>

የታዬ እውነታዎች እና ተጨማሪ ምስክርነት

የታዬ እውነታዎች እና ተጨማሪ ምስክርነት

 

በታዬ ዳንደዓ ቃለመጠይቅ ውስጥ የተነገሩ ጉዳዮች እውነታነት ላይ የብልጽግና ሰዎች ሊያተባብሉ ሲረባረቡ፣ ሌላው የሰማውን ደግሞ ለላማመን ከብዶት ሲያመነታ ታዝቤ ግርም አለኝ

ታዬ የተናገራቸው ጉዳዮች ለሰፊው ሕዝብ በገሃድ አይታወቁ ይሆናል እንጂ፣ በመንግስት አመራር ላይ በነበሩና ቅርበት በነበራቸው ሌሎች ልሂቃን ዘንድ ሁሉም የሚያውቃቸው እውነታዎች ናቸው። በነገራችን ላይ ታዬ ካጋለጣቸው እውነታዎች ውስጥ ከፊሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ በተገኙበት ስብሰባ ላይ የተነገሩ መሆናቸው አይካድም፤ ይፋ ማውጣቱን ታዬ ጀመረው እንጂ።

እስኪ እኔም ስለ አማራ፣ ኦሮሞ እና ሌሎች ጉዳዮች ከታዬ በተጨማሪ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በቅርቡ ለሕዝብ ባጋለጧቸው ጉዳዮች ላይ የራሴን ምስክርነት ልጨምር።

ስለ ኦሮሞ እና አማራ

አብይ አንዱን ወገን ሲያይ ሌላውን ማማትና ማጠልሸት ዋነኛው የፖለቲካ ስልቱ መሆኑን ለማሳየት ያክል አንድ ሁለት ትዝብቶችን ላጋራ። አንድ ቀን ከሌሎች የኦሮሞ አመራሮች ጋር ሆነን ከአብይ ጋር ተሰብስበን ሳለ ፌደራሊዝም ስለማጣላቱ፣ የቀድሞ ንጉሶችን ስለማወደሱ ወ.ዘ.ተ ትችት አዘል ጥያቄ ስናነሳለት፤ መልሱ «አታስቡ በአፌ መስማት የሚፈልጉትን እየነገርኳቸው በተጨባጭ ግን የኦሮሞን ሥልጣን አጠናክራለሁ» አለ።

በዚያው እለት እኛ ከወጣን በኋላ የተወሰኑ የአማራ ልሂቃን ጋር ስብሰባ ነበረው። የዚያን እለት ማታ ከተሰብሳቢዎች አንዱ ከነበረ ሰው ጋር ተደዋውለን ስናወራ፣ «ትንሽ ታገሱኝ እንጂ የኦሮሞ ብሔረተኝነት ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ የጋረጠውን አደጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት አበጅለታለሁ። አሁን አፋቸውን የሚከፍቱትን የኦሮሞ ልሂቃን ከአጭር ጊዜ በኋላ አንዳቸውንም አታይዋቸውም። አጠፋቸዋለሁ። ኦሮሚያ የሚባለው ነገርም አይኖርም» እንዳላቸው ነገረኝ። የዚህን ንግግር እውነታነት በወቅቱ እዚያው የነበረን ለአብይ ቅርብ የሆነን የኦሮሞ ተወላጅ በሌላ ጊዜ ጠይቄው አረጋገጠልኝ።

በነገራችን ላይ እኔን ሁሌ ሲተቸኝ የነበረው «የሰሜኖችን ጌም መጫወት አትችልም፤ ሁሉን ነገር በገሃድ ትናገራቸዋለህ» በሚል ነበር።

ጥበቃዎቼን በሌሊት አስነስተው ሊገድሉኝ የሞከሩ ጊዜ ደግሞ፣ ሁለታችንንም የሚቀርብ አንድ ሰው ልኮ ድርጊቱ ላይ እጁ እንደሌለና ውሳኔው የምክትሉ (ደመቀ መኮንን) እንደሆነ አስነገረኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገር ውጭ በመሆኑ፣ ደመቀ በእጁ የገባውን ሥልጣን ተጥቀሞ ያደረገው እንደሆነ፣ ይሄም “ኦሮሞን እርስ በርሱ ለማባላት” ጠላት የሸረበው ሴራ መሆኑንም አከለበት። ይህንኑ ትርክት የሚያራምዱ ፖስቶች በፌስቡክ ሲለቀቁ እንደነበር ታስታውሳለችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ቀን የግንቦት 7 አመራር አባላት የነበሩትን አንዳርጋቸው ጽጌ እና ነዓምን ዘለቀ ቤቴ ጋብዤ መወያየታችንን አብይ ሰምቶ ነበርና ሲያገኘኝ «እነዚያ ሰዎች ሊያጠፉህ እያሴሩ ነው። በአካል ባታገኛቸው ይሻላል። በተለይ ምግብህን ተጠንቀቅ። እነሱ (አማራዎች ማለቱ ነው) ካንተ የባሰ ጠላት እንደሌላቸው ነው የሚያምኑት። ማንኛውንም አጋጣሚ ተጠቅመው ሊያጠፉህ ዝግጁ ናቸው። ተጠንቀቅ! አንተ እንደው ሰው አትሰማም። እኔ በበኩሌ ነግሬሃለሁ» አለኝ። ለካ እነሱንም ያንኑ ሰሞን አግኝቶ ስለእኔ ክፉን ሁሉ ካወራቸው በኋል «እሱን እኔ ራሴ በቅርቡ እደፋዋለሁ» በማለት በእጁ የሽጉጥ ምልክት በማሳየት ጭምር እንደነገራቸው ሰማሁ።

