሊጠየቁ የሚገባቸው ወንጀለኞችን ለህግ ያቀርባል? ስብስቡ ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበት ዕዳ ለመክፈል ምን ዓይነት አዋጭ የምጣኔ ኃብት አሰራር ይተገብራል? አራት ኪሎ እንዲያስቀምጠው ብቻ የምዕራቡን አገር ባለሥልጣናት ማለዳ እጅ የሚነሳው ስብስብ የኢትዮጵያን ጥቅምና የሕዝቡ ግብረገባዊ ባህል አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ምን ዓይነት ብልሃት እየተጠቀመ ነው? ስብስቡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መቦረቅያ ሜዳ እንዳያገኙ ጠንካራ አጥር ያበጃል? ስብስቡ የታራዙ፣ የተራቡ፣ የሚያለቅሱ ወገኖች ፈጣን ፍትህ እንዲያገኙ የሚያስችል መላ ዘይዷል? እነኚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው። ሊወድቅ ባጋደለ መንግሥት ጥራ ስር ተከልሎ፣ አድፍጦ ተሽቀዳድሞ ወደ ሥልጣን ማማ መሮጥ ሊቆም ይገባል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች “ባልበላውም ጭሬ እበትነዋለሁ” እንዳለችዋ ዶሮ ባያተርፉም ኢትዮጵያን ከማዳከም ወደ ኋላ አይሉም። ኢትዮጵያ ጠሎች ይህን ሁሉ ደባ ፈጽመው አሁንም አለሙም፣ አላደጉም፣ አላተረፉም፣ አልበለጸጉም። ቢለሙ፣ ቢያድጉ ቢያተርፉና ቢበለጽጉ ኖሮ እሰየው – እንደመዥገር የተጣበቁባትን ኢትዮጵያ ለቀቅ ያደርጓት ነበር። ክፉዎች ሁሉ የብዝበዛ ምንጫቸው ኢትዮጵያ ነች። ከቻሉ ነዋሪዎቿን እያጋጩ፣ ሃሚታ፣ስድብና የዘር ልዩነት እየፈበረኩ በማንአለብኝነት ይቦጠቡጧታል፣ ካልቻሉ ደግሞ ያሳደገቻቸውን ኢትዮጵያ የመሰደዳቸው ምክንያት አድርገው የምዕራቡ ዓለም የመኖርያ ፍቃድ ማግኛ ካርዳቸው ያደርጓታል። ክፉዎች “የበሉበትን ወጨት ሰባሪዎች” ናቸው። የመዥገር ፖለቲካ (parasitic politics) የኅልውና ጠንቅ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ክፉኛ ጎድቷታል።
የመፍትሄ ሃሳብ
“አዛኝ ቅቤ አንጓች” አስመሳይ እብብታቸው መሸጎጡን የማያውቁ የዋህ ፖለቲከኞች “ስሜት አብራጅ” እንጂ “መፍትሄ አምጭ” ውሳኔ ላይ ላይ መድረስ አይችሉም። “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” (repeating the same shit) ማለት ይህ ነው። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ይወርዳል፣ አሁንም “ያለፈው መንግሥት ይሻል ነበር” የሚለው ብሶት ይደገማል። “ታጥቦ ጭቃ ፖለቲካ” – አሁንም ብስጭት (frustration)፣ ተስፋ መቁረጥ (disillusionment) ተደጋጋሚና ፍሬያማ ባልሆነ ጠባይ ሲጠመዱ መኖር (engaged in repetitive and unproductive behavior)።
የባሰው ኢፍትሃዊነት ዝም ማለት ነው (The worst injustice is to be silent)። ዝም ያለ አዋቂና ምሁር ዝም በማለቱ በእግዚአብሄር ዘንድ ተጠያቂ ነው። መሠረታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር፣ የችግሩ ውስብስብነት ነው። ውስብስብ ነገሮች የሚፈቱት በአዋቂ ነው። ስለሆነም፤
ሀ. “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ብሂል እንዳይደገም የኢትዮጵያ ጉዳይ በአዋቂዎችና በአገር ወዳዶች መመከር ይኖርበታል። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በወያኔ የተባረሩት ምሁራን ዝምታቸውን ሰብረው “የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል” ብለው የፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ የመፍትሄ ሃሳብ ሊያመነጩ ይገባል።
ለ. ጡረተኞች ጭምር በአገሪቱ ልዩ ልዩ መንግሥታዊ የአስተዳደር ዘርፎችና በአገሪቱ መከላከያ ኃይል ሲሥሩ የነበሩ ሁሉ ቆም ብለው “የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳስቦኛል” በሚል መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ሐ. የሃገር ሽማግሌዎች፣ በንግዱና በተለያዩ በማህበራዊ ትስስር ዘርፉ አስተዋጾ ሲያደርጉ የነበሩ አገር ወዳዶች ሁሉ በውይይቶች መሳተፍ ይገባቸዋል።
መ. መምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የበረራ ሠራተኞች፣ ሾፌሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች፣መሃንዲሶች፣ ተማሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ተዋንያን፣ ድምጻውያን፣ አትሌቶች፣ ሙዚቀኞች፣ ባጠቃላይ ሁሉም – የአገሪቱን ተደጋጋሚ ውድቀት ለማስቀረት በፖለቲካ ጉዳይ ላይ መሳተፋቸው ወሳኝ ነው። ማንም ተራ ጮሌ ዳግም ወደ መንግሥት ሥልጣን እንዲመጣ ዝም ማለት አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የኅሊና ጸጸት ውስጥ ያደርጋል። ሞኝነትና ከንቱ ስሜት ሊቆም ይገባል።
ሠ. የኦርቶዶክድ ቤተ ክርስትያን አባቶች ፍርሃታቸውን አቅበው መንግሥትን መገሰጽ አለባቸው። ይህ ሁሉ ምዕመን በዘረኞች ሲገደሉና ሲታረዱ ዝም ማለት እንኳንስ ከሃይማኖት አባቶች ይቅርና ከድመትም አይጠበቅም። የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤቱ እስልምና ሲጠቃ ዝም ማለቱንም ያቁም።
መደምደምያ
በህይወት ያሉ ቁልፍ የአስተዳደር ሰዎችና በሳል ስብዕናዎች ከመከሩበት የአገሪቱ ዋነኛ ጠላቶች ሰርገው ገብተው አገሪቱን ወደ ኋልዮሽ መገፍተራቸው ይቆማል። ከላይ የተጠቀሱት አብዛኛዎቹ እድሜና ልምድ ጠገብ በመሆናቸው የመፍትሄ ሃሳብ አያጡም። አንጋፋዎቹ ምሁራን ፈጥነው ኢትዮጵያን ካላዳኑ በቀር ሃገራቸው የጠላቶች መፈንጪያ ሆና ትቀጥላለች፣ ልጅ የልጅ ልጆቻቸውም እንደተሰደዱ ይቀራሉ። “ውጡ ካገራችን” የሚባልበት ቀን ከመጣም የተሰደዱት የሚመለሱባት አገር አትኖራቸውም። “እኔ ምን አገባኝ፣ ነገ ወደ ውጭ እሄዳለሁ” የሚለው ራስ ወዳድነት በአርበኞች አፅም ላይ የመራመድ ክህደት (betrayal) ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሌሎች አገሮች ሰላምን ያጣጥም ዘንድ መልካም መልካሙን ሃሳብ ይወያይበት። መልካም ባልሆነው ጋሬጣ ላይ እየተነታረክን ጊዜ አናጥፋ። መፍትሄ ከውጭ አይመጣም። “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ” ነው። ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን የደረሰ ሁሉ ነገ ዛሬ ሳይል በጋራ በህብረት መቆም አለበት። በዘር ልዩነት የሚያባላውን የዘረኞች ምሽግ መደርመስ ጊዜ አይሰጠውም። የአማራ፣ ትግራይና ኦሮሞ ልሂቃን ሚዛን በማይደፉና ለመኖር ዋስትና በማይሰጡ አላፊ ነገሮች እየተሻኮቱ ወገናቸውን እመከራ አይዳርጉ። ለመሆኑ የአማራ፣ የትግራይና የኦሮሞ ልሂቃን እንዴት ቆም ብለው የዘረኞችን ደባ ማጤን ተሳናቸው? የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር እልባት እንዳያገኝ – አዙሪቱንና ዑደቱን የሚያጦዙት – ዘረኞች ዛሬም የማጋጨቱን ሤራና ሸር ሲጎነጉኑ እያየ ዝም የሚለው የፖለቲካ ልሂቃን – ምን ይሰማው ይሆን?
አንድ ትልቅ ሃቅ አለ። በኢትዮጵያ መቀለድ ቅድስት አገር አድርጎ በሠራት እግዚአብሄር መቀለድ ነው። ተደጋጋሚ ስህተት ባለመሥራት “ካሁኑ መንግሥት ይልቅ ያለፈው ይሻል ነበር” የሚባለው ጸጸትና ቁጭት ላንዴና ለመጨረሻ እንዲቀረፍ – ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ ባንድነት ሊነሳ ይገባል። የሕዝብን ሥልጣን የሚቀሙ – ችግርና ድህነት፣ አድሎና በደል፣ ወከባና ሁከት አምጭዎች ይወገዱ።
ሰው ያስባል እግዚአብሄር ይፈጽማል – ለሁሉም የእርሱ የአምላካችን እርዳታ ይጨመርበት።