በሥልጣን ላይ ያለ አገዛዝ/‹‹የፖለቲካ ማኅበር›› የ‹‹ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን›› የመጥራትና የመሰብሰብ መብት ማን ሰጠው?
ከይኄይስ እውነቱ
ኢትዮጵያ አገራችን አሁን የምትገኝበት ምስቅልቅል በርእሰ ጉዳዩ ላይ እንድንነጋገር የሚያደርግ አይደለም፡፡ በድፍረት ለመናገር ሕዝብም (ከቀበሌ ጀምሮ በየፖለቲካ መዋቅሩ ከርሡን አስቀድሞ የሚልከሰከሰውንና የተቈረጠውን የአገዛዙን ዕድሜ ለመቀጠል የሚራወጠውን ጨምሮ) እንደ ሰው ተፈጥሮ ‹ሰው› መሆን አቅቶት ‹ሬሳ› ሆኖ ባርነትን የመረጠ የሚመስልበት ሁናቴ ውስጥ መገኘቱ÷ በወሬ አገር ይገነባ ይመስል ከወያኔ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአገዛዙን ቅጥፈት እያዳመጠ ውሸት በማራገብ በተዘዋዋሪ ለፋሺስቶች ተባበሪ መሆኑ÷ ከሥጋዊውም ከመንፈሳዊውም ሕይወት ሳይሆን በግብዝነት ስንፍናውን በሃይማኖት ስም ደብቆ ቤተ ክርስቲያኑን ከነሙሉ ሀብቷ ለዐላውያን ካስረከበ በኋላ ለበዓል ክርስትና ‹ዓለም ጉድ አለ› እያለ በቀን ቅዠት ውስጥ መገኘቱ÷ አንዳንዱም በስውር ተልእኮ ‹የአእላፋት ዝማሬ› እያለ በተራ ‹ጭፈራ› ብዙዎችን ገደል ይዞ እየገባ መሆኑ፤ ባንፃሩም ለህልውና ትግል ተገደው ጫካ የገቡት/በረሃ የወረዱት ወገኖቻችን ለጠላቶቻቸው በመመቸታቸው፤ በተለይም ብአዴን ለተባለው የአገር ነቀርሳ በወንዝና በዝምድና ቋጠሮ የሚያሳዩት ቸልተኝነትና ልፍስፍስነት÷ አለን ብለው የሚኮሩባቸው እሤቶችና ተግባራቸው (በተለይም ውስጣዊ አንድነትን በማምጣት፣ በፖለቲካም ሆነ በወታደራዊ አደረጃጀት፣ ወጥነት ባለው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ፣ እንዲሁም በጠንካራ ዲስፕሊንና በመከባበር የማይገለጽ መሆኑ ወዘተ.) የማይገናኝ መሆኑ÷ ከውስጣቸውም ጥቂት የማይባሉ (ከመነሻውም ሆነ ከጊዜ በኋላ የተነሡ) ከሃዲዎች/ባንዳዎች በአመራርም ሆነ በተራ ተዋጊነት መገኘታቸውና ለጥቅማ ጥቅም ተገዝተው ለፋሺስታዊው አገዛዝ ማደራቸው÷ አልፎ ተርፎም የርስ በርስ ግጭት መፍጠራቸው÷ ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከምቢያው ቂጥ እንዲሉ ህልውናው አደጋ ላይ ከወደቀው ሕዝብ ይልቅ ጊዜያዊ ሥልጣን ዐቅላቸውን ያሳታቸው መሆኑ፤ በማናቸውም መመዘኛ መወገድ የሚገባው የሞተው አገዛዝ በነርሱ ድክመትና በሚዲያ ላይ በሚያራግበው ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነፍስ ዘርቶ እንዲቀጥል ምክንያት በመሆናቸው ርእስ ሊሆን በማይገባው ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ተገደድሁ፡፡
ላለፉት 7 ዓመታት ኢትዮጵያን በታሪካችን ተወዳዳሪ በሌለው ሁናቴ እያፈረሳትና እያጠፋት ያለ ኃይል ሳይገባው በጉልበት በያዘው መንበር ላይ ‹ምርጫ› እያለ የተለመደውን ድራማ እንዲሠራ የሚፈቀድ ‹ሬሳ› የሆነ ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን እንዴት በድፍረት ትዘልፋለህ የሚል ወገን ብዙ ይመስለኛል፡፡ ዘለፋ ሳይሆን እውነታ ነው፡፡ መቼም አእምሮና ኅሊና ካለን ሩቅ ሳንሔድ በዚሁ በኛው ክፍለ ዓለም በአፍሪቃ የተለያዩ አገሮች የሚሆነውን ማስተዋል ነው፡፡ ምን ነካን ጎበዝ! ከዚህ በታች ወዴት ልንወርድ ነው? ለመገፋትም እኮ ጠርዝ ያስፈልጋል፡፡ የኛ ‹ጠርዝ› የቱ ጋ ነው? ካለፍነው እኮ ዓመታት ተቆጥሮአል፡፡ የሰውነታችንን ቱምቢ/ውኃ ልክ ማን ወሰደብን?