ስለ ወለጋ

ከበቀለ ገርባ ጋር ወደ ወለጋ ለመሄድ ማቀዳችንን ስነግረው «ባትሄድ ይሻልሃል። ወለጋዎች አምርረው ይጠሉሃል። ስንት የግድያ ሴራ አቅደውብህ እንዳከሸፍን አታውቅም። ዝርዝሩን ከፈለክ እገሌ ይነግርሃል» ብሎ አጠገባችን ወደነበረ አንድ ከፍተኛ የፀጥታ ሰው ጠቆመ። “ሄድህላቸውማ በህይወት አይመልሱህም። አንተ ይሄ የሀረርጌ ባህልህ የዋህ ያደርግሃል፤ ሁሉን ሰው ታምናለህ» አለኝ። እኔ በበኩሌ፣ «እንደ አወዛጋቢ የፖለቲካ ሰው ብዙ የሚጠሉኝ፣ ምናልባትም ሊያጠቁኝ የሚፈልጉ ግለሰቦች ሊኖሩ ይቻላሉ።

እንደ ማኅበረሰብ የሚጠላኝም ሆነ ሊያጠቃኝ የሚፈልግ ግን ያለ አይመስለኝም» አልኩት።

ወደ ወለጋ እየሄድን ጌዶ የተባለች ከተማ እንደደረስን ታዬ ደንደዓ ደወለልኛና ጉዞዬ ትክክል እንዳልሆነና “ሸኔ” ሊገድላቸው ከሚፈልጋቸው አምስት ሰዎች ውስጥ አምስተኛው እንደሆንኩ ነገረኝ። እኔም ታዬ የሚነግረኝ መረጃ መነሻው የት እንደሆነ ቀደም ብሎ ከአብይ ጋር ከነበረኝ ወይይት ሰለተረዳሁ፣ «ወደ አንደኛ ደረጃ ከፍ እስክል ድረስ ሥራዬን እቀጥላለሁ» ብዬ ቀለድኩበት።

አብይ ይህን እኔን ወለጋ ብሄድ እንደምገደል ሲያራምድ የነበረውን ትርክት፣ ትንሽ ቆየት ብሎ እራሱም ቢሄድ እንደሚገደል በቤተመንግሥት አዳራሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች በተሰበሰቡበት መናገሩ ትዝ ይላችኋል ብዬ አስባለሁ። ይህን የፀረ-ወለጋ አቋም ከ2018-2022 በነበረው ጊዜ በግል እና በዝግ ውይይት ብቻ ሳይሆን በግልጽ ሲያራምዱ ነበር። በሂደት ቡራዩ ላይ በአነጋገር ዘዬ እየለዩ ወደ ማሰር ሁሉ ደርሰው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ስለ ሸገር

ከታች በምታዩት ቪዲዮ ውስጥ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ «ሸገርን የፈጠርነው የኦሮሞን ፖለቲካ ከአዲስ አበባ ለማስወጣት ነው» በማለት አንድ ባለሥልጣን ነገረኝ ይላል። ዶ/ር ዳኛቸው እንዳለው ይህንን የነገረው ባለሥልጣን አብይ ባይሆን እንኳን፣ ትርክቱ ከአብይ መንጭቶ በተዋረድ ከላይ እስከታች ሲነዛ የነበረ ነው።

ለአማራው ዶ/ር ዳኛቸው «ሸገርን የፈጠርነው የኦሮሞ ፖለቲካን ከአዲስ አበባ ለማውጣት ነው» እያሉ፣ በተገላቢጦሽ ደግሞ ኦሮሞን በግልም በቡድንም ሲያገኙ፣ አንዳንዴ «ሸገርን የመሰረትነው የአማራ የበላይነት ያለባት አዲስ አበባ እንዳትስፋፋ እንደ ዶናት ለመክበብ ነው»፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ «የአማራ ክልል ተስፋፍቶ ከአዲስ አበባ ጋር እንዳይገጥም ድንበር ለማበጀት ነው» ይላሉ። ይህ ምስጢር ሳይሆን የቀድሞው “ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን” ወደ ሸገር ከተማ በተቀየረ ሰሞን በየስብሰባው ለኦሮሞ ማኅበረሰብ ሲነገር የነበረ ትርክት ነው።