በወያኔ ትግሬና በተወራጁ የኦሕዴድ/ኦነግ የኦሮሞ ጐሠኞች አገዛዞች ‹‹የፖለቲካ ማኅበር›› የሚባል ነበረ/አለ? የተቃዋሚ ፓርቲ የሚባል ነበረ? አሁንስ አለ? ከሌለ እነዚህ ከአገዛዙ ጋር ተሰበሰቡ የተባሉት እነማን ናቸው? ማንን ነው የወከሉት? ምንድን ነው የሚፈልጉት? ሕዝብና አገር ሲታመስ የት ነበሩ? የእምነት ተቋማት ሲወድሙ፣ መዋቅሮቻቸው በዓላውያን በጉልበት ሲያዙ፣ አማንያን በጠራራ ፀሐይ ሲዋረዱ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ የት ነበሩ? ካህናት፣ መነኮሳትና የአብነት ተማሪዎች ሲረሸኑ የት ነበሩ? አሁን ከየት ተገኙ? ደጋግሞ እንደተነገረው በጐሣ ሥርዓት ውስጥ ለሕዝብ ላገር ሊቆም የሚችል የፖለቲካ ማኅበር ሊኖር አይችልም፡፡ ተፈጥሮው አይፈቅድለትምና፡፡ በወያኔም ሆነ በውላጁ ፋሺስታዊ አገዛዝ የታየው እውነታ ይኸው ነው፡፡ ‹ፓርቲ› ብሎ ራሱን በጐሣ ያደራጀው ስብስብም ጐሣውን በመደበቂያነት (ህልውናው አደጋ ላይ ሲወድቅ ወይም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሕዝባዊ መሠረቴ ነው ብሎ) ለመጠቀም እንጂ ለሁሉም የጐሣው አባላት የቆመ አይደለም፡፡ የጐሣ ቡድን እና በሠለጠነ መልኩ የሚደረግ የፓርቲ ፖለቲካ ዓይንና ናጫ ናቸው፡፡፡ ስለሆነም ፍላጎቱ ያላቸው ቡድኖች ቢኖሩም እንኳን ‹‹የተቃዋሚ ፓርቲ›› የሚባል አደረጃጀት ሊኖር አይችልም፡፡ የጐሣ ሥርዓቱ አይፈቅድምና፡፡ ይህ እንዳይሆን የጐሣ ሥርዓቱ በሕግም በመዋቅርም ያረጋግጣል/አረጋግጧልም፡፡ ከዚህ ውጭ በጐሣ አገዛዝ ውስጥ በፖለቲካ ስም የሚደራጅ ስብስብ የያዘው ‹ስም› ብቻ የጐሣ ላለመሆኑ ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ስሙን ተከትሎም ሀገር-አቀፍ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ‹‹የመጫወቻው ሕግ›› (ገዢው ስምምነትና መርህ) ጐሣን መሠረት ያደረገ ነውና፡፡
አገራችን ባላት የፖለቲካ ታሪክ እስካሁን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተደረገ ምርጫ የመንግሥት ሥልጣን የተያዘበት ሁናቴ የለም፡፡ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሩን መንግሥት ለመመሥረት ፍላጎቱን ቢያሳይምና መብቱን ለመጠቀም ቢሞክርም ወያኔ ትግሬ ያጨናገፈው የ1997ቱ ምርጫም በደም የተደመደመ ነው፡፡ ‹ምርጫ› የተባሉት ሁሉ አስቀድሞ የተሠሩ ድራማዎችና ‹የተውኔቱን ጽሑፍ› ተከትሎ የተደረጉ ትወናዎች ናቸው፡፡ ለዚያውም ኃይልና ዓመፃ የሠፈኑባቸው፣ አልፎ ተርፎም የሰው ሕይወት የተገበረባቸው፣ እና በመጥፎ ምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ አነጋገር (ጥቂት የደበዘዙ ልዩ ሁናቴዎችን የግለሰቦችን ጥረት/ተጋድሎ ትተን) በሁለቱም ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዞች የመደራጀትም ሆነ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግም ሆነ ሐሳብን በንግግርም ሆነ በጽሑፍ የመግለጽ ነፃነት በተግባር አልነበረም፤ የለም፡፡ ከዚህ አልፎ አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦችን በማቅረብ፣ በመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት እንዲኖርና ግልጽነት የሠፈነበት መሆኑን በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ‹ተቃዋሚ ቡድኖች› አልነበሩም፤ የሉም፡፡ መሥዋዕትነት ተከፍሎም ቢሆን እንኳን አንድም ጊዜ ሕዝብን አስተባብሮ ‹የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ› በተግባር ያደረገ ‹ተቃዋሚ ቡድን› አልታየም፡፡ በፈተና ነጥሮ ለመውጣት ከመነሻውም የተዘጋጀ አንድም ‹ተቃዋሚ ቡድን› አልታየም፡፡ ‹ምርጫ› በሚባለው ድራማ ጊዜ ለአገዛዙ ቋሚ ለጓሚ÷ ገረድ ደንገጥር በመሆን ፍርፋሪ ለመልቀም የሚሰባሰቡ ባለድርጎዎች ግን እንደ አሸን የፈሉበት ጊዜ መሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ እነዚህ ባለ ድርጎዎች ‹ተቃዋሚዎች› ሳይሆኑ አጃቢዎች፣ አዳማቂዎች፣ ለአገዛዙ የሐሰት ሕጋዊነትና ተቀባይነት ለመስጠት በከለላነት የሚያገለግሉ አድርባዮች/ሎሌዎች የሚለው ስም በትክክል ይገልጻቸዋል፡፡
በቅርቡ ርጉም ዐቢይ ‹ተቃዋሚ ፓርቲዎችን› ሰብስቦ አነጋገረ የሚል ወሬ ሰማሁ፡፡ ባይገርመኝም የእሱም ድፍረት፣ ‹ተቃዋሚዎች› የተባሉት ባለድርጎዎች ይሉኝታ ቢስነት ለሕዝብና ላገር ያላቸውን ከፍተኛ ንቀት በድጋሚ አሳየኝ፡፡ እንደሚታወቀው አገዛዞች ራሳቸው ላወጡት ሕግ እንኳን ተገዢዎች አይደሉም፡፡ ለመሆኑ ርጉም ዐቢይ የትኛው ሕግ ፈቅዶለት ነው ‹ባለ ድርጎዎቹን› የሰበሰበው? በየትኛው ችሎታ? በ‹መንግሥትነት› ወይስ በጉልበት በያዘው ‹ገዢ ፓርቲነት›? ወያኔ ትግሬ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መልክዐ ምድር ሲያበላሽ ከፈጸመው ይቅርታ የሌለው ጥፋት አንዱ ሆን ብሎ በ‹መንግሥት› እና ‹ፓርቲ› መካከል ያለውን ልዩነት ደብዛ ማጥፋቱ ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ከሁለት አንዱን ‹ባርኔጣ› አጥልቆ ብቅ ይላል፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት፣ በስም ብቻ ካልሆነ በሦስቱ የመንግሥት የሥልጣን አካላት/ቅርንጫፎች – ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው – መካከል አንዱ ከሌላው ኃያል ሆኖ ገኖ እንዳይወጣ የርስ በርስ ምዘናና ቊጥጥር ሥርዓት በሕግም ሆነ በተግባር በሌለበት አንዱ አካል በአምባገነንነት እንደፈለገው ቢፈነጭ የሚገርም አይሆንም፡፡ ከዘመነ ደርግ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አገዛዞች በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስቱንም የመንግሥት ቅርንጫፎች ሚና በተግባር ጠቅልሎ የያዘው ‹ሕግ አስፈጻሚው› አካል ነው፡፡ ከወያኔ ዘመን ጀምሮ የዘለቀው ‹ሙት ሸንጎ/ፓርላማ› ዋና ተግባሩ አስፈጻሚው (ርግጡን ለመናገር የአስፈጻሚው አለቃ) ያቀረበለትን አጀንዳ በጥንቃቄ ሳያስብበትና ሳይመረምር እጅ እስኪቃጠል አጨብጭቦ ማጽደቅ መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ከኅሊናቸው የተፋቱና አእምሮአቸውን ለሌሎች አሳልፈው የሰጡ ነሆለሎች ስብስብ ነው፡፡ እነዚህ ‹የሙታን ስብስቦች› ‹ተቃዋሚ› እንደተባሉት በአፍኣ እንደሚገኙ ባለድርጎዎች፣ አገዛዙ በ‹ቋሚነት› የያዛቸው በውሳጤ የሚገኙ ‹ባለ ድርጎዎች› ናቸው፡፡ ቦታው ላይ እስካሉና አንዳንዶቹም ጊዜአቸው ካበቃ በኋላ በሚያሳዩት ሎሌነት መጠን ቤት፣ መሬት፣ ተሽከርካሪ፣ በንቅዘት ያለ መጠየቅና ሌሎችንም ጥቅማ ጥቅሞች ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል የሕግ የበላይነት የለም ካልን ዳኝነት አፈር ድቤ በልቷል ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ለአገዛዙ ህልውና ወሳኝ የሆኑ የዳኝነት ጉዳዮች በስልክ በሚተላለፍ ቀጭን ትእዛዝ ወይም በቀላጤ የሚወሰነው ‹አስፈጻሚው› በተባለው አካል ነው፡፡
ይህን እውነታ ይዘን ስንነጋገር፣ የትኛውም አገዛዝ (መንግሥት ማለት የማይገባ ክብር መስጠት ስለሚሆን) ወይም ‹ገዢ ፓርቲ› የተደራጁ የፖለቲካ ተቀናቃኞች ቢኖሩት እንኳን (በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሉም እንጂ) ከምርጫ ጋር በተያያዘ መሰብሰብ የሚችልበት አንዳች ሥልጣን የለውም፡፡ ድርጊታቸውንም እሱ በፈለገው መንገድ መቆጣጠር በጭራሽ አይችልም፡፡ ሕግ በማይሠራባትና ሥርዓተ አልበኝነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ግን ሰውን ገድሎና በግሬደር አፍሶ ቀብሮ ለአስከሬን ዛፍ ጥላ እንተክላለን ማለትም ይቻላል፡፡ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አገርና በሕዝብ የተመረጠ ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ቢኖረን ሊያደርግ የሚችለው ለነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የሚያገለግል የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ በሕዝብና በተቃዋሚዎች ተሳትፎ ተተችቶ እንዲጸድቅ የማድረግ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲደረግ ኃላፊነት የመውሰድ፣ ምርጫ ባግባቡ እንዲካሔድ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ በፖለቲካ ማኅበር የተደራጁ ዜጎች በፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ከባቢን መፍጠር ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ፋሺስታዊውን የርጉም ዐቢይ የጐሣ አገዛዝ የግድ ማስወግድ አለብን የምንለው በዋናነት ሕዝባችንን ከጥፋት ለማዳን/ከጐሣ አገዛዝ ለመታደግ፣ አደጋ ላይ የወደቀውን የአገራችን ህልውና ከነሙሉ መልካም እሤቶቿና ታሪኳ÷ ክብሯና ኩራቷ ለማረጋገጥ፣ የአገራችን ባለቤት