አማራውን ሲያገኙ «የኦሮሞን ፖለቲካ ከሸገር ለማውጣት ነው»፣ ዞር ብለው ደግሞ ኦሮሞውን ሲያዋሩ «የአማራን መስፋፋት ለመገደብ ነው» እያሉ ያምታቱ እንጂ፣ ሸገር የተመሰረተበት እውነተኛው ዓላማ ግን የገጠር ቀበሌዎችን ወደከተማ በማካለል መሬትን ከፍ ባለ ዋጋ ለመቸብቸብ እንዲያመች መሆኑ መታወቅ አለበት።

በእኔ እይታ አብይ ብሔሮችንም ሆነ ግለሰቦችን የሚያጥላላው ለአንዱ ወግኖ ሌላውን ለመጥቀም አይደለም። የከፋፍለህ ግዛ ታክቲክ አካል ነው። አንድን ግለሰብ ወይም ቡድን ሲይገኝ በተፃራሪ አቋም ላይ ይገኛል ብሎ የሚያስበውን ሌላ ወገን በማጣጣል በወቅቱ አጠገቡ የነበረውን ለማማለል ይሞክራል። የኦሮሞ ልሂቅ የሆነ ሰው ሁሉ ስለ አማራ፣ አማራ የሆነ ደግሞ ስለ ኦሮሞ ክፉው ሲወራ መስማት የሚያስደስተው ይመስለዋል። በትግራይ እና አማራ፤ በሲዳማ እና ወላይታም እንዲሁ።

በአንድ ብሔር ተወላጅ መካከል ራሱ በጎሳ እና በአካባቢ ለያይቶ ማማት ልማዱ ነው። በኦሮሞ ውስጥ የወለጋን ተወላጅ ሲያገኝ አርሲን ወይም ሸዋን ይቦጭቃል። ለምሳሌ ያኔ ወለጋን ሲያጥላላ እንዳልነበረ ሁሉ፣ በቅርቡ ደግሞ የተወሰኑ የወለጋ ልሂቃንን ምሳ ጋብዞ ሽመልስ የሸዋ ማፊያ አደራጅቶ ኦሮሚያን እየበዘበዘ መሆኑን፣ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድና ተተኪ ሰውም እንዲያስቡበት ነገራቸው። ከጥቂት ቀናት በኋላ ይህንኑ አነጋገር ለአርሲ አከባቢ ተወላጆች ደገመላቸው። በአማራው ወገንም በተለይ ጎንደር እና ጎጃም ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ በሃሜት የመከፋፈል ስልት ይጠቀማል። እነ አምባቸው የተገደሉ ሰሞን ሲነዛ ከነበረው አስቀያሚ ትርክት ጀምሮ፣ በአሁኑ ወቅት እየተጠቀመበት ያለውን ታክቲክ ውስጥ-አዋቂ የሆኑ የአማራ ልሂቃን ብዙ ሊነግሩን እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ። በሃይማኖት ረገድ የሚጫወተውን እዚህ መፃፍ ደባሪ ስለሆነ ለጊዜው መተዉ ይሻላል።

መጀመሪያ ላይ እንደጠቀስኩት ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ለማራራቅ አብይ ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የሃሜት ስልቶች ዛሬ ላይ አብዛኛው የሀገራችን ልሂቃን ነቅተውበታል። ብዙ ሰው የማይናገረው አንድም በራሱ እና በቤተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የበቀል እርምጃ ፈርቶ ነው። ሌላው ደግሞ አብይ ስለ ግለሰቦች፣ ብሔሮች እና ሃይማኖቶች የሚናገረውን ሃሜት በሕዝብ ፊት መድገም ቀፍፎት ነው። እኔም ይህቺን ምስክርነት ለማጋራት የወሰንኩት አንዳንድ አዲስ ተደማሪ ፋርሴቡላዎች ታዬ ደንደዓ የተናገራቸውን ታሪኮች ለማጣጣል ሲሞክሩ በማየቴ ነው። በሚዲያ ታዬ የተናገረውን እውነትነት ለመካድ እየሞከሩ፣ በግል ደግሞ የአብይን ሃሜቶች እንደ ስትራቴጂካዊ ብልጠት ሲያደንቁ ይስተዋላሉ። የአብይ ተራ ብልጣብልጥነት ሰዎችን እና ቡድኖችን አቃቅሮ ለጊዜያዊ ሥልጣን መደላደል ቢረዳውም፤ ሀገሪቷን ለከፋ የእርስበርስ ጦርነት እና እያየን ላለነው የኦኮኖሚ መንኮታኮት እንዳጋለጣት ይዘነጋሉ።

የአብይ በሃሜት የመከፋፈል ስልት ሕዝባችን እና ሀገራችን ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመጠገንና ከዚህም የባሰ አደጋ እንዳያደርስ ለመግታት፣ ታዬ ደንደዓ የጀመረውን የማጋለጥ እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ ነው። እስካሁን አብይ በነዛቸው ሃሜቶች መጠራጠር እና መቃቃር ውስጥ ገብተው የቆዩ የፖለቲካ ልሂቃንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው እና ተናብበው መስራት ይኖርባቸዋል።

ጃዋር መሐመድ

@Jawar_Mohammed

Filed in: Amharic