ሆነን ያለምንም መሳቀቅ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ተረጋግጦ በፈቃዳችን ሥልጣን ላይ የምናስቀምጠውና የተሰጠውን አደራና ኃላፊነት ሳይወጣ ሲቀር ልናነሣው የምንችለው አካል ሥልጣን መያዙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ በርግጥ እንደ ርጉም ዐቢይ ያለ ዱያታም በአገር መንበረ ሥልጣን ላይ በጭራሽ ቦታ እንዳያገኝም ነው፡፡ ባንፃሩም ምዕራቡን ወይም ምሥራቁን ለመከተል፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ርእዮተ ዓለም ተከታይነት ፈልገን ከሆነ መንገዳችንን ከጅምሩ የምንስት ይመስለኛል፡፡
የሺሕ ዓመታት ታሪክ ያለን ጥንታዊ አገር ነን እያልን፣ የረዥም ዘመናት የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ እንዳለን እያወሳን፣ በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው ቀደምት መሆናችንን እየተናገርን፣ የነፃነት አኩሪ ታሪክ ያለን አገር ሆነን፣ የባለ ብዙ ነገዶች ሕዝብ መለያችን ሆኖ ሳለ፣ ከእምነትም ሆነ ከባህል የመነጩ በርካታ መልካም እሤቶች ባለቤት ሆነን ሳለን፣ ልዑል እግዚአብሔር የተፈጥሮ ጸጋ አድሎን እያለ እንዴት አገርና ሕዝብን ባግባቡ የምንመራበት ሥርዓት ማቆም አቃተን? ‹ሰው› የሚሆን ሰው እንዴት አጣን? በውስጥ አድር ባዩ፣ ከሃዲውና ከርሣሙ፣ በውጭ ደግሞ ባመዛኙ ነገር ሠሪውና አእምሮው በባዕዳን ቅኝ የተገዛ አይሎብን በእጅጉ ተቸገርን፡፡
አንድ የመጨረሻ ነጥብ ላክልና ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ ኢሕአፓ የሚባል የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያቆሸሸ (ወያኔ ለተከለብን የጐሣ ሥርዓት መሠረት የጣለ) ድርጅት ርጉም ዐቢይ በጠራው ስብሰባ ከተገኘ በኋላ ስብሰባውን ረግጦ ወጣ የሚል ወሬም ሰምተናል፡፡ አዬ ጉድ! እኔ እስከማውቀው ድረስ በዚህ ድርጅት ውስጥ የነበሩትና በሕይወት ያሉ አረጋውያን አንዳንዶቹ ንስሓ ገብተው፣ አገር በጐሠኛ ፋሺስቶች እጅ መውደቋን ዐውቀው እያዘኑ አርፈው ተቀምጠዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን (ነፍሳቸውን ይማርና) እንዳሉት በዕርግና ውስጥ የተደበቀ ጕርምስና ይዘው የሥልጣን ፍትወታቸውን ለማርካት ለዘመናት እየቧገቱ ይገኛሉ፡፡ አይ አለመታደል! የድሮዎቹስ በዕድሜም ለጋነት፣ በዕውቀትና ልምድ ባለመብሰልም፣ አገራቸውን በቅጡ ባለማወቅም፣ በባዕዳን ተልእኮ ውስጥ በመውደቅ፣ አንድ ትውልድ በደም አበላ ታጥቦ እንዲያልቅ ምክንያት ቢሆኑም፣ ላልገባቸውና ለተሳሳተ ዓላማም ቢሆን ራሳቸውን እስከ ሞት የታመኑ አድርገው ነበር፡፡ አሁን ተሰብሰበዋል የተባሉት ‹ባለ ድርጎዎች› ፖለቲካን መተዳደሪያ ያደረጉ መሸጦዎች ናቸው፡፡ ኢሕአፓም ከነዚህ መሸጦዎች አንዱ ነው፡፡ እንደ ዘመዳቸው ‹ብርሃኑ ነጋ› የሥልጣን ‹ፍርፋሪ› ካገኘን ብለው በፀሐያቸው መጥለቂያ ሰዓት የተገኙ ብኩኖች ናቸው፡፡ አይ ኢትዮጵያ ስንቱን ጉድ ተሸክማለች